ቀጥታ, በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ለመወያየት ኦማን ያዘጋጀችው የባሕረሰላጤው አገራት ጉባዔ ወደ ሌላ ጊዜ ተላለፈ

ኦማን በሆርሙዝ ወሽመጥ አዲስ የመርከቦች መተላለፊያ ላይ ለመነጋገር ለሰኞ አቅዳ የነበረውን ቀጣናዊ ጉባዔ መሰረዟን አስታወቀች። ጉባዔው ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው በአገሪቱ ደቡባዊ ከተማ ሳላህ ነበር። የኦማን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እሁድ አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ ጉባዔው ወደ ሌላ ቀን የተላለፈው “ገንቢ የሆነ ውይይት እንዲካሄድ የሚያስችል ሁኔታን ለመፍጠር ነው” ብሏል።

ጭምቅ ሃሳብ

በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ለመወያየት ኦማን ያዘጋጀችው የባሕረሰላጤው አገራት ጉባዔ ወደ ሌላ ጊዜ ተላለፈ

የቀጥታ ሽፋን

በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ለመወያየት ኦማን ያዘጋጀችው የባሕረ ሰላጤው አገራት ጉባዔ ወደ ሌላ ጊዜ ተላለፈ

ኦማን በሆርሙዝ ወሽመጥ አዲስ የመርከቦች መተላለፊያ ላይ ለመነጋገር ለሰኞ አቅዳ የነበረውን ቀጣናዊ ጉባዔ መሰረዟን አስታወቀች።

ጉባዔው ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው በአገሪቱ ደቡባዊ ከተማ ሳላህ ነበር።

የኦማን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እሁድ አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ ጉባዔው ወደ ሌላ ቀን የተላለፈው “ገንቢ የሆነ ውይይት እንዲካሄድ የሚያስችል ሁኔታን ለመፍጠር ነው” ብሏል።

መግለጫው አክሎም ስብሰባውን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ ያስፈለገው ለቀጣናው ደህንነትና መረጋጋት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ እንዲሁም የቀጣናውን ሕዝቦች የትብብርና የሰላም ፍላጎት የሚያሟሉ ዘላቂ መግባባቶች ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ የውይይት ሁኔታዎችን ለመፍጠር ካለ ፍላጎት በመነሳት መሆኑ ተገልጿል።

የኦማን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አልቡሳይዲ “መግባባት ላይ ለመድረስ ካለ ፍላጎት በመነሳት ጉባዔው ነገ [ሰኞ] በሳላህ ለማካሄድ ታቅዶ የነበረው ጉባዔ ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፏል” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።

“መረጋጋት እና በቀጣናውን ዘላቂ ትብብር የሚያመጣ ውይይት ለማካሄድ ቁርጠኞች ነን” ሲሉም በመግለጫቸው ላይ አስታውቀዋል።

አልቡሳይዲ በኤክስ ገጻቸው ላይ በለጠፉት መግለጫ ላይ በጉባዔው ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቀውን የባህሬን፣ ኢራን፣ ኢራቅ፣ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ፣ ኦማን፣ ኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ኩዌት ባንዲራዎችን አጋርተዋል።

ጉባዔው የሚካሄድበትን አዲሱን ቀን ያላስታወቁት የኦማኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለምን ወደ ሌላ ጊዜ እንደተላለፈም የሚገልጽ ማብራሪያ አልሰጡም።

ጉባዔው ወደ ሌላ ጊዜ የተላለፈው ባህሬን የቀጣናው ሚኒስትሮች ጉባዔ ላይ ኢራን በመካተቷ የተነሳ እንደማትሳተፍ ካስታወቀች በኋላ ነው።

የባህሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቅዳሜ ዕለት ከኢራን ጋር ያለን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሳይሻሻል አገሪቱ በምትሳተፍበት የትኛውም የሚኒስትሮች ጉባዔ ላይ አንገኝም ሲሉ አስታውቀዋል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ አርብ ዕለት ስምንት የባሕረ ሰላጤው አገራት ሚኒስትሮች የሚገኙበትን እና ኦማን የምታስተናግደውን ጉባኤ ቴህራን ማቀናጀቷን ተናግረው ነበር።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ፣ እሁድ ዕለት በለንደን ለሚገኘውና በአረብኛ ቋንቋ ለሚሰራጨው 'አል-አራቢ አል-ጃዲድ' የተባለ የዜናአውታር እንደተናገሩት፣ "የዚህ ስብሰባ ዋናው እና ብቸኛው አጀንዳ በሆርሙዝ ባህር ወሽመጥ ውስጥ የሚገኘው አዲሱ የባህር መስመር ነው" ብለዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም ኢራን እና ኦማን አዲሱን መስመር የሚወስን ስምምነት እንዲሁም ዝግጅቶቹን በዝርዝር የሚያሳዩ ካርታዎችን እና የጋራ መግለጫን አጠናቀዋል ብለዋል።

ከኦማን ጋር የተደረገው ስምምነት የሆርሙዝ ባህር ወሽመጥ እንደገና መከፈትን “በምንም መልኩ” እንደማያመለክት አጽንኦት ሰጥተዋል።

በኢራን ጦርነት በተደጋጋሚ ጥቃት ከደረሰባቸው አገራት መካከል ባህሬን አንዷ ናት።