የሁቲ ኃይሎች ሃኒሽ የተባሉትን ለአፍሪካ ቀንድ የቀረቡ ደሴቶችን መቆጣጠራቸው ተዘገበ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ይዞታቸውን እያሰፉ የመጡት የየመን ታጣቂ ኃይሎች ሁቲዎች ከአሥርት ዓመታት በፊት ኤርትራ እና የመን በይገባኛል የተዋጉባቸውን ሃኒሽ ደሴቶችን መቆጣጠራቸው ተዘገበ።

በደቡባዊ ቀይ ባሕር የሚገኙትን እነዚህ ቁልፍ ደሴቶች የሁቲ ኃይሎች ሰኞ ዕለት የያዙት በሳዑዲ የሚደገፈውን የየመን መንግሥት ኃይሎችን በማስወጣት መሆኑን አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ዘግቧል።

አሁን የሁቲ ታጣቂዎች በደቡባዊ ቀይ ባሕር ከኤርትራ እና ከጂቡቲ ጋር በሚዋሰነው ቦታ ላይ የሚገኙትን ሃኒሽ ደሴቶችን መቆጣጠራቸው በጂቡቲ የሚገኘውን የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል 32 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንዲቀርቡት አድርጓቸዋል።

ኤርትራ ነጻ አገር ከሆነች ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከ30 ዓመት በፊት በሃኒሽ ደሴቶች ላይ የይገባኛል ጥያቄ አንስታ ከየመን ጋር ጦርነት ውስጥ ገብታ እንደነበር ይታወሳል።

በደሴቶቹ የተነሳ በኤርትራ እና በየመን መካከል የተከሰተውን ለአጭር ጊዜ የቆየ ወታደራዊ ፍጥጫን ተከትሎ የኤርትራ ኃይሎች ለአጭር ጊዜ ትልቁን ሃኒሽ ደሴትን ተቆጣጥረው ነበር።

ነገር ግን ጉዳዩ ወደ ዓለም አቀፍ የዳኝነት ፍርድ ቤት ቀርቦ ዓሳ አስጋሪዎች ለማረፊያነት ከሚጠቀሙባው ውጪ ሰዎች ያልሰፈሩባቸው አብዛኞቹ የሃኒሽ ደሴቶች ክፍሎች በየመን ግዛትነት ውሳኔ አግኝተዋል።

ባለፈው ሳምንት በቀይ ባሕር ዳርቻ የሚገኙ ወደቦችን እና ደሴቶችን የተቆጣጠሩት የኢራን አጋር የሆኑት ሁቲዎች ከሆርሙዝ ወሽመጥ ቀጥሎ ወሳኝ በሆነው የባብ ኤል መንደብ ወሽመጥን ለመቆጣጠር የሚስችላቸውን ሞካ የተባለውን የወደብ ከተማን እና ፔሪም የተባለችውን ደሴት ተቆጣጥረዋል።

ግስጋሴያቸውን እያጠናከሩ የመጡት የሁቲ ኃይሎች በቀይ ባሕር ላይ ስትራቴጂካዊ አስፈላጊ መሆናቸው የሚነገርላቸው ትልቁ እና ትንሹ ሃኒሽ ደሴቶችን መቆጣጠራቸው በዓለም የባሕር ጭነት መጓጓዣ መስመር ውስጥ ቁልፍ በሆነው መተላለፊያ ላይ ያላቸውን ተጽእኖን የሚያጠናክር ነው።

የሁቲ ባለሥልጣናት ሰኞ ዕለት እንደተናገሩት ኃይሎቻቸው ሁለቱን ደሴቶች የተቆጣጠሩት በሳዑዲ አረቢያ የሚደገፉ የየመን መንግሥት ወታደሮች በባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ ዙሪያ በፍጥነት የተስፋፋውን የሁቲዎችን ግስጋሴ ለመመከት ጥረት እያደረጉ ባሉበት ጊዜ ነው።

ይህ ሁቲዎች የሃኒሽ ደሴቶችን የተቆጣጠሩበት ድል ባለፈው ሳምንት ሞካ ወደብን፣ ፔሪም ደሴትን እና ሌሎች የቀይ ባሕር ዳርቻ አካበቢዎችን ከተቆጣጠሩ በኋላ የተገኘ ሲሆን፣ በሳዑዲ መርከቦች እንዲሁም በዓለም የነዳጅ አቅርቦት እና ዋጋ ላይ ተጨማሪ ጫና ሊያሳድር ይችላል።

ባለፉት ሳምንታት በሳዑዲ የሚደገፈው ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው የየመን መንግሥት ኃይሎች ከሁቲዎች የገጠመውን ተደጋጋሚ ጥቃት ለመመከት ጥረት ቢያደርጉም፣ የአማጺያኑን ግስጋሴ ለመግታት አልቻሉም።

የመንግሥት ደጋፊ ኃይሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎች ከደሴቶቹ ከተፈቱ በኋላ፣ ሁቲዎች ከባብ ኤል መንደብ 160 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኙት የሃኒሽ ደሴቶች ላይ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የየመን መንግሥት አጋር ኃይሎች ደሴቶቹን ለቅቀው መውጣታቸውን ተከትሎ የሁቲ ተዋጊዎች ቦታውን መያዛቸውን ሁለት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የየመን መንግሥት እና አንድ የሁቲ ባለሥልጣናት አረጋግጠዋል።

የሁቲ ታጣቂዎች በቁልፍ የመንግሥት ይዞታዎች ላይ ጥቃት ከከፈቱበት ካለፈው ሳምንት ወዲህ በቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ የሚገኙትን ሞካ እና ዱባብ የተባሉ የወደብ ከተሞችን ተቆጣጥረዋል።

ይህም ሁቲዎች በጠላትነት ለፈረጇት ለሳዑዲ አረቢያ የዘይት ኤክስፖርት እጅግ ወሳኝ የሆነውን የባብ ኤል መንደብ ወሽመጥን ታጣቂዎቹ ለመቆጣጠር ያስችላቸዋል።

በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች፣ በሰሜናዊ የመን ሰፊ አካባቢዎችን የሚቆጣጠሩ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት በሳዑዲ አረቢያ በሚደገፉት የየመን መንግሥት ኃይሎች ላይ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍተው እየገሰገሱ ነው።