በድምጻውያን ጉሮሮ ላይ የቆመው ኤአይ የኢትዮጵያን ሙዚቃ መልክ እንዴት ሊለውጠው ይችላል?

በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ተገርበው በአዲስ መልክ የተሠሩ ሙዚቃዎች የዩቲዩብ ገፆችን ወርረዋል።
የአንጋፋ እና ተወዳጅ ድምጻውያን የሙዚቃ ሥራዎች አማርኛው በተኮላተፈ የኤአይ አንደበት እየተዘፈኑ ነው።
አንዳንዶቹ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዕይታዎች አሏቸው። የአድማጭን ትኩረት የሳቡም ይመስላሉ።
ፀሐዬ ዮሐንስ ሥራዎቹ በኤአይ መልሰው ከተቀናበሩ አንጋፋ ድምጻውያን መካከል አንዱ ነው።
ፀሐዬ እነዚህን ሥራዎቹን ሰዎች አጋርተውት ነበር ለመስማት የሞከረው።
"ስሰማው ቶሎ ነው የሰለቸኝ፤ አልጨረስኩትም" ይላል።
ሙዚቃ ስሜት ነው የሚለው ፀሐዬ፣ "ከትክክለኛው ሙዚቃ ምን አጥተው ነው እንደዚህ የሚሠሩት?" ሲልም ይጠይቃል።
በኮምፒዩተር ተጠንቶ የተሠራ የኤአይ ሙዚቃ ለወረት ይሠራ እንደሆነ እንጂ ዘላቂ ይሆናል የሚል ሃሳብም የለውም።
ሌሎች ባለሙያዎች ደግሞ "ኤአይ በተለይ አዳዲስ የሙዚቃ ሥራዎችን ለመሥራት በሃሳብም ሆነ በቴክኒክ ጥሩ አጋዥ ነው" ሲሉ በበጎ ተመልክተውታል።
ለመሆኑ የዘመኑ የቴክኖሎጂ ልህቀት በተለይ በሙዚቃው ዘርፍ ምን ያሳጣ፣ ምን ያስገኝ ይሆን?
የኢትዮጵያን ሙዚቃስ በምን መልኩ ሊለውጠው ይችላል?
![ሙዚቀኛ ብሌን ዮሴፍ፣ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር የሮያሊቲ አስተዳዳር ኃላፊና ድምጻዊ ኃይሉ ሩትስ እና ድምጻዊ ፀሐዬ ዮሐንስ [ ከቀኝ ወደ ግራ]](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/640/cpsprodpb/7748/live/691bb430-5b84-11f1-8b8c-6d33e1d5abb6.jpg.webp)
የፎቶው ባለመብት, Blen Yosef/ Haile Roots/ Tsehaye Yohannes FB
ዋና መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው እሁድ ኤአይ መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ አቤኔዘር ጌታቸው "ይህ የቴክኖሎጂ ክስተት ለሙዚቃ ዲሞክራሲን ያመጣ ነው" ይላል።
ኤአይ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ እና የገንዘብ አቅም ላላቸው ምዕራባውያን እና ብዙ የሚነገር ታሪክ እና ባህል እያላቸው ለመሥራት አቅሙ ለሌላቸው አፍሪካውያን እኩል ዕድልን እንደሰጠም ያምናል።
ይህም በአቅም ችግር ምክንያት ከሙዚቃው የራቁ ባለሙያዎችን ሊስብ እንደሚችል ያክላል።
ሙዚቀኛዋ ብሌን ዮሴፍም ቴክኖሎጂው የራሱ የሆነ ጥቅም እና ጉዳት እንዳለው ጠቅሳ አዳሰስ ሥራዎችን ለመሥራት እንደ አጋዥ መጠቀሙ የባለሙያውን ጊዜ ለመቆጠብና ፈጠራን ለማገዝ እንደሚረዳ ታስረዳለች።
ኤአይ በተለይ በሙዚቃው ዘርፍ የሰዎችን የአዕምሮ ንብረት ባለቤትነት መብትን ለመንጠቅ መሣሪያ በመሆን በይበልጥ ይኮነናል።
ሁለቱም ባለሙያዎች በዚህ ይስማማሉ። ይህ ግን ቴክኖሎጂው በመፈልሰፉ ሳይሆን ያለ አግባብ ጥቅም ላይ በመዋሉ የመጣ ችግር እንደሆነ ይገልጻሉ።
ብሌን "በሕይወት ያሉም ሆነ የሌሉ ድምጻውያን የሌላቸውን ተፈጥሮ በማላበስ እና አዲስ ማንነት በመፍጠር ያለፈቃድ የሰዎችን ማንነት እየነጠቀ ነው" ትላለች።
"ባለቤት አልባ የኤአይ ሙዚቃዎች እየጎረፉ ነው" የምትለው ብሌን፣ ይህን መቆጣጠር አለመቻሉ አሳዛኝ እንደሆነ ትናገራለች።
የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ሲነሳ ስሙ በግንባር ቀደምትነት የሚነሳው አለማየሁ እሸቴ ባለቤት ወ/ሮ አየሁ ከበደም የባለቤታቸው ሥራዎች በኤአይ ተሠርተው መስማታቸው ካሳዘናቸው መካከል ይገኙበታል።
"በማን አለብኝት ታዛቢ የሌለው አስመስለው ሙዚቃውን እየተጫወቱበት ነው ያለው። ለማን አቤት ይባላል?" ሲሉም ይጠይቃሉ።
"ፈቃድ እንኳን ሳይጠይቁ አስመስለው ይሠራሉ። እኛም ወዴት ሄደን እናመልክት፣ ኮፒራይት ይከበር ተባለ ግን ውጤቱን አናውቀውም" ይላሉ በምሬት።
ኤአይ አዲስ የቴክኖሎጂ ክስተት እንደመሆኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገራት የባለቤትነትን መብት የሚጠብቁበት እና የሚቆጣጠሩበት ሕግ የላቸውም።
በኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር በቅጅ እና ተዛማች መብቶች የሮያሊቲ አስተዳደር አመራር ድምጻዊ ኃይሌ ሩትስ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን መልክ ለማስያዝ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ይገልጻል።
ነገር ግን ኢትዮጵያ እስካሁን የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ባለመሆኗ በተለይ በዲጂታል የሚሠራጩ የአዕምሮ ንብረት ባለቤትነትን ማስጠበቅ ሳይቻል ቀርቷል።
የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን የተለያዩ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን፣ የአዕምሮ ንብረት ባለቤትነትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስጠበቅ አንደኛው ነው።
ከኤአይ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ድንበር ተሻጋሪ የባለቤትነት ጥያቄዎች (ኮፒ ራይት) ጉዳዮች የሚታዩትም በዚሁ ዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፍ ነው።
ኢትዮጵያም የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል የኮፒራይት አዋጆቿን እያሻሻለች ነው።
በአዋጁ ማሻሻል ላይ የኤአይ ጉዳይ መነሳቱን የጠቀሰው ድምጻዊ ኃይሌ፣ የወጥ ሥራዎች መብት መጠበቅ በሕጉ እንዲካተት ተደርጎ እየመጣ መሆኑን ገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ የሙዚቃ ሥራዎች በራዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ ለንግድ ትርፍ ጥቅም ላይ በሚውሉበት ጊዜ ገንዘብ መሰብሰብ የሚያስችል ሥርዓት እየዘረጋን ነው ብሏል።
ይህንን ከአዕምሮ ንብረት ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር ሆነው ለማስመረቅ እና ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጁ መሆናቸውን በመገለፅም በኤአይ የሚሠሩም ሆኑ ሌሎች ሥራዎች ወደ ሕግ ማዕቀፍ እንደሚገቡ አስረድቷል።
የኮፒራይት ሕግ በየጊዜው ከዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች መወለድ ጋር አብሮ እየተሻሻለ መጥቷል።
እንደ ስፖቲፋይ ያሉ ሌሎች የሙዚቃ ማሰራጫዎች እና ማውረጃዎች የባለቤትነት መብትን መጠበቅ የሚያስችሉ ሥርዓቶችን ዘርግተዋል።
የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኩ - ዩቲዩብ - ባለፈው ዓመት ወጥነት ለሌላቸው እና ከሌሎች ለተቀዱ ሥራዎች ክፍያ መፈፀም እንደሚያቆም ገልጿል።
ይህ የሌሎች ሰዎች የሙዚቃ ሥራዎች በኤአይ ተቀናብረው መቅረባቸውን ባያስቆምም፣ በኤአይ የተቀናበሩ ወጥ ሥራዎች ለአድማጮች እንዲቀርቡ ያበረታታ ይመስላል።
"የሙዚቃ ዲሞክራሲ ዘመን"
ድምጻዊያን ሥራዎቻቸውን ለአድማጭ ለማድረስ ዓመታትን ይገብራሉ። የተሻለ ሥራ ይዞ ወደ አድማጭ ለመድረስ የአቀናባሪዎችን ወረፋ መጠበቅ፣ ፕሮዲዩሰሮችን መፈለግ ይጠበቅባቸዋል።
አቀናባሪዎችም ከስቱዲዮዋቸው ሳይወጡ ቀኑን እና ሌሊቱን ያሳልፋሉ። በዚህም ዘመን የማይሽራቸውን የሙዚቃ ሥራዎች አበርክተዋል፤ እያበረከቱ ነው።
ሆኖም በአቅም እጦት ብቻ ብቃት እና ተሰጥኦ እያላቸው ህልማቸውን ማሳካት ሳይችሉ የቀሩ አሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ የሙዚቃ ሥራዎችን በዓለም አቀፍ የሙዚቃ ጥራት ደረጃ ማቅረብ አለመቻሉ ብዙ ጊዜ የሚነሳ ጉዳይ ነው።
የኤአይ ባለሙያው አቤኔዘር የሰው ሠራሽ አስተውሎት በሙዚቃውም ሆነ በፊልሙ ዘርፍ 'ዲሞክራሲ' ይዞ መጥቷል ይላል።
ብዙ አቅም እና ሃብት ሳያስፈልግ፣ ጥበቃ ሳይኖር ጥሩ የሙዚቃ ሃሳብ ያለው ባለሙያ ጥሩ ሥራ መሥራት ይችላል ብሎ ያምናል አቤኔዘር።
ለዚህም በቅርቡ በዓለም የዲጂታል ሙዚቃ ሰንጠረዥ ላይ በአንደኝነት ሲደመጥ የነበረውን 'ዎክ ማይ ዎክ' የተሰኘውን የአገረሰብ ሙዚቃን ይጠቅሳል። ሙዚቃውን በሰባት ወራት ውስጥ 10 ሚሊዮን አድማጮች ተመልክተውታል።
አቤኔዘር በተለይ በሙዚቃው ዘርፍ አዳዲስ ሙዚቃ ለመሥራት በብዙ መንገድ ፈተና የሆነባቸውን ባለሙያዎች ወደ ሙዚቃውና ወደ ሙያው እያስገባ እንደሆነ ይናገራል።
"አንድ ሙዚቀኛ አንድ መሣሪያ እና ሃሳብ ካለው ግጥሞችን አዘጋጅቶ ጥሩ ሙዚቃ ማዘጋጀት ይችላል፤ ይህ መቶ በመቶ ትክክለኛ ነው አይደለም የሚለው ጥያቄ ውስጥ እንዳለ ሆኖ ጥሩ ዕድልን እየፈጠረ ነው ብዬ አስባለሁ።"
ይህ ግን ሙዚቃ በስሜት እና በቡድን የሚሠራ ጥበብ እንጂ በኮምፒዩተር የሚዘጋጅ አይደለም ለሚለው ድምጻዊ ፀሐዬ አይዋጥለትም።
ፀሐዬ ኤአይ በሌሎች ዘርፎች ሊረዳ ቢችልም፣ የሙዚቃ ሥራን ግን አያቀልም ብሎ ነው የሚያምነው።
"ሙዚቃ እንጨት መፍለጥ አይደለም። ሙዚቃ በቡድን የሚሠራ ሥራ ነው። ምን ስላጣን ነው በኤአይ ሙዚቃ የምንሠራው? ትክክለኛ የነበረው ነገር ስላጣነው ነው የምንሠራው?! . . . በሰው ተፈጥሮ ሊወጣ የማይችል እንጉርጉሮ እና ቅላፄ የምንሰማው። ይህ አሰልቺ ነው" ይላል።
የሙዚቃ ባለሙያዋ ብሌን በበኩሏ ትክክለኛው ሁለቱን ሚዛናዊ አድርጎ ማስኬድ ነው የሚል አቋም አላት።
ኤአይ ጊዜን እና ገንዘብን ሳይፈጅ በፍጥነት ሙዚቃ ለመሥራት የሚያስችል ቢሆንም የኢትዯጵያን ታሪክ፣ ባህል፣ የሙዚቃ መሣሪያዎች፣ አገላለፆች በትክክል ስለማይሰጥ በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ማንነታችንን ሊነጥቀን ይችላል ስትል ስጋቷን ትገልጻለች።
ነገር ግን ይህንን በመፍራት ከቴክኖሎጂው ጋር እኩል ከመራመድ ራስን መግታት እንደማይገባ ትመክራለች።

የፎቶው ባለመብት, Walk My Walk
ኤአይ የፈጠራ አቅምን ያዳክማል ወይስ ያሻሽላል?
ኤአይ የሰዎች ጫና ለማቅለል እና ጊዜን ለመቆጠብ ያግዛል በሚል ጥቅም ላይ ቢውልም የሰውን ልጅ የፈጠራ አቅም ያዳክማል የሚሉ አስተያየቶች ይሰማሉ።
ድምጻዊ ኃይሌ ኤአይ "የሰው ልጅ ፈጠራ ፀር ነው" ይላል።
"ኤአይ ሙዚቃ የሚሠራው በዓለም ላይ ካሉ ዜማዎች ተምሮ ነው። እንደ የሰው ልጅ አዲስ ፈጠራ አይሠራም" ሲልም ምክንያቱን ያስቀምጣል።
ምንም ቢሆን የቱንም ያህል ደረጃ ላይ ቢደርስ ከሰው ልጅ ፍጥረት እና አቅም ይበልጣል ብሎም አያስብም።
የእርሱን ሃሳብ ፀሐዬም ይጋራዋል። ኤአይ ሌሎች ሥራዎችን ለማሳለጥ ቢያግዝም በተለይ በሙዚቃው ዘርፍ የሰውን ልጅ አቅም ወደ ዜሮ የሚያወርድ ነው ብሎ ያምናል።
አሁን በምሰማው ነገር ደስተኛ አይደለሁም የሚለው ፀሐዬ፣ "የወደፊቱ ዓለም አስጨናቂ ነው። ለብዙ ነገር ጥሩ አይደለም" ብሏል።
የኤአይ ባለሙያው አቤኔዘር ግን ጥቅም እና ጉዳቱ የሚወሰነው እንደ አጠቃቀማችን ነው የሚል ሃሳብ አለው።
"በሙዚቃውም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ኤአይ ገና ጅምር ላይ ነው ያለው። ሕጎች፣ መመሪያዎች እና ደንቦች የሉም። " የሚለው አቤኔዘር፣ ይህ ክፍተቶችን ቢፈጥርም ኤአይ የሰው ልጅን የፈጠራ አቅም ያግዛል እንጂ ያዳክማል የሚል እምነት የለውም።
"የሙዚቃ እውቀት የሌለው ባለሙያ ከሰው ጋር የሚደርስ ሙዚቃን መሥራት አይችልም።
የተሠሩትን ሥራዎችን ለመገምገምም የሙዚቃ እውቀት እና የፈጠራ አቅምን ይጠይቃል" ይላል።
ኤኤይ አጋዥ እንጅ የሰውን ልጅ ፈጠራ የሚተካ አይደለም የሚለው አቤኔዘር፣ ሙዚቀኞች ይህንን እውቀት ማሳደግ እና መጠቀም ካልጀመሩ ስለ ሙዚቃ ምንም እውቀት የሌለው ሰው ኢንደስትሪውን ያበላሸዋል የሚል ስጋት አለው።
"ፈጠራ ይነጥፋል፣ ሙድ ይጠፋል" የምትለው ብሌንም፣ ለባለሙያዎች አዲስ ዕይታ በመስጠት፣ በማነቃቃት ረገድ ኤአይ መልካም ጎን እንዳለው ትጠቅሳለች።
ሆኖም ትክክለኛ የፈጠራ ባለሙያዎችን ችግር ውስጥ ሊከት ይችላል የሚል ስጋት አላት።
"ኤአይ ውበት የሆኑ፣ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ የሆኑና ያልተጋነኑ ስህተቶችን ይነጥቃል። ይህም ስህተትን መፍራት ስለሚፈጥር እንዲሁም ከፍጥነቱ ጋር መራመድ ስለማይቻል በኤአይ ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ክህሎት ያላቸው የፈጠራ ሰዎችን ይነጥቀናል" ስትል አስረድታለች።
ጥናቶችም ለጥያቄዎች እና ውስብስብ ችግሮች ፈጣን ምላሽ የሚሰጡ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) መተግበሪያዎች እየበዙ መምጣታቸው የሰው ልጅን የማሰብ አቅም ሊያዳክሙ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
ኤአይ ላይ የሚኖር "ሙሉ በሙሉ የሆነ ጥገኝነትን" ማስወገድ እንደሚገባም ይመክራሉ።

የወደፊቱ የሙዚቃ ዓለም፡ ወደ ስቱዲዮ ወይስ ወደ ኤአይ?
አንጋፋው ድምጻዊ ፀሐዬ በቴክኖሎጂው የግስጋሴ መነፅር የወደፊቱን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ሲመለከት የሚታየው ስጋት ነው።
ባለሙያዎች ሥራቸውን ሲነጠቁ፣ የሰው ልጅ ፈጠራ ዳዋ ሲውጠው ነው የሚታየው።
ኃይሌ ሩትስም የሙዚቃ ምርጫ ለአድማጩ የሚተው ቢሆንም የኢትዮጵያ ሙዚቃ ለዛ ማሳጣቱ አይቀሬ ነው ይላል።
አቤኔዘር ግን የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ ሙዚቃ በዓለም አቀፍ ደረጃ እኩል ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያደርግ ዕድል ይዞ ስለመጣ የወደፊቱ ሙዚቃ ጥሩ መልክ እንደሚኖረው ይገምታል።
ምክንያቱን ሲያስረዳም ሌላው ዓለም ላይ ያሉ ባለሙያዎች የፈለጉትን ዓይነት ሙዚቃ ወይም የፈጠራ ሥራ ለመሥራት የገንዘብ እንዲሁም ቴክኖሎጂ አቅሙ አላቸው፤ አፍሪካ ግን ብዙ የሚነገር ታሪክ እና ባህል ቢኖረውም በአቅም ችግር ምክንያት የሚፈለገውን ያህል ለዓለም ማሳየት ሳይቻል መቆየቱን ይገልጻል።
ኤአይ ለሁሉም እኩል መድረክ መስጠት በመቻሉ ወደፊት ጥሩ ሥራዎችን ይጠብቃል።
በመሆኑም ሙዚቀኞች የቴክኖሎጂ ዕውቀታቸውን በማሳደግ መጠቀም እንዲጀምሩ ይመክራል። ይህ ካልሆነ ግን እውቀት የሌለው ሰው ዘርፉን መበረዙ አይቀር ሲልም ያሳስባል።
አዲሱ ቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ብቻም ሳይሆን ለበርካታ ዘርፎች ስጋት ይዞ ነው የመጣው የሚለው ድምጻዊ ፀሐዬ በበኩሉ ኤአይ አዎንታዊ በሆነ መልኩ የሚለውጠው ነገር አለ ብሎ አያምንም።
"ኤአይን ማስቆም የሚቻልበት መንገድ ስለሌለ ዝም ብሎ ከመመልከት ውጪ ምርጫ የለም" ብሏል።
ሙዚቀኛዋ ብሌንም በተለይ የኢትዮጵያ ሙዚቃ እና ኤአይ መዋደድን የሚፈጥረው ዕድል እንዳለ ብታምንም ስጋት አላት።
ኤአይ በዓለም ላይ የተማራቸው ሙዚቃዎች ላይ ተመሥርቶ፣ ብዙኃኖች በተጠቀሙበት መንገድ እንደሚሠራ የምትገልፀው ብሌን፣ "እንደ ኢትዮጵያ የራሳቸው የሙዚቃ መሣሪያ ፣ ምት፣ ያሬዳዊ መሠረት ያላቸው ዜማዎች ለኤአይ ሩቅ ናቸው፤ በመሆኑም የእኛ ባልሆኑ ነገሮች ሊተኩ እና ልናጣቸው እንችላለን" ትላለች።
ከዚህም ባሻገር ታሪክን፣ ማንነትን፣ ባህልን ወዳልሆነ መንገድ ሊወስደው እንደሚችል ታስረዳለች።
ይህም የሚመጣው ትውልድ ኤአይ በውል ያልተረዳውን እና ያልሠራውን የእኛን የማይመስል ሙዚቃ ሊረከብ ይችለል የሚል ፍርሃት አላት።
ሆኖም የቴክኖሎጂን በረከት መቀበል እንደሚገባ ፤ ነገር ግን ራስን ማጣት እንዳይመጣ ሚዛናዊ በማድረግ እንደ አጋዥ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ትመክራለች።
"ይህን ሚዛን ከሳትን ከባድ ነው የሚሆነው። ምን ሊሆን ይችላል? የሚለውን ግን መተንበይ አዳጋች ነው" ብላለች።















