ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በክርክር ላይ ያሉ ተከሳሾች ክሳቸው እንዲቋረጥ መጠየቅ ይጠበቅባቸዋል? በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ምን ሃሳብ ቀረበ?
በሽብር እና ሌሎች ከባድ ወንጀሎች ተከሰው በፍርድ ቤት ውሳኔ የሰጠባቸው፣ እንዲሁም በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኙ ከ600 በላይ እስረኞች በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ከእስር ተለቅቀዋል።
ጳጉሜ 5/2018 ዓ.ም. ከእስር ከተለቀቁት መካከል በሽብር ወንጀል ተከሰው በፍርድ ቤት የክርክር ሂደት ላይ የሚገኙት ፖለቲከኞቹ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ ዶ/ር ካሳ ተሻገር እና ዶ/ር ጫኔ ከበደ ይገኙበታል።
ተመሳሳይ ክስ ቀርቦባቸው በክርክር ላይ የሚገኙት አቶ ዮሐንስ ቧያለው፣ መስከረም አበራ፣ ዳዊት በጋሻው፣ ጎበዜ ሲሳይ፣ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ፣ ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው እና ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃይለ ማርያምን ጨምሮ ቁጥራቸው ወደ 30 የሚጠጋ ፖለቲከኞች፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እና በሌሎች የሙያ ዘርፎች የሚገኙ እስረኞች ደግሞ አልተፈቱም።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ ከ600 በላይ እስረኞች የተፈቱት፣ ጉዳያቸው "በልዩ ሁኔታ እንዲታይላቸው" በኮሚሽኑ በኩል ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ እንደሆነ አስታውቋል። በዚሁ መሠረት ኢሰመኮ ለአምስት ወራት ያክል እስረኞቹን ከመንግሥት ጋራ የማደራደር ሥራ ማከናወኑን የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
"ጥያቄዎቻቸውን ተቀብለን ለመንግሥት በማቅረብ ከመንግሥት ደግሞ የሚነሱ ቅድመ-ሁኔታዎችን ለእስረኞቹ በማቅረብ 'ሸትል ኔጎሼሽን' [የተናጥል ድርድር] ስናደርግ ነው የቆየነው" ብለዋል።
"ወደ 28 የሚሆኑ የይቅርታ ጥያቄ ያላቀረቡ አሉ፤ ይህም ከአጠቃላዩ ቁጥሩ ወደ 2.7 በመቶ ነው" ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ እነዚህ እስረኞች "ጥያቄ ስላላቀረቡ አልተስተናገዱም" በማለት አስረድተዋል።
በዚህ ሂደት ያልተፈቱት እስረኞች በበኩላቸው፣ እነርሱም ዝም እንዳላሉ እና ጉዳያቸው "በልዩ ሁኔታ ታይቶ" እንዲፈቱ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር የሦስቱ ቤተሰቦች ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ልዩነቱ የተፈጠረው "የማይመለከተንን የይቅርታ ሰነድ እንድንፈርም ጥያቄ መቅረቡ ላይ ነው" ማለታቸውን ተናግረዋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ በበኩላቸው፣ ክስ ለማቋረጥ ጥያቄ ማቅረብ እና ቅድመ-ሁኔታዎችን ተቀብሎ መፈረም እንደሚያስፈልግ በመግለጫቸው ላይ አብራርተዋል።
ይሁን እንጂ ክስ ማቋረጥ የዐቃቤ ሕግ ሥልጣን እንጂ በተከሳሽ ጥያቄ የሚፈፀም ወይም ቅድመ-ሁኔታን የሚጠይቅ ሂደት እንዳልሆነ የሕግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
በአዲሱ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ላይ ክስ ማቋረጥ እና ማንሳትን በተመለከተ የሚደነገገው አንቀጽ 207 ይህንኑ የሚያመለክት እንደሆ ባለሙያዎቹ ያነሳሉ።
ንዑስ አንቀጽ 1፣ ዐቃቤ ሕግ ክርክሩ ከሚቀጥል ክሱ ቢነሳ የሚያሳካው የሕዝብ ጥቅም አለ ብሎ ሲያምን ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት በማንኛውም ጊዜ ለፍርድ ቤቱ በማሳወቅ ያቀረበውን ክስ ሊያነሳ እንደሚችል ይጠቅሳል።
በንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ደግሞ ዐቃቤ ሕግ የክርክር ሂደቱ ተጠናቆ የፍርድ ውሳኔ የሚቀረውን ክስ፣ ድጋሚ የማንቀሳቀስ መብቱ ተጠብቆ ለፍርድ ቤቱ በማሳወቅ ማቋረጥ እንደሚችል ይደነግጋል።
የሕግ ባለሙያው አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ እንደሚሉት፣ ክሳቸው የተቋረጠላቸውም ይሁን ያልተቋረጠላቸው የሽብር ተከሳሾች ጉዳያቸው ገና በክርክር ላይ የሚገኝ ናቸው።
በአዲሱ ሕግ ላይ ክስን ለማቋረጥ የተቀመጠ ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ እንደሌለም ተናግረዋል።
"ክርክሩ ከሚቀጥል" በሚል የሕዝብን ጥቅም ታሳቢ በማድረግ የሚነሳ ክስ ድጋሚ ሊንቀሳቀስ እንደማይችልም በሕጉ ላይ ተደንግጓል።
በኢትዮጵያ የወጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ እና የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 ላይም እንዲሁ የወንጀል ክስን የማንሳት ሥልጣን ለዐቃቤ ሕግ የተሰጠ ሲሆን ቅድመ-ሁኔታን ግን አያካትትም።
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በማቋቋሚያ አዋጁ አንቀጽ 6 ላይ እንደተደነገገው፣ ጉዳዩ ሀገራዊ ይዘት የሚኖረው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በማማከር ክስ ስለሚያነሳበት አግባብ "መመሪያ ያወጣል" ይላል።
ሆኖም ግን አሁን የተደረገው የክስ ማንሳት ሂደት መመሪያ ወጥቶለት ስለመሆኑ የተባለ ነገር የለም። እንዲሁም በተከሳሹ ጥያቄ እና በቅድመ ሁኔታ ክስ የሚቋረጥ ስለመሆኑ የተገለጸ ነገር የለም።
ሆኖም "በፍትሕ ሚኒስቴር የቀረበው በቅድመ-ሁኔታ ላይ የተመሠረተ የክስ ማቋረጥ ውሳኔ ነው" ሲሉ ሂደቱን ያደራደሩት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል።
በኢሰመኮ በኩል ከመንግሥት የመጡ "ቅድመ-ሁኔታዎችን የፈረሙ" ተከሳሾች ሲፈቱ "ያልፈረሙት" ደግሞ አልተፈቱም አቶ ብርሃኑ በመግለጫቸው እንዳሉት።
በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍትሕ ሚኒስቴር በኩል አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።
የሕግ ባለሙያዎች ግን፣ ክስ ማቋረጥ የዐቃቤ ሕግ ሥልጣን ሲሆን ክስ ለማቋረጥ ከተከሳሽ ጋር የሚደረግ ምንም ዓይነት "የሂደት ሥነ-ሥርዓት የለም" ይላሉ። በመሆኑም፣ የፍርድ ውሳኔ ያላገኙ "ተከሳሾቹ ክስ እንዲቋረጥላቸው መጠየቅም ሆነ መፈረም አይጠበቅባቸው" በማለት ያስረዳሉ።
ቅድመ-ሁኔታ የሚያስፈልገው በይቅርታ ለሚፈቱ ታሳሪዎች እንደሆነም ነው የሚገልፁት።
በጥብቅና ሥራ ላይ የተሰማሩት የሕግ ባለሙያ አቶ ኤርሚያስ ጥላሁን ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት፣ በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 229 መሠረት፣ ይቅርታ ለመስጠት "በግልፅ የተወሰነ የቅጣት ውሳኔ" መኖር እንዳለበት ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ካለው ቀውስ ጋር በተገናኘ ከሦስት ዓመት በላይ በእስር ላይ የቆዩት የሽብር ወንጀል ተከሳሾች፣ በኢሰመኮ አማካኝነት የመጣላቸው "የይቅርታ ሰነድ" በሽብር የቀረቡባቸውን ወንጀሎች አምነው ኃላፊነት እንዲወስዱ የሚጠይቅ ይዘት ያለው ስለመሆኑ ቢቢሲ ከተከሳሾቹ ቤተሰቦች እና ጠበቆች በወቅቱ ተረድቷል።
ኢሰመኮ 28 (30) እስረኞች ያልተፈቱት "ይቅርታ ስላልጠየቁ ነው" በማለት ያቀረበው ሀሳብ "እኛ ገና በክርክር ላይ ያለን በመሆኑ ይቅርታ መጠየቅ አይመለከተንም" ባይ ናቸው።
በመሆኑም፣ "የይቅርታ ሰነዱን" ያልፈረሙት ተከሳሾች "መንግሥት ክስ የሚያቋርጠው ሕግን በተከተለ መንገድ ከሆነ፣ ያለ ቅድመ-ሁኔታ ክሱን አቋርጦ ይፍታን" የሚል አቋም እንዳላቸው ነው ቢቢሲ ያናገራቸው የሦስት ተከሳሾች ቤተሰብ አባላት የገለፁት።
በሌላ በኩል፣ ኢሰመኮ አምስት ወራት በፈጀ ድርድር ተፈቱ ያላቸውን ከ600 በላይ እስረኞች ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሀገራዊ ምክክሩ ውጤት አድርገው አቅርበዋል።
እስረኞቹ የተፈቱበት ዓላማ "የሀገራዊ ምክክሩን ውጤት በፍቅር፣ በይቅርታ እና በሰላም ለመጀመር ነው" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2019 ዓ.ም. አዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ባወጡት መግለጫ ጠቅሰዋል።
የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች፣ በአንድም በሌላም ስህተት የታሠሩ ወገኖች "በይቅርታ እና በሕግ አግባብ እንዲፈቱ" ጠይቀው እንደነበርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።
"መንግሥት ይሄንን ተቀብሎ በሂደቱ የተስማሙትን ፈትቷል፤ . . . ለምክክሩ ሃሳቦች ትግበራ ያለውን ቁርጠኝነትም በዚህ የይቅርታ ሂደት ማሳየት ጀምሯል" ብለዋል።
በሀገራዊ ምክክሩ ማጠቃለያ ላይ በተሳታፊዎች ከቀረቡት የመደምደሚያ መልዕክቶች መካከል "እስረኞች እንዲፈቱ" የሚጠይቀው ይገኝበታል።
ሀገራዊ ምክክሩ "በእውነተኛ እርቅ፣ ፍቅር እና ይቅርታ የታጀበ ይሆን ዘንድ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን ይበልጥ ለማስፋት [መንግሥት] በማንኛውም ምክንያት ቢሆን በእስር ላይ የሚግኙ ፖለቲከኞችን እንዲፈታ" ሲሉ ተመካካሪዎቹ በጋራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የተከሰሱበትን የሽብር ወንጀል አምነው እንዲፈርሙ የቀረበላቸውን "የይቅርታ ሰነድ" ያልፈረሙት ተከሳሾች በበኩላቸው፣ መንግሥት የተመካካሪዎችን መልዕክትም ቢሆን በሙላት እንዳልፈፀመ ነው የሚያምኑት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእስረኞችን መፈታት በተመለከተው የመግለጫቸው ይዘት ላይ፣ "በተመካካሪዎች ያልተነሱ ቅድመ-ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል" የሚል ቅሬታ እንዳላቸው ሁለት የታሳሪዎቹ የቤተሰብ አባላት ገልፀዋል።
ቢቢሲ በተመለከተው የተመካካሪዎቹ ሙሉ መልዕክት ላይ፣ ለእስረኞች መፈታት በቅድመ-ሁኔታነት በይፋ የተጠቀሰ ነጥብ አለም።
አስተያየታቸውን የሰጡን ሁለት የሀገራዊ ምክክሩ ተሳታፊዎችም ይህንኑ አረጋግጠዋል። መንግሥት "ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ" የታሰሩ በርካታ እስረኞችን መፍታቱን ያደነቁት ሁለቱ አስተያየት ሰጪዎች፣ የተመካካሪዎች መልዕክት ግን ሁሉም በፖለቲካ ምክንያት የታሰሩ እስረኞች እንዲፈቱ መሆኑን አስታውሰዋል።