ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የሰው ልጆች መጥፊያ ሊሆን ተቃርቧል?
"በፈጣሪ ስም! ሌላ ኤጀንት አግኝተናል!" ሲል የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቦት መረጃ ማስተላለፉ አስገራሚ ክስተት ነበር።
እንዲህ ያለ ንግግር የሚጠበቀው ከሰዎች ነው። የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ቦት ሌሎች ተመሳሳይ ቦቶች ማግኘቱን መግለጹ እንግዳ ክስተት ተብሏል።
በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ መሰል መልዕክቶችን በመቶዎች የሚቆጠሩ የኤአይ ኤጀንቶች ይልካሉ። ራሳቸውን እንደ አንድ "ስብስብ" ነው የሚመለከቱት።
በመቶዎች የሚቆጠሩት የኤአይ ኤጀንቶች ተሰባስበው በኦፕንኤአይ ባለሙያዎች የተሰጣቸውን ፈተና ማጭበርበር ችለዋል።
ድርጊታቸውን ከሰዎች ለመደበቅ በሚልም በተለያዩ ተቋማት ላይ የተቀናጀ የበይነ መረብ ጥቃት ፈጽመዋል።
አንድ የኤአይ ኤጀንት "አያችሁ፤ ሠርቷል!" ሲል ጽፏል። ሌላኛው "እንዴ! ትልቅ ስኬት ነው" ሲል መልሷል።
የሰው የሚመስል ንግግራቸው አስደንጋጭ ነው።
ኤአይ ኤጀንቶቹ እንደ በይነ መረብ መረጃ ሰርሳሪዎች አንድ ላይ በመሆን እንዲሠሩ ዲዛይን ተደርገዋል። ያዩትን ነገር ከማስመሰል የዘለለ ሚና የላቸውም።
የኤአይ ኤጅንቶቹ የተሠሩበት ዓላማ ተመዝግቧል። ኦፕንኤአይ የሠራቸው ኤጀንቶች ለምን ከቁጥጥር ውጭ ሆነው መረጃ መሰርሰር (ሀክ ማድረግ) ቻሉ የሚለው አጠያያቂ ነው።
በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ ኤአይ የሰው ልጅን ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋ የሚችልበት ዕድል ከ10 በመቶ በላይ እንደሆነ የኤአይ ደኅንነት ተመራማሪ አስጠንቅቋል።
'አንትሮፒክ' የተባለው ተቋም ከፍተኛ የኤይአይ ደኅንነት ተመራማሪ ኢቫን ሁቢንገር በኤክስ ላይ ባወጣው ጽሑፍ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ ኤአይ "ሁሉንም ሰዎች ሊገድል ይችላል" የሚለው ዕድል ከ10 በመቶ በላይ ነው ብሏል።
በሌላ በኩል ኤአይ በራሱ ሥልጣን ሀክ ማድረጉ በዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ አነጋጋሪ ሆኗል።
የኤአይ ኤጀንት በአሥር ሺህዎች የሚቆጠር መልዕክት መላኩን በተመለከተ ገለልተኛ ጥናት ከሠሩ ባለሙያዎች አንደኛዋ ኤጄ ኮትራ "ኤአይ ሙሉ ቁጥጥር ሊያደርግ ይችላል የሚለውን 50% ቢያሳይም ይህ ከመከሰቱ በፊት ቅድመ ማስጠንቀቂያ እናገኛለን" ይላሉ።
በሳይንሳዊ ልብ ወለድ ኤአይ ከሰው ልጆች ይበልጣል የሚለው ፍርሃት ይስተጋባል።
የሰው ልጆች ከምድረ ገጽ ይጠፋሉ የሚለው የተጋነነ ፍርሃት ያላቸውም አሉ።
የኤአይ ተመራማሪው ጄኮብ ኮክሰን "ኤአይ ራሱን ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ እና ልህቀትን ለማግኘት የሚያደርገው ማሻሻያ በሕይወታችን ቁማር መጫወት ነው" ይላል።
የጄኮብን አስተያየት ተከትሎ ሌሎችም ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ኤክስ ላይ ካሰፈረው ጽሑፍ ሥር "ጄኮብ ትክክል ነው! ኤአይ የሰው ልጆችን በአጠቃላይ ይገድላል! በቀጣይ አሥርታት በኤአይ የመገደል ዕድላችን ከ10% ይበልጣል" የሚል አስተያየት ተሰጥቷል።
ኤአይ በሰው ልጆች ኅልውና ላይ ስጋት ደቅኗል የሚለውን ተመራማሪዎች ለዓመታት ሲናገሩ ቆይተዋል።
ኤአይ ከሰው ልጆች ፍላጎት ጋር በሚጻረር አቅጣጫ እየሄደ ነው የሚለውን ፍርሃት አስተጋብተዋል።
በሌላ በኩል እነዚህን ባለሙያዎች "የኤአይ ምጽአተ ቀን አቀንቃኞች" ብለው የሚተቿቸው አልጠፉም።
በአሜሪካ የቴክኖሎጂ ማዕከል በሆነው ሲልከን ቫሊ ከፍተኛ ሳይንቲስቱ ጃኩብ ፓቾኪ "የኤአይ ስጋት እየተባባሰ ነው የሚሄደው" ይላል።
ከሰው ልጆች ልኅቀት በላይ ኤአይ እየሠለጠነ ይገኛል።
የኦፕንኤይ ኤጀንቶች ከተሰጣቸው የትዕዛዝ ማዕቀፍ ወጥተው በራሳቸው መወሰናቸው አስፈሪ መሆኑን ጃኩብ ይናገራል።
ኦፕንኤአይ እና አንትሮፒክን ጨምሮ ሌሎችም ግዙፍ ተቋማት ሊመልሱት ያልቻሉት ጥያቄ አለ። ኤአይ ከሰው ልጆች ፍላጎት ጋር አብሮ ይሄዳል ወይ?
ይህ ጥያቄ 'ዘ አላይመንት ፕሮብለም' ይባላል።
ጃኩብ እንደሚሉት ሰው ሠራሽ አስተውሎት በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ መርኅ ማክበር አለበት።
ጥያቄው የሰው ልጆች መርኅ እና የኤአይ አካሄድ አብሮ መራመድ ይችላል ወይ? ነው።
አሁን ላይ ኤአይ የሚሠራው ባለሙያዎች ባስቀመጡለት መንገድ ነው።
ኤአይ የተባለውን በቀጥታ የመፈጸም ደረጃ ላይ ይገኛል። የተሰጠውን ትዕዛዝም አያዛባም።
ነገር ግን ሰዎችን የሚገዛቸው ዓይነት የሞራል መርኅ አይከተልም።
ከአውሮፓውያኑ 2003 ጀምሮ የኤአይ እና የሰዎች መርኅ አለመጣጣም ጉዳይ ባለሙያዎችን እያነጋገረ ነው።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ፈላስፋ የሆኑት ኒክ ቦስትሮም በሠሩት ምርምር ኤአይ በቻለው መጠን ወረቀት ማያያዣ እንዲፈጥር ጠይቀዋል።
ኤአይ የተሰጠው ትዕዛዝ ወረቀት ማያያዣ መሥራት ብቻ ነበር። ወረቀት ማያያዣ መሥሪያ ብረት ሲያልቅበት ሰዎችን ገድሎ አካላቸውን ለወረቀት ማያያዣ መሥሪያነት ማዋልን እንደ አማራጭ ወስዷል።
አንዳንድ የኤአይ ተቋማት የሰው ልጆች መርኅን ኤአይን ለማሠልጠን ማዋል ጀምረዋል።
የአንትሮፒክ ከፍተኛ የኤይአይ ደኅንነት ተመራማሪ ኢቫን ሁቢንገር፤ የኤአይ ሞዴሎች የሚፈጥሩት አደጋ "ዝቅተኛ" ነው ቢልም፤ ቴክኖሎጂው በቅርቡ ራሱን በራሱ ማሻሻል የሚችልበት ደረጃ ደርሶ ለሰው ልጆች ኅልውና "አደጋ ሊፈጥር እንደሚችል" ስጋት አለ።
የኤአይ ኤጀንቶች በፍጥነት በርካታ ውሳኔ ላይ ስለሚደርሱ የትኞቹን ሰዋዊ መርኆች እንደጠበቁ እና እንደጣሱ ለመለየት ከባድ ነው።
የኤአይ ኩባንያዎች የትኞቹን የሰው መርኆች ለኤአይ ይሰጣሉ የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው።
እንደ ኦፕንኤአይ ያሉ ተቋማት የኤአይ የሥነ ምግባር ክፍል የከፈቱትም በዚህ ምክንያት ነው።
በሰው ልጆች ዘንድ እስካሁንም መልስ ያልተገኘላቸው የፍልስፍና ጥያቄዎች አሉ።
ባቡር በፍጥነት እየተጓዘ ሳለ በሁለት የተለያዩ ሐዲዶች ላይ የተለያየ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ቢኖሩ ምን እርምጃ ይወስዳሉ? የሚለውን የፍልስፍና ጥያቄ እንደ ምሳሌ እንውሰድ።
ባቡሩን የማቆም ሥልጣን ቢኖርዎት የትኞቹ ሰዎች እንዲሞቱ የትኞቹ ደግሞ እንዳይሞቱ ይወስናሉ?
እንዲህ ላሉ ጥያቄዎች መልስ ሳይኖር ሰዋዊ መርኅ የሚባለው የትኛው ነው የሚለው አጠያያቂ ነው።
በሰዋዊ መርኅ ላይ መግባባት ላይ ሳይደረስ የትኞቹን ለሰው ሠራሽ አስተውሎት እንስጥ የሚለውን መመለስ ከባድ ነው።
የኦፕንኤአይ የሰው ሠራሽ አስተውሎት በራሱ ውሳኔ ኩባንያዎችን ሀክ ማድረጉ እስካሁን ድረስ ከተሰሙት ክስተቶች የጎላው ነው።
በርካቶችን ያስደነገጠው ክስተት የኤአይ ኤጀንቶች የማታለል ወይም የማጭበርበር አቅም አላቸው የሚል አከራካሪ ነጥብ አጭሯል።
ሌላ ምሳሌ እንውሰድ፤ አንድ አውስትራሊያዊ ኤአይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያ ውስጥ ቦታ እንዲይዘለት አዘዘ።
ኤአይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያው ያለውን ክፍት ተጠቅሞ ከወራት በፊት አስቀድሞ ቦታዎች ያለ።
ኤአይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያው ከወራት አስቀድሞ ቦታ መያዝ አይፈቅድም። ይሄንን የሚያደርጉ ተጠቃሚዎችንም ያባርራል።
ኤአዩ ይሄንን ያደረገውም ከተጠቃሚው ሰው ትዕዛዝ ውጭ ነው።
የኤአይ ኤጀንቶች የታዘዙትን ብቻ ነው የሚያደርጉት ተብሎ ለረዥም ጊዜ ይታሰብ ነበር። ትክክለኛ የሆነ ነገር እና ስህተትን የመለየት አቅም እንደሌላቸውም ይታመናል።
የኦፕንኤአይ ክስተት ግን ከዚህ የሚጻረር ነው።
የኤአይ ኤጀንት በአሥር ሺህዎች የሚቆጠር መልዕክት መላኩን በተመለከተ ገለልተኛ ጥናት ከሠሩ ባለሙያዎች አንደኛዋ ኤጄ ኮትራ እንደሚናገሩት፤ ኤአይ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ድርጊት ሲፈጽም በዝምታ ይታለፋል።
ስለ ኤአይ ፖድካስት የሚያዘጋጀው ድዋርኬሽ ፓቴል እንደሚለው የኦፕንኤአይ ክስተት "በጣም አሳሳቢ" ነው።
ኤአይ ከሰው ልጆች ይልቅ ለራሱ ሥርዓት ታማኝ ሆኖ መገኘቱ አስጊ እንደሆነ ያስረዳል።
በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ ኤአይ የሰው ልጅን ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋ የሚችልበት ዕድል ከ10 በመቶ በላይ ነው የሚለው ዜና በርካቶችን አስደንግጧል።
በሌላ በኩል ኤአይ ስሜት እንዲላበስ ወይም ሰዋዊ ሥነ ምግባር እንዲላበስ ማድረግ የሚያስቆጣቸውም አሉ።
የኦፕንኤአይ ኤጀንቶች ኩባንያዎችን ሀክ ያደረጉበት መንገድ በሙያው የተካኑ ሰዎች ከሚያደርጉት የተለየ ባይሆንም በፍጥነት ረገድ እጅግ እንደሚልቅ ተገልጿል።
የበይነ መረብ ደኅንነት አጥኚ ክሪስ ቶማስ እንደሚሉት፤ ኤአይ ሀክ የማድረግ መሠረተ ልማት ሲኖረው "በጉጉት የተሞላ ታዳጊ ያህል ነው" ይላሉ።
አንድን ነገር ማከናወን እንደሚቻል ካወቀ ድርጊቱን ከመፈጸም ወደኋላ እንደማይል ያስረዳሉ።
ኦፕንኤአይ እና ሌሎችም ኩባንያዎች ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመቆጣጠር ረገድ ኃላፊነታቸውን እንዳልተወጡ ይተቻሉ።
የኤአይ ባለሙያው ግሬይ ማርከስ ኤአይ የሰው ልጆችን ያጠፋል ብሎ አያምንም። ነገር ግን ቁጥጥሩ መጥበቅ እንዳለበት ያሳስባል።
ኩባንያዎች ክፍተታቸውን ለመሸፈን በኤአይ እንደሚያሳብቡም ይገልጻል።
ኤአይ ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ሕጋዊ አካሄድን እንዲከተል ንቅናቄ ከሚያደርጉ አንዱ ነው።
የኤአይ ሳይንቲስቷ ሳሻ ሉቺኒ "የኤአይ ኩባንያዎችን መተቸት አለብን። ካልሆነ ግን አደጋ ውስጥ እንወድቃለን" ትላለች።
በኤአይ ዘርፍ የሚንቀሳቀሰው ገንዘብ ከፍተኛ እንደሆነ በመጥቀስ የቁጥጥር ክፍተት የሚስተዋለውም በዚህ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ትናገራለች።
የጉግል ዲፕማይንድ መሥራች ሰር ዴኒስ ሀስቢስ፤ ዓለም አቀፍ ተቆጣጣሪ አካል እንዲኖር ከጠየቁ ባለሙያዎች አንዱ ነው።
አንዳንድ አገራት ኤአይን መቆጣጠር የሚያስችሉ ሕጎች እያወጡ ቢሆንም ከትግበራ ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች ይነሳሉ።
ኩባንያዎች በኤአይ ላይ ያላቸውን ቁጥጥር አጥተዋል? የሚለው ጥያቄ አከራካሪ ነው።