ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለቀድሞ ፍቅረኛው ያበረከታቸውን ስጦታዎች በገንዘብ አስልቶ እንዲመለስለት ክስ ያቀረበው ግለሰብ ጥያቄው ውድቅ ሆነ
አንድ ሲንጋፖራዊ ለቀድሞ ፍቅረኛው ለስጦታ እና ለተለያዩ ነገሮች ያወጣውን በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ዶላር ከተለያዩ በኋላ ለማስመለስ ያቀረበው ክስ በፍርድ ቤት ውድቅ ተደረገበት።
ቻንደር አጋርዋል የቀድሞ ፍቅረኛው ፌሊሺያ ሊ አብረው በነበሩ ጊዜ ያወጣውን 468,000 የሲንጋፖር ዶላር ወይም ወደ 370 ሺህ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለማስመለስ በፍርድ ቤት ክስ መሥርቶ ሲከራከር ቆይቶ ነበር።
ነገር ግን ጉዳዩን የተመለከተው የሲንጋፖር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከሳሽ ገንዘቡን ለቀድሞ ፍቅረኛው ያወጣው ወዶ ፈቅዶ በመሆኑ እንድትመልስለት ፍቅረኛውን እንደማያስገድድ ወስኗል።
የፍርድ ቤቱ ዳኛ ሊ ሴዩ ኪን እንደገለጹት፣ አጋርዋል ከሊ ጋር ፍቅር ከመጀመሩ በፊትም ቢሆን ውድ ስጦታዎችን በተደጋጋሚ ይሰጣት ነበር፣ እናም ገንዘቡ እንድትመልስለት እንደማይጠብቅ ያረጋግጥላት ነበር።
አጋርዋል የአንድ የትራንስፖርት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲሆን፣ ቀድሞ ፍቅረኛው ፌሊሺያ ሊ ደግሞ የአውሮፕላን አስተናጋጅ ነበረች። ሁለቱ በአውሮፓውኑ 2019 በአንድ በረራ ላይ ተዋውቀው፣ ከአንድ ዓመት በላይ በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ነበሩ።
አጋርዋል ሊ ከሌላ ወንድ ጋር ግንኙነት እንዳላት ከጠረጠረ በኋላ በመለያየተቸው በፍቅር ጊዜ ለፍቅረኛው ያወጣውን ገንዘብ በማስላት እንድትመልስለት ክስ መሥርቷል። እንዲሁም ሊ በግንኙነታቸው ወቅት "ወለድ የሌላቸው ብድሮችን" በተደጋጋሚ ጠይቃው እንደነበር ተከራክሯል።
እነዚህም በአስር ሺህዎች የሚቆጠር ዶላር የክሬዲት ካርድ ወጪዎች፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለውጭ ጉዞዎች፣ ቤቷን ለማስዋብ እና ለሕይወት ኢንሹራንስ ክፍያዋ ገንዘብ ማውጣቱን ጨምሮ ሌሎችም ያወጣቸው ወጪዎችን እንድትመልስለት ጠይቋል።
ሊ በበኩሏ የቀድሞ ፍቅረኛዋ እንዲመለሱለት የዘረዘራቸው ውጪዎች "በፍቅር እና በአክብሮት የተበረከቱ ስጦታዎች ናቸው እንጂ ብድር አይደሉም" ስትል ተከራክራለች።
ዳኛዋም ከሊ ጋር በመስማማት፣ አጋርዋል ያቀረበው ክስ እና ክርክር በሰነድ ማስረጃ ያልተደገፈ እጅግ ደካማ መሆኑን ጠቁመዋል። ለምሳሌ፣ ሊ እነዚያን ብድሮች እንደወሰደች የሚያሳይ ማረጋገጫ ማቅረብ አልቻለም ብለዋል።
"ለፍርድ ቤቱ የቀረበው ማስረጃ በሙሉ ከሳሽ በተከሳሽ ተማርኮ በግንኙነታቸው ወቅት ውድ ስጦታዎችን ሲያበረክትላት እንደነበር ብቻ ያሳያል" ብለዋል ዳኛው።
"ነገር ግን ግንኙነቱ በመጥፎ ሁኔታ ሲቋጭ፣ አጋርዋል በቂም ተነሰስቶ የቀድሞ ፍቅረኛውን ከፍተኛ ዋጋ ለማስከፈል ክስ መሥርቷል" ሲሉ ዳኛዋ ክሱን ውድቅ አድርገውታል።
ዳኛዋ በተጨማሪም አጋርዋል "ብዙ ገንዘብ ያለው እና ውድ ነገሮችን የሚወድ ሰው" መሆኑን፣ ሊ ደግሞ "ከዚያ ደረጃ የራቀች" መሆኗን መገንዘባቸውን ገልጸዋል።
ሁለቱ የቀድሞ ፍቅረኞች ባደረጓቸው በርካታ የጽሑፍ መልዕክት ልውውጦች ውስጥ ሊ አጋርዋል ውድ ስጦታዎችን ሲያቀርብላት መደነቋን፣ አንዳንድ ጊዜም ለመቀበል ማመንታቷን ገልጻ እንደነበር ዳኛው ጠቅሰዋል።
እንዲህ ዓይነቱ ክስ በሴንጋፖር ውስጥ የመጀመሪያ አይደለም። ከሦስት ዓመት በፊት ሌላ ግለሰብ የፍቅር ጥያቄውን ውድቅ ያደረገችበት ሴት ከ3 ሚሊዮን የሲንጋፖር ዶላር በላይ የሚገመት ካሳ እንድትከፍለው በመጠየቅ ሁለት ክሶችን አቅርቦ ነበር።
ኬ. ካውሺጋን የተባለው ግለሰብ፣ ኖራ ታን ለተባለች ሴት ያቀረበውን የፍቅር ጥያቄ ባለመቀበሏ "የሥነ ልቦና ጉዳት እንደደረሰበት እና መልካም ስሙ እንደተበላሸ" ተከራክሮ ነበር።
ጉዳዩን የተመለከተው የአገሪቱ ፍርድ ቤት ግን ክሶቹን ውድቅ አድርጎታል። በኋላም ሴቷ ተከሳሽ ታን በከሳሿ ካውሺጋን ላይ ተቃዋሚ ክስ በማቅረብ፣ ከተከሰሰችበት ክስ ራሷን ለመከላከል ያወጣችውን ወጪ እንዲከፍል ጠይቃለች።