ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ሕዋ ላይ የጦር መሣሪያ ማሰማራቷን ለመጀመሪያ ጊዜ አመነች
አሜሪካ ሕዋ ላይ የጦር መሣሪያ ማሰማራቷን ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ማረጋገጫ ሰጠች።
የአሜሪካ አየር ኃይል ጸሐፊ ትሮይ ሚኔክ፤ በምድር ዙርያ መሣሪያ ማሰማራት አሜሪካን ከጠላት ኃይሎች ለመከላከል አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የአየር፣ ሕዋ እና ሳይበር ጉባዔ ላይ ንግግር ያደረጉት ኃላፊው፤ እየተለወጡ ለመጡ የጥቃት ዓይነቶች ምላሽ ለመስጠት አገራቸው ዝግጁ መሆኗን ጠቅሰዋል።
የጦር መሣሪያው በምድር ዙርያ የትኛው አካባቢ ላይ እንደተቀመጠ እና ምን ዓይነት አቅም እንዳለው ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
ከዚህ በፊት ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ሕዋ ላይ ያለውን ወታደራዊ አቅም ለማጎልበት ዕቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
ሩሲያ እና ቻይና አሜሪካ ላይ ለወደፊት ጥቃት ለማድረስ እንዲመቻቸው ሳተላይቶቿን ዒላማ ለማድረግ እየሠሩ ነው ሲሉም ከስሰዋል።
አሜሪካን ከሚሳዔል እና ሌሎችም የአየር ጥቃቶች ለመከላከል 'ጎልደን ዶም' የተባለ የመከላከያ ሥርዓት ተዘርግቷል። የዚህ መከላከያ ሥርዓት አንድ አካል የሕዋ ወታደራዊ አቅምን ማጠናከር እንደሆነ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አስታውቋል።
የሕዋ ወታደራዊ አቅም ግንባታ ሚሳዔል መቃወሚያን ያካትታል።
በአውሮፓውያኑ 1967 የተፈረመ ስምምነት በሕዋ ላይ ጅምላ ጨራሽ መሣሪያ ማሰማራትን ያግዳል።
ከዚያ ወዲህ ኃያላኑ አገራት አሜሪካ፣ ሩሲያ እና ቻይና ከስምምነቱ ውጭ የሆኑ የመከላከያ አማራጮችን ይከተላሉ።
የተፎካካሪዎቻቸውን ሳተላይት ዒላማ ማድረግ አንዱ መንገድ ነው። ይህም ወታደራዊ ግንኙነት፣ ስለላ እና ጉዞን ያሰናክላል።
ትራምፕ አምና ባስተላለፉት ትዕዛዝ የአሜሪካ የሕዋ ኃይል ሚና መከላከል ብቻ ሳይሆን ጥቃት ማድረስም ነው ብለዋል።
በአውሮፓውያኑ 2019 የተመሠረተው የአሜሪካ የሕዋ ኃይል በአገሪቱ በ70 ዓመታት ውስጥ አዲሱ ወታደራዊ ክንፍ ነው።
ዓላማው በሕዋ ላይ የአሜሪካን ንብረቶች ማስጠበቅ እንደሆነ ተገልጿል። ይህም የግንኙነት እና ስለላ ሳተላይቶችን መከላከልን ያካትታል።
የአሜሪካ ሕዋ ኃይል ቃል አቀባይ "ሕዋ ላይ ለመወዳደር እና ቁጥጥር ለማድረግ ተልዕኮዎችን ይወጣል" ብለዋል።
"የጠላቶችን አቅም ለማምከን ተንቀሳቃሽ እና ቋሚ መንገዶች እንጠቀማለን። ይህም ማወክ፣ ማዳከም እና አስፈላጊ ከሆነ ማውደምን ይጨምራል" ሲሉም አክለዋል።
ቃል አቀባዩ አያይዘውም "ለመከላከል እና ለማጥቃት እናውለዋለን" ብለዋል።
ያለፈው ጥር ላይ ሁለት የሩሲያ ሳተላይቶች ቢያንስ በደርዘን የሚቆጠሩ የአውሮፓ ሳተላይቶችን መጥለፋቸው ተገልጿል።
ሳተላይቶችን በመጥለፍ ስሱ መረጃ ማግኘት፣ ማስተላለፍ እና ሌሎች ሳተላይቶችን መቆጣጠር ይቻላል።
በአውሮፓውያኑ 2024 አሜሪካ እና ሩሲያ ሌሎች ሳተላይቶችን ማጥቃት የሚችል ሳተላይት አሰማርተዋል።
ሩሲያ ስለ ጉዳዩ በይፋ አስተያየት አልሰጠችም።
የአሜሪካ ሕዋ ኃይል እንደሚለው ቻይና "በዘመናዊ የወታደራዊ አቅም ግንባታዋ ውስጥ የሕዋ መሣሪያ መቃወሚያዎችን" እየሠራች ነው።
በአንጻሩ ሩሲያ ሕዋን "የውጊያ አውድማ" አድርጋ እንደምትመለከት እና በሕዋ ላይ የበላይነት መያዝ ለወደፊት ግጭቶች "ቁልፍ" መሆኑን እንደምታምን አሜሪካ ገልጻለች።