ቻይና በኤአይ ዙሪያ "አደገኛ ፉክክር" እያደረገች ነው በሚል የሚቀርብባትን አስተያየት ተቸች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ቻይና በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) አስተዳደር ዙሪያ "የስጋት ትርክቶች" ያለቻቸውን አስተያየቶች በመቃወም፣ "ግጭት እና አደገኛ ፉክክር ውስጥ ከመግባት መቆጠብ ያስፈልጋል" ስትል አስጠነቀቀች።

አገሪቱ ይህን ያለችው፣ የአንትሮፒክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳሪዮ አሞዴይ የኤአይ እድገት ፍጥነት እንዲቀንስ ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው። ይህም ቻይና በኤአይ ውድድር ውስጥ ቀድማ እንዳትወጣ በሚያደርግ መልኩ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ ባሉ ትልልቅ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቤተ ሙከራዎች ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያዎች፣ ኤአይ ሊያስከትል ስለሚችለው አደጋ ጠንከር ያሉ ማስጠንቀቂያዎችን ሲያቀርቡ ተስተውለዋል። አንዳንዶቹም ቴክኖሎጂው የሰው ዘርን እስከ ማጥፋት ሊደርስ ይችላል ሲሉ ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው፣ አገራቸው ከቻይና በፈጠነ መልኩ የኤአይ ቴክኖሎጂን ማልማት መቻሏን ማረጋገጥ እሳቸው ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ እንደሆነ ገልፀዋል።

የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጉኦ ጂያኩን "የስጋት፣ የግጭት እና የአደገኛ ፉክክር ትርክቶች የዓለም አቀፍ የኤአይ አስተዳደር ሂደትን ከማወክ ባለፈ ለማንም አይጠቅሙም" ሲሉ ሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

"ሁሉም ወገኖች ኤአይ ግልፅ፣ ሁሉን አቀፍ፣ ለሁሉም ጠቃሚ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲቀጥል በጋራ መስራት አለባቸው" ሲሉም አክለዋል።

እነዚህ አስተያየቶች የዓለም ቀዳሚ የኤአይ ኃያላን በሆኑት ሁለቱ አገሮች ቻይና እና አሜሪካ መካከል ስምምነት ላይ መድረስ ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ የሚያሳዩ ናቸው።

የአሜሪካ እና የቻይና መንግሥታት የኤአይ ልማትን ለመቆጣጠር ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ብሎ ማሰብ "ሊሆን በማይችል ደረጃ አስቸጋሪ ነው" ሲሉ በሲንጋፖር የኤስ. ራጃራትናም ዓለም አቀፍ ጥናቶች ትምህርት ቤት የወታደራዊ ጥናት ፕሮግራም ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ቻንግ ጁን ያን ገልፀዋል።

"የብሔራዊ ደኅንነት ፍላጎቶቻቸው አካል በመሆኑ፣ ከኤአይ ጋር በተገናኘ ፍጥነቱን መቀነስ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ አቀራረብ እንዲኖረው መተባበር እጅግ የማይታሰብ ነው" ብለዋል።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ ሁለቱ ግዙፍ የዓለም ኢኮኖሚ ባለቤቶች አሜሪካ እና ቻይና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ቀዳሚነትን ለማግኘት በሚያደርጉት ፉክክር ዋናውን ስፍራ ይዟል።

አሜሪካ ወሳኝ የኤሌክትሮኒክስ ቺፖች ለቻይና እንዳይላኩ እገዳ ብታደርግም፣ የቻይና የኤአይ ፈጠራ እየሰፋ መጥቷል።

ብዙ ባለሙያዎች እንደሚያምኑት አሜሪካ አሁንም በዘርፉ ቀዳሚውን ደረጃ ይዛ ትገኛለች። የቻይና ኩባንያዎች ደግሞ በአሜሪካ የኤአይ ኩባንያዎች ላይ በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር የሚያፈሱትን ኢንቨስተሮች ትኩረት ለመሳብ ከአሜሪካ ጋር ፉክክራቸውን ተያይዘዋል።

ሆኖም ኤአይ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል የቻይናውን መሪ ዢ ጂንፒንግን ጨምሮ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ቻይና "ዕድገትን እና ደኅንነትን ማጣጣም" እንዳለባት፣ ተዛማጅ ሕጎችንና የሥነ ምግባር መመሪያዎችንም ማሻሻል እንዳለባት፣ እንዲሁም አደጋዎችን የመከላከል አቅሟን በማጠናከር "የሕዝቡን ፍላጎት እና የብሔራዊ ደኅንነት ጥቅሞችን መጠበቅ" እንዳለባት የአገሪቱ የደኅንነት ሚኒስትር ቼን ይዢን እሁድ ዕለት ገልጸዋል።

እንደ ውጭ የስለላ ተቋማት ያሉ "የጠላት ኃይሎች" ኤአይን ለክፉ ዓላማ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ አስጠንቅቀው፣ በአለም አቀፍ ደረጃ ትብብር እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።

በአትላንቲክ ካውንስል የቻይና ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ኬንተን ቲቦ በቅርቡ ባወጡት ጽሑፍ፣ "ዋሽንግተን እና ቤይጂንግ በኤአይ አደጋዎች ጉዳይ የጋራ ግንዛቤ እንዳላቸው የሚያመለክቱ ጠንካራ ምልክቶች አሉ" ብለዋል።

ቻይና ከአሜሪካ ጋር ለመስራት "ቴክኒካዊ ምክንያቶች" አሏት ብላ የምትከራከረው ቲቦ፣ ምክንያቱም የቻይና ኤአይ አበልጻጊዎች ሞዴሎቻቸው ከቻይና ውጭ እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ማየት፣ እንዲሁም ያሉባቸውን ድክመቶች መለየትና መረዳት ስለሚችሉ ነው ትላለች።

ቻይና የዓለም ሰው ሰራሽ አስተውሎት ትብብር ድርጅትን ሐምሌ ወር ላይ አቋቁማለች። ይህ ተቋም ዓለም አቀፍ የኤአይ አስተዳደርን የመግራት ዓላማ ያለው ነው።

ይህ እየሆነ ያለው በአሜሪካ ውስጥ የኤአይ ቁጥጥር እንዲጠናከር የሚጠይቁ ድምፆች እየበረቱ ባሉበት ወቅት ነው።

በተለይም የቀድሞው የአንትሮፒክ ተመራማሪ ጃኮብ ኮክሰን ባለፈው ሳምንት፣ "አሁን ያለው የኤአይ እድገት ፍጥነት ከቀጠለ፣ ሁላችንም በቅርብ ጊዜ ልንሞት የምንችልበት እድል ከፍተኛ ነው" ሲሉ ከባድ ማስጠንቀቂያ ከሰጡ በኋላ በዘርፉ ላይ የሚደረገው ውይይት ይበልጥ ተጠናክሯል።

ሆኖም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ አደጋዎቹን አቅልለው በመመልከት አሜሪካ በቻይና ላይ ያላትን ማስጠበቅ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። "ምክንያቱም ኤአይን የሚያሸንፍ ሁሉንም ያሸንፋል" ብለዋል።