ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በየመን በሚካሄደው ውጊያ ምክንያት በ24 ሰዓት ውስጥ 1,400 ሰዎች ጂቡቲ ገቡ
በየመን ውስጥ እየተስፋፋ ያለውን ውጊያ በመሸሽ በርካታ ሰዎች ቀይ ባሕርን በመሻገር ወደ ጂቡቲ መግባታቸውን የአገሪቱ ኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ሚኒስትር አስታወቁ።
በየመን መንግሥት ኃይሎች እና በኢራን በሚደገፉት የሁቲ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ባለው ውጊያ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 1,400 ያህል ሰዎች ከየመን ወደ ጅቡቲ መሰደዳቸውን ሚኒስትሩ ኢሊያስ ሙሳ ዳዋሌ ገልጸዋል።
የሁቲ ታጣቂዎች ባለፉት ቀናት በቀይ ባሕር ዳርቻ ያሉ የየመን ግዛቶችን እየተቆጣጠሩ ባሉበት ወቅት ጦርነቱ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ወደሚገኙ አካባቢዎች እየተስፋፋ ነው።
የጂቡቲ ኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ሚኒስትር ኢሊያስ ሙሳ ዳዋሌ በኤክስ የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ እንደጻፉት፣ ጦርነቱን የሸሹት 1,400 ሰዎች የባብ ኤል መንደብ ወሽመጥን በማቋረጥ ነው ወደ ጂቡቲ የገቡት።
የመንግሥታቱ ድርጅት የስደት ድርጅት (አይኦኤም) የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ሳፊያ ኢብራሂም ለፈረናሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንደገለጹት፣ ወደ ጂቡቲዋ ኦቦክ የባሕር ዳርቻ ከደረሱት ሰዎች መካከል ሴቶች እና ሕጻናትም ይገኙባቸዋል።
በሁቲ ታጣቂዎች እና በየመን መንግሥት ኃይሎች መካከል የሚደረገው ውጊያ እየቀጠለ ባለበት በአሁኑ ጊዜ በቀጣይ ቀናት ተጨማሪ ሰዎች ወደ ጂቡቲ ሊመጡ እንደሚችሉ የአይኦኤም ባልደረባ ተናግረዋል።
በተባበሩት መንግስታት መረጃ መሠረት፣ እየተባባሰ በመጣው ውጊያ ከሐምሌ ወር ጀምሮ ቢያንስ 76,000 ሰዎች በየመን ውስጥ ተፈናቅለዋል። በተለይም በባለፈው ሳምንት ውጊያው እንደገና ከተቀሰቀሰ በኋላ የተፈናቃዮች ቁጥር አራት እጥፍ ጨምሯል።
ሁቲዎች ባለፈው ሳምንት በሳዑዲ አረቢያ በሚደገፉት የየመን መንግሥት ኃይሎች ላይ አዲስ ጥቃት ከፍተው በባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ ዙሪያ ያሉ አካባቢዎችን ዒላማ አድርገዋል።
በቅርብ ቀናትም በባሕር ዳርቻው አካባቢ ወደፊት በመገስገስ ሐሙስ ዕለት ሞካ የተባለችውን የወደብ ከተማን ተቆጣጥረዋል።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በሁቲዎች እና በየመን መንግሥት ኃይሎች መካከል በተካሄዱ ውጊያዎች ከሁለቱም ወገኖች በመቶዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎች መገደላቸው ተዘግቧል።
ከዚያ በኋላ ሁቲዎች በቀይ ባሕር ያሉ የየመን የባሕር ዳርቻዎችን እና ደሴቶችን በመቆጣጠር፣ ዓርብ ዕለት ደግሞ የዓለም ንግድ መርከቦች ወደ ቀይ ባሕር እና ወደ ሱዌዝ ቦይ ለመድረስ የሚጠቀሙበትን ወሳኝ የባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ ላይ የምትገኘውን ደሴት በመያዝ በአካባቢው ላይ ያላቸውን ቁጥጥር አስፍተዋል።
ኢራን የሆርሙዝን ወሽመጥን ከዘጋች በኋላ፣ በተለይ ሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ምርቷ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የባብ ኤል መንደብ መተላለፊያን ዋነኛዋ የመርከቦቿ የጉዞ መስመር አድርጋ እየተጠቀመችበት ነበር።
ነገር ግን ሁቲዎች በቀይ ባሕር ዳርቻዎች ላይ ያላቸውን ይዞታ እያሰፉ በመጡባቸው ባለፉት ወራት ተቀናቃኛቸውን የየመን መንግሥትን የምትረዳው ሳዑዲ አረቢያን ዒላማ በማድረግ በቀይ ባሕር በኩል መርከቦቿ እንዳያልፉ አግደዋል።