ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ሐዘናችንን የበለጠ አክብዶታል" ልጆቻቸው በሳዑዲ በሞት ተቀጥተው መቅበር ያልቻሉ ወላጆች
"ይህን ሁሉ ሥርዓት ያከናወንነው ቤተሰቡ እንዲጽናና እና እርማችንን ለማውጣት ነበር፤ ግን መጽናናት አልቻልንም" ይላሉ በልጃቸው ክብሮም ሞት ልባቸው የተሰበረው አቶ ክንፈ አረጋዊ።
"ይህ ለእኔ የዕድሜ ልክ ሐዘን እና ጸጸት ነው።" ይላሉ።
ክብሮም ክንፈ አረጋዊ በዚህ ዓመት ሰኔ ወር ላይ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ካናቢስ በሕገ ወጥ መንገድ ሲያስገቡ ተይዘዋል በሚል በቁጥጥር ሥር ውለው የሞት ቅጣት ከተፈጸመባቸው አምስት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ነው።
በኢትዮጵያውያ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ሕይወቱን በማንኛውም መልኩ ላጣ ሰው መደበኛ የቀብር ሥነ ስርዓት ማከናወን የተለመደ ተግባር ነው።
የሟች አስከሬን በሬሳ ሣጥን ተደርጎ የሟች ቤተሰቦች እና የሃይማኖት አባቶች ሃይማኖታዊ ሥርዓትን ይፈጽሙለታል። ወዳጅ ዘመዶችም አስክሬኑን በመሰናበት እርማቸውን ያወጣሉ።
ነገር ግን የክብሮም አስክሬን ለቤተሰቦቹ ባለመሰጠቱ ለ25 ዓመቱ ሟች ይህ ሥርዓት ሊከናወን አልቻለም።
ሳዑዲ አረቢያ ከቻይና እና ኢራን ቀጥሎ በዓለም ላይ በቁጥጥር ሥር ያዋለቻቸውን ግለሰቦች በሞት ከሚቀጡ አገሮች መካከል አንዷ ነች።
የሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ እንደሚያሳየው ሳዑዲ አረቢያ እስከ ሐምሌ 20 ድረስ 116 ሰዎችን በሞት ቀጥታለች።
በአውሮፓ የሳውዲ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዱዋ ዳኢኒ "አስከሬን አለመስጠት የአስተዳደር ውሳኔ ብቻ አይደለም። ቅጣቱን ወደ ሟች ቤተሰቦች የሚያሻግር ጭምር ነው" ይላሉ ።
የተባበሩት መንግሥታት የሃይማኖትና የእምነት ነፃነት ራፖርተር ናዚላ ጋኒያ የሳዑዲ አረቢያ አስከሬንን ያለመስጠት እርምጃ "ማሰቃየትና ማዋረድ" ሲሉ ገልጸዋታል።
ዘመዶቻቸው እንደሚሉት ሰኔ 16 በደቡባዊ ሳዑዲ አረቢያ አሲር ግዛት በሚገኘው ካሚስ ሙሼይት የተገደሉት አምስት ኢትዮጵያውያን ስለግድያዎቹ ምንም ዓይነት ቅድመ ማስጠንቀቂያ አልተሰጣቸውም። የግል ንብረቶቻቸውን ወይም መሞታቸውን የሚገልጽ ማስረጃም አልደረሳቸውም።
ክብሮም ክንፈ አረጋዊ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሄደው እአአ በ2020 ከአባቱ ጋር ነበር። በወቅቱ አባት እና ልጅ በቁጥጥር ሥር ውለው ለ15 ወራት ከታሰሩ በኋለ ተባረሩ።
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት፣ ክብሮም ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመመለስ ወሰነ።
ቀይ ባሕርን በጀልባ አቋርጦ በየመን አድርጎ ወደ ሳዑዲ ገባ።
ክብሮም እአአ በ2023 የሳዑዲን ድንበር ሲያቋርጥ በአገሪቱ የጸጥታ አካላት እንደገና ተይዞ በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ክስ ተመስርቶበታል።
ክንፈ ልጃቸው ከሦስት ወራት እስር በኋላ የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት ለቢቢሲ ተናግረዋል። ከሦስት ዓመት እስር በኋላም በሰኔ ወር በድንገት የሞት ቅጣቱ ተፈጽሞበታል።
ክንፈ "ከእኛ ጋር የመነጋገር ዕድል እንኳን አላገኘም" ሲሉ እያለቀሱ ያስረዳሉ። "ስለሞቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ነው ያወቅኩት" በማለትም አክለዋል።
አቶ ክንፈ ልጃቸው ንፁህ እንደሆነ እና በሳዑዲ አረቢያ በስህተት እንደተፈረደበት ያምናሉ።
"ልጄ ሃሺሽ በማዘዋወር ውስጥ እንደተሳተፈ የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም" ሲሉም ተናግረዋል።
"የሞት የምስክር ወረቀቱን ወይም ንብረቱን ወይም አስከሬኑን ማንም አልሰጠኝም። ዝም ብዬ አለቅሳለሁ፤ በዝምታ እህህ እላለሁ። ሌላ ምን ማድረግ እችላለሁ?" ሲሉም ይጠይቃሉ።
በተመሳሳይ ወንጀል ተፈርዶበት በተመሳሳይ እስር ቤት ይገኝ የነበረው ጽጋቡ ገብረማርያም በዚያኑ ዕለት የሞት ቅጣት ተፈጽሞበታል።
ማዕከላዊ ትግራይ ውስጥ ከምትገኝ የገጠር ወረዳ የመጣው የ26 ዓመቱ ወጣት ከስምንት ልጆች መካከል የመጀመሪያ ልጅ ነው።
ድህነትን እና የእርስ በእርስ ጦርነትን በመሸሽ አካባቢውን ለቅቆ የወጣው የ18 ዓመት ልጅ ሳለ መሆኑን አባቱ ሀጎስ ገብረመስቀል ተናግረዋል።
"በአካባቢያችን ለወጣቶች ብዙ ሥራ የለም። እኔን ለመርዳት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሄዶ ነበር" ይላሉ አቶ ሀጎስ።
ጽጋቡ በአደንዛዥ ዕፅ ወንጀል ተከሶ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር በእስር ቤት አሳልፏል። ለመጨረሻ ጊዜ ከቤተሰቡ ጋር የተነጋገረው በየካቲት ወር ነበር።
"በቅርቡ እንደሚመጣና እንደሚያገባ አጫውቶን ነበር" ሲሉ አቶ ሀጎስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እናቱ ለተኪሮስ ገብረጻዲቅ፣ ለልጃቸው የምትሆነው ሚስት ፈልገው ለመዳር እየተዘጋጁ ሳለ በመገደሉ ቀብሩን ማዘጋጀታቸውን በሐዘን ስሜት ውስጥ ሆነው ይናገራሉ።
"ልጆቼ በሙሉ ሴቶች ናቸው፤ እሱ ብቸኛው ወንድ ልጄ ነበር። እህቶቹ ወንድማቸው በቅርቡ ወደ ቤቱ እንደሚመጣ ከፍተኛ ተስፋ ነበራቸው። በእሱ ሠርግ ላይ ለመዝፈን እየተዘጋጁ ነበር። አሁን ግን ልባቸው ከእኔ የባሰ ተሰብሯል" ሲሉ የተፈጠረባቸውን ስሜት ይናገራሉ።
የጽጋቡን መሞት ከሳዑዲ አረቢያ ከሚኖሩ ዘመዶቻቸው ከሰሙ በኋላ በአካባቢያቸው በሚገኘው ቤተ ክርስቲያን ፍትሃት እንዲፈጸም እና የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዲካሄድ ለማድረግ ወሰኑ።
ቤተሰቡ በባሕሉ መሠረት ለአርባ ቀናት ሐዘን የተቀመጡ ቢሆንም "አስከሬኑ ለቤተሰቡ ያልተሰጠበትን ምክንያት ማወቅ እፈልጋለሁ" ይላሉ ለተኪሮስ። "ይህ ካልሆነ ሐዘናችንን በጣም ያከብደዋል፤ ልባችንንም ይሰብራል።" ብለዋል።
የጽጋቡ ወላጆች የሳዑዲ ባለሥልጣናት የልጃቸውን ወንጀል የሚያሳይ ማስረጃ እንዲያቀርቡ እና ሌሎች መጠቀሚያ አድርገውት እንዳይሆን ሲሉ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው ዓመት ባወጣው ሪፖርት መሠረት ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ከተገደሉት መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት የውጭ ዜጎች ናቸው። ዳኢኒ ተጋላጭ የሆኑ ግለሰቦች በወንጀለኛ ቡድኖች ዒላማ እንደሚሆኑ ይናገራሉ።
"አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ድንበር ለማቋረጥ እንደሚረዷቸው በመግለጽ እቃዎችን እንዲይዙ እንደሚደርጉ ሪፖርት አድርገዋል፣ ፓኪስታናውያን ደግሞ የተከለከሉ ዕጾችን እንዲውጡ እንደሚገደዱ መዝግበናል፣ አንዳንድ ጊዜ በግዳጅ ወይም ሥራ እናስቀጥራችኋለን የሚል ማባበያ ይቀርብላቸዋል" ሲሉ ዳኢኒ ያስረዳሉ።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2015 ንጉሥ ሳልማን ቢን አብዱላዚዝ አል ሳዑድ ዙፋኑን ከተረከቡ በኋላ በሳዑዲ አረቢያ በሞት የተቀጡት ሰዎች ቁጥር ከ2,000 በልጧል፤ ከእነዚህም ውስጥ 42 በመቶ የሚሆኑት የውጭ ዜጎች ናቸው።
ድርጅቱ በ2025 ሳዑዲ አረቢያ 356 ሰዎችን በሞት መቅጣቷን አስታውቆ ይህም እስከዛሬ ከተመዘገበው ከፍተኛው ነው ብሏል።
የሳዑዲ ሕግ ባለሥልጣናት አስከሬኑን በኤምባሲው ወጪ ወደ አገራቸው እንዲወስዱ ይፈቅዳል፣ ዳኢኒ ግን ይህ ፈጽሞ እንደማይፈፀም ተናግረዋል።
"የሞት ቅጣት የተፈጸመበት የውጭ አገር ዜጋ አስከሬን ለቤተሰቡ የተሰጠበትን ጊዜ አናውቅም። የሳዑዲ ዜጎችን በተመለከተ በሰነድናቸው ጉዳዮችም ተመሳሳይ ነገር ይታያል" ሲሉ አብራርተዋል።
ቀደም ሲል አንዳንድ ቤተሰቦች የተገደሉ እስረኞች አስከሬን፣ የቱርክ እና የዮርዳኖስ ዜጎችን ጨምሮ፣ ወደ አገራቸው እንዲመለስ የሚጠይቅ ዘመቻ አካሂደዋል፤ ነገር ግን አልተሳካላቸውም ሲሉ ዳኢኒ አክለዋል።
"ለዮርዳኖሳውያን ቤተሰቦች የተሰጠው የሞት የምስክር ወረቀት በሚያስደንቅ ሁኔታ አጭር ነበር። አስከሬኑ የት እንደተቀበረ ወይም ስለሞቱበት ሁኔታ ምንም መረጃ አልያዘም" ሲሉም አብራርተዋል።
ቢቢሲ የሳዑዲ የአገር ውስጥና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን እንዲሁም በለንደን በሚገኘው ኤምባሲ በኩል ምላሽ እንዲሰጡ ቢጠይቅም አንዳቸውም ምላሽ አልሰጡም።
የሳዑዲ ባለሥልጣናት ስለ አደንዛዥ ዕፅ ወንጀሎችን በተመለከተ ጠንካራ አቋም ነው ያላቸው።
የሳዑዲ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር በሰኔ ወር ሃሺሽ ይዞ ተገኝቷል በሚል ተከስሶ የተፈረደበት የሳዑዲ ዜጋ መገደሉን ሲያሳውቅ ከቁርዓን ጥቅሶችን በመውሰድ "በምድር ላይ ሙስና የሚፈጽሙ" ሰዎች ላይ ከባድ ቅጣት እንደሚፈጸም አስታውቋል።
መግለጫው መንግሥት "የዜጎችን እና የነዋሪዎችን ደኅንነት ከአደንዛዥ ዕፅ ወረርሽኝ ለመጠበቅ እና በሕጉ መሠረት በአደገኛ ዕፅ ተጠቃሚዎች እና በአዘዋዋሪዎች ላይ ከባድ ቅጣት ለመጣል ቁርጠኛ ነው" ይላል።
በሳዑዲ አረቢያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ቢጠየቅም ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።
ሳዑዲ አረቢያ በአሁኑ ጊዜ ምን ያህል እስረኞች የሞት ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ እንደሆኑ ባታሳውቅም፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገምታሉ።
የሂዩማን ራይትስ ዎች የመካከለኛው ምሥራቅ እና የሰሜን አፍሪካ ክፍል ተመራማሪ የሆኑት ጆይ ሺአ "በሳዑዲ አረቢያ በድብቅ ወይም ያለ ማስጠንቀቂያ የሚፈጸሙ የሞት ፍርዶች የእስረኛውን እና የቤተሰብ አባላትን ለሞት ለመዘጋጀት የሚያስችል በቂ ጊዜ የማግኘት መብታቸውን ይጥሳሉ" ይላሉ ።
አንዳች ተዓምር እንዲመጣ መፀልይ
የሞት ፍርዳቸውን ለሚጠባበቁ እስረኞች ቅጣቱ መቼ እንደሚፈጸም አለማወቅ የበለጠ ፍርሃት እና ጭንቀት ይፈጥርባቸዋል።
ለደኅንነቱ ሲባል የሚገኝበት ቦታ እና ማንነቱን መግለጽ ያልቻለ አንድ እስረኛ ስለእስር ቤቱ ሁኔታ ለቢቢሲ ተናግሯል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2023 በቁጥጥር ስር ሲውል የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ውስጥ ተሳትፏል በሚል ክስ ተመስርቶበታል። ጥፋተኛ ሆኖ መገኘቱን እና የሞት እንደተፈረደበት ቢናገርም ይቅርታ እንደሚደረግለት ተስፋ ነበረው።
በዚህ ዓመት ግን 15 እስረኞች ሲገደሉ በማየቱ በፍርሃት ውስጥ እንደሚኖር ያስረዳል።
"ጥበቃዎቹ በሮቹን በከፈቱ ቁጥር የሚቀጥለው ተራ የማን እንደሚሆን እናስባለን።"
ተዓምር እንዲፈጠር እየጸለየ መሆኑን ቢናገርም የከፋ ነገር ከተከሰተ አስከሬኑ ወደ ቤቱ እንዲላክ ይፈልጋል።
"ወላጆቼ አስክሬኔን እንኳን ማየት እንደማይችሉ ሳስብ እጨነቃለሁ።"