ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ "ከፍተኛ የአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን አይቀርም" የተባለ የድሮን ጥቃት ፈፀመች
ሩሲያ በዩክሬን እና በፖላንድ ድንበር አቅራቢያ በመንገደኞች ባቡር ላይ የድሮን ጥቃት ፈፀመች። የድሮን ጥቃቱ የተፈፀመው የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እና ከፍተኛ የአውሮፓ ኅብረት የደኅንነት ባለሥልጣናት በባቡር መስመሩ አልፈው ብዙ ሳይቆይ ነበር።
ቦሪስ ጆንሰን እና የዩኬውን ጆናታን ፖዌልን ጨምሮ ሌሎች የአውሮፓ ብሔራዊ የደኅንነት አማካሪዎች በኪየቭ ዓመታዊውን እና መሪዎች፣ የፖለቲካ፣ የቢዝነስ፣ የደኅንነት እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣናት የሚሳተፉበትን ስብሰባ ታድመው ሲመለሱ በሌላ ባቡር በተመሳሳይ የባቡር መንገድ ነበር ያለፉት።
በያሆዲይን የባቡር ጣቢያ በደረሰው በዚህ ጥቃት የባቡሩ ሞተር ከመጎዳቱ በስተቀር የደረሰ ጉዳት አለመኖሩ ተገልጿል። የዩክሬን ባለሥልጣናት እንዳሉት ጥቃቱ ሲፈፀም ሁሉም መንገደኞች ከባቡሩ ወጥተው ነበር።
ሩሲያ በምዕራባዊ ዩክሬን የሚገኝ የባቡር መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት መፈጸሟን ገልጻለች። የዩክሬን መንግሥት የባቡር መንገድ ኩባንያ የሆነው ዩክርዛሊዝንይትሲያ "የድሮን ጥቃቱ ዒላማ ዲፕሎማቶቹን ያሳፈረው ባቡር ሊሆን እንደሚችል" ገልጿል።
የድሮን ጥቃቱ በተፈፀመበት ወቅት በያሆዲይን ባቡር ጣቢያ በሌላ ባቡር ውስጥ ተሳፍረው የነበሩት የቀድሞው የሲአይኤ ኃላፊ ዴቪድ ፔትሮውስ ክስተቱ " አስደንጋጭ" ነበር ብለዋል።
ኩባንያው በሰጠው መግለጫ በተደጋጋሚ በሚደርስ የሩሲያ ጥቃት ዛቻ ምክንያት በተደረገ የሰዓት ለውጥ ምክንያት ባቡሩ ከጣቢያው የተነሳው ከሚጠበቀው ሰዓት ቀድሞ ነው ብሏል።
ጨምሮም ጥቃት በተፈፀመበት ባቡር መንገደኞች እንዲወጡ ትዕዛዝ የተሰጠው በሩሲያ ድሮን ጥቃቱ ከመፈፀሙ ከ15 ደቂቃ በፊት እንደሆነ ገልጿል።
በኪየቭ ስብሰባ የታደሙት የቀድሞው የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ካርል ቢልድት ለቢቢሲ እንደተናገሩት በተሳፈሩበት ባቡር ውስጥ የነበሩ መንገደኞች ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ ከመፈቀዱ በፊት ለመውጣት እንዲዘጋጁ ተነግሯቸው ነበር።
"ባቡሩ ውስጥ ነበርኩ። ባቡሩ ከቆመ በኋላ ለመውጣት እንድንዘጋጅ ተነገረን። ከተወሰነ ደቂቃ በኋላ ሁሉም ሰላም እንደሆነ እና ጉዟችንን እንድንቀጥል ተነገረን" ብለዋል።
ባቡሩ በፖላንድ ድንበር በሚገኘው ዶሮሁስክ ጣቢያ በሰላም ደርሷል።
የዩክሬን እና የፖላንድ ባለሥልጣናት እንዳሉት የሩሲያ ድሮን ጥቃት የተፈፀመው ከፖላንድ ድንበር 2 ኪሎ ሜትር ዘልቆ በገባ ሥፍራ ነው።
ጥቃቱን ተከትሎ የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሲይቢሃ፣ በዩክሬን እና ፖላንድ ድንበር የተፈፀመው " አረመኔያዊ ጥቃት " [ የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን] ሽብር የአውሮፓ ኅብረት እና ኔቶ ደጅ እንዳንኳኳ ይቆጠራል" ሲሉ ይህም በሞስኮ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የሚያደርግ እንደሆነ ገልጸዋል።
የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ አሁን የተፈፀመውን ክስተት ላይ ለመነጋገር አስቸኳይ ስብሰባ አካሂደዋል።
"በሩሲያ በኩል የሚፈፀመው ድርጊት መባባሱ ግልጽ እየሆነ ነው። ወደ ድንበራችን እየቀረቡ ነው" ብለዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ባቡሮች፣ የባቡር መስመር፣ የነዳጅ ማከማቻዎች እና ድንበር ቦታዎች ላይ የምትፈፅመውን ጥቃት አባብሳ የቀጠለች ይመስላል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በዩክሬን እና ሞልዶቫ ድንበር መካከል በፈፀመችው የድሮን ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን የዩክሬኑ ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ሳምንት በደቡባዊ ዩክሬን በመንገደኞች ባቡር ላይ በተፈፀመ ጥቃት አንድ ሴት ረዳት ተገድላለች።
የሩሲያ ጥቃቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዩክሬናውያን ዋና የመጓጓዣ መንገድ የሆነው የባቡር መሠረተ ልማት በእጅጉ ጎድተዋል። ሩሲያ እአአ በ2022 ሙሉ በሙሉ ወረራ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ሁሉም የአየር ጉዞዎች ታግደዋል።
የአውሮፓ አገራትም በግዛታቸው ላይ ለተከሰቱ ክስተቶች ሩሲያን ተጠያቂ እያደረጉ ነው።
ባለፈው ሳምንት ጀርመን በነሐሴ ወር በሌፕዚግ አየር ማረፊያ ላይ ለደረሰው የድሮን ጥቃት ሩሲያ ተጠያቂ እንደሆነች ገልጻለች። ሞስኮ ግን ክሱን አጣጥለዋለች።
ከጣሊያን እስከ ኢስቶኒያ ድረስ በመከላከያ ተቋማት ላይ በርካታ የእሳት አደጋዎች የተከሰቱ ሲሆን አንዳንድ አገራት ሩሲያን ተጠያቂ አድርገዋል።