ናይጄሪያ በደቡብ አፍሪካ ንብረታቸውን ጥለው ለሸሹ ዜጎቿ ካሳ ልትጠይቅ ነው

እቃቸውን የጫኑ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ባለፉት ሳምንታት ፀረ ስደተኛ ተቃውሞዎችን በመፍራት በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካዊያን ስደተኞች ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው ወጥተዋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ናይጄሪያ በቅርብ ወራት በተደረጉ ተቃውሞች ምክንያት ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው ለተመለሱ ዜጎቿ ካሳ ልትጠይቅ መሆኑን አስታውቃለች።

የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኪሚቢ ኢሞሞቲሚ ኢቢንፋ ለቢቢሲ ጉዳዩ "በከፍተኛ ደረጃ" በሁለቱ አገራት መንግሥታት መካከል ንግግር ይደረግበታል ብለዋል።

በደቡብ አፍሪካ የናይጄሪያ ተወካይ ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት አሌክሳንደር አጃይ ባለፈው ማክሰኞ ናይጄሪያዊያን ጥለዋቸው የወጡ ንግዶች እና ንብረቶችን መንግሥት መመዝገብ መጀመሩን ተናግረዋል።

ከደቡብ አፍሪካ እስኪወጣ ድረስ እየተጠባበቀ ያለ አንድ ናይጄሪያዊ ለቢቢሲ ለአስር ዓመት ገደማ በደቡብ አፍሪካ መኖሩን እና ለደኅንነቱ ስጋት ስላደረበት ንግዱን እና ቤቱን ጥሎ መውጣቱን ተናግሯል።

የ32 ዓመቱ ኦጎዲሮ ኢርጆር ዊልሰን "በፍርሃት ምክንያት ሁሉንም ነገር" እያጣ መሆኑን ገልጿል።

"ልብሴን ጨምሮ ሁሉንም ነገር ቤቴ ጥዬ ነው የወጣሁት።"

የ32 ዓመቱ ናይጄሪያዊ ከደቡብ አፍሪካ መንግሥታቸው እንዲያስወጣቸው እየተጠባበቁ ካሉ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዜጎች ውስጥ አንዱ ነው። ባለፉት ሳምንታት ከ600 የሚበልጡ ናይጄሪያዊያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት ወደ አገራቸው የተመለሱት ስደተኞች ሕገ ወጦች እንደሆኑ የሚናገሩ ሲሆን፤ ይህ ግን በናይጄሪያዊያን ውድቅ ተደርጓል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

መንግሥት ሕገ ወጥ ስደተኝነትን ለመከላከል እርምጃ እየወሰደ አይደለም በሚሉ ቡድኖች በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ባለፉት ሳምንታት 25 ሺህ የሚሆኑ አፍሪካዊያን ስደተኞች ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው ወጥተዋል።

አንዳንድ የፀረ ስደተኛ ቡድኖች ሰነድ አልባ የሆኑ ስደተኞች ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው እንዲወጡ እስከ ሰኔ 23/2018 ዓ.ም. ድረስ ቀነ ገደብ ሰጥተው ነበር።

ቡድኖቹ ማክሰኞ ዕለት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉበት የተቃውሞ ሰልፍም አካሂደዋል። ሰልፎቹ በአብዛኛው ሰላማዊ የነበሩ ቢሆንም የውጭ አገር ዜጎች ላይ የተፈፀሙ አንዳንድ ክስተቶች ግን ነበሩ።

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በአብዛኛው ስደተኞች ላይ በተፈፀሙ ወንጀሎች እና ዝርፊያዎች 900 የሚሆኑ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።

ቢቢሲ በናይጄሪያ የካሳ ጥያቄ ዙሪያ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት አስተያየት እንዲሰጥ ጠይቋል።

የናይጄሪያ ተወካይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው የወጡትን ዜጎች በሙሉ እንደ ንግድ፣ ተሽከርካሪ፣ የሚንቀሳቀሱ እና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በትክክል እንዲመዘግቡ መጠየቃቸውን ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢቢንፋ ለቢቢሲ መደበኛ ጥያቄ ከመቅረቡ በፊት በካሳው እውነተኛነት ማረጋገጫ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

"ከደቡብ አፍሪካ ጋር ግንኙነት አላቋረጥንም፤ በከፍተኛ ደረጃ አሁንም እያነጋገርናቸው ነው። የተለመዱ ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን ተጠቅመን ዝርዝሩን እንፈታዋለን" ብለዋል።

ናይጄሪያዊው ዊልሰን በደቡብ አፍሪካ በልብስ ንግድ ላይ ለበርካታ ዓመታት ተሰማርቶ እንደነበር ተናግሯል።

ይሁን እንጂ አሁን ሱቁን ዘግቶ በፕሪቶሪያ የናይጄሪያ ከፍተኛ ኮሚሽን አቅራቢያ ለመጠለል ተገዷል።

በቀጣዩ በረራ ከደቡብ አፍሪካ ለመውጣት ተራው የደረሰው ዊልሰን በሱቁ ጥሎት የወጣው ንብረት 16 ሺህ ራንድ (975 ዶላር) እንደሚያወጣ ተናግሯል።

ዊልሰን የመኖሪያ ፈቃዱ በ2021 ዘመኑ እንዳበቃ እና ለማደስ እንዳልቻለም ገልጿል።

ካሳ የማግኘት ተስፋ እንደሌለውም ተናግሯል።

"የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ካሳ መክፈል ከቻለ በጣም ጥሩ ይሆናል። ነገር ግን ይህ እንደማይሆን አውቃለሁ" ብሏል።