ቻይና ከረዥም ሕንጻ ጋር ስለተጋጨው አውሮፕላን መረጃ የማትሰጠው ለምንድን ነው?

ሲአይቲአይሲ ታወር የተባለው ባለ 109 ፎቅ ሕንጻ ጉዳት ደርሶበታል

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሲአይቲአይሲ ታወር የተባለው ባለ 109 ፎቅ ሕንጻ ጉዳት ደርሶበታል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በቤይጂንግ አነስተኛ አውሮፕላን ከረዥም ሕንጻ ጋር ተጋጭቶ አብራሪው ከሞተ አራት ቀናት ተቆጥረዋል።

አውፕላኑ የጫነው አብራሪውን ብቻ ነበር። በደረሰው አደጋ 13 ሰዎች ተጎድተዋል። አደጋው ለምን እና እንዴት እንደተከሰተ እስካሁን መረጃ አልወጣም።

የቻይና መንግሥት በሚያስተዳድረው 'ቤይጂንግ ዴይሊ' ላይ ስለ አደጋው መሠረታዊ መረጃ የሚገልጽ መግለጫ በ60 ቃላት ብቻ ተወስኖ ወጥቷል።

ከቻይና ኮምኒስት ፓርቲ ዋና መሥሪያ ቤት በጥቂት ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ በዦንግናንሂ ስለደረሰው አደጋ ዝርዝር መረጃ አለመውጣቱ አጠያያቂ ሆኗል።

ሲአይቲአይሲ ታወር የተባለው ባለ 109 ፎቅ ሕንጻ ጉዳት ደርሶበታል።

አውሮፕላኑ ከሕንጻው ጋር ሲጋጭ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ከኢንተርኔት ላይ እንዲጠፉ ተደርጓል።

ሦስት የአቪዬሽን ተቋማት ለቢቢሲ እንደገለጹት የአነስተኛ አውሮፕላኖች ጉዞ እንዳይከናወን ተነግሯቸዋል። ተቋማቱ ዝርዝር መረጃ እንዳይሰጡ ስለታዘዙ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት አልፈቀዱም።

በተፈጠረው የመረጃ ክፍተት ምክንያት ስለ ክስተቱ የሴራ ትንታኔዎች እየተሰራጩ ይገኛሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዓለም ላይ ጠንካራ የበረራ ቁጥጥር ከሚደረግባቸው አገሮች አንዷ በሆችው ቻይና አውሮፕላኑ እንዴት መጓጓዝ ቻለ የሚለው ከተነሱት ጥያቄዎች አንዱ ነው።

ቻይና መረጃን ስታፍን ይሄ የመጀመሪያው አይደለም። የቻይና ኮምኒስት ፓርቲ ወይም አስተዳደሩ ላይ ትችቶች ሲሰነዘሩ መስማት አልተለመደም።

ትችት አዘል ወይም ፖለቲካዊ ውይይት በፍጥነት ይከስማል።

ከአውሮፕላን አደጋው ጋር ያልተያያዙ የአውሮፕላን ምሥሎች አልያም የስላቅ አስተያየቶችም ከቻይና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እንዲሰረዙ ተደርጓል።

በቻይና የወይን ጠርሙስ ቅርጽ የተሠራው ሕንጻ ዝነኛ ነው። ብዙዎች መልካም ዕድል የሚያመጣ ሕንጻ አድርገው ይወስዱታል።

በፈተና ጥሩ ውጤት ለማምጣት ወይም ሥራ ለማግኘት የሚፈልጉ ወጣቶች ሕንጻውን ይጎበኛሉ፤ ሕንጻው አጠገብ ፎቶ ተነስተው ከፀሎት ጋር በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩታል።

አይ ኦን ቻይና የተባለው የበይነ መረብ ድረ ገጽ ኃላፊ ማናያ ኮታስ እንደሚሉት ቤይጂንግ ስለ አውሮፕላን አደጋው መረጃ ማፈን የፈለገችው "በትክክል ምን እንደተፈጠረ እስካሁን እርግጠኛ ስላልሆኑ" ነው።

"እንዲህ ያለ ክስተት የተለመደ አይደለም። የመንግሥትን ብቃት ጥያቄ ውስጥ የሚከት እና የፓርቲውን ትርክት የሚገዳደር ነው" በማለት ያስረዳሉ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአቪዬሽን ተቋማት አነስተኛ አውሮፕላኖች እንዳይጓጓዙ መታገዱን ከማረጋገጥ ባለፈ መረጃ ለመስጠት አልፈለጉም።

ቤይጂንግ የምትሠራ የበረራ ማሠልጠኛ ተቋም ባለሙያ "ስለ ጉዳዩ እንዳናወራ ታዝዘናል። እባካችሁ ሌሎችን አነጋግሩ" ብላለች።

ቼንግዱ የሚገኝ ሌላ ተቋም የትኛው መሥሪያ ቤት ትዕዛዙን እንደሰጠ ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቶ የስልክ ንግግሩን ቶሎ አቋርጧል።

የቤይጂንግ ዋነኛ የፖለቲካ ተቋማት በሚገኙበት አካባቢ ማለትም እስከ 100 ስኩዌር ኪሎሜትር ባለው ርቀት በረራ አይፈቀድም።

ይህም ቲያናመን አደባባይ እና የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚኖሩበት እንዲሁም የሚሠሩበትን ዦንግናንሂ ቅጥር ጊቢ ይሸፍናል።

የቻይና ተንታኙ ቢል ቢሾፕ በኤክስ ገጻቸው "ክስተቱ ከፍተኛ የደኅንነት ክፍተት ነው። አውሮፕላኑ ጥቂት ሰከንዶች ቢጓዝ ዦንግናንሂ ይደርሳል። ይህም በቤይጂንግ የደኅንነት ሥርዓት ከፍተኛ ቀውስ ያስከትላል" ብለዋል።

ቻይና በቅርቡ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ላይ ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፋለች።

ድሮኖች ወደ ዋና ከተማዋ ቤይጂንግ ከመግባታቸው እና ከመውጣታቸው በፊት መመዝገብ አለባቸው።

በቺካጎ ካውንስል ኦፍ ግሎባል አፌርስ የጥናት ክፍል ምክትል ፕሬዝዳንት ሬይመርድ ኩዎ "ከድሮን ከፍ ያለ አነስተኛ አውሮፕላን ወደ ዦንግናንሂ መድረሱ ከፖለቲካ አንጻር አሳፋሪ እና የደኅንነት ክፍተትም ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።

የፓይለቱ ወይም የቴክኒክ ስህተት ሊሆን ቢችልም "ሆነ ተብሎ የተፈጸመ ድርጊት" ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል።

ቻይና ሠራሽ አውሮፕላኑ ሁለት መቀመጫ ያለው አውሮራ ኤስኤ60ኤል መሆኑን የበረራ መረጃ ተከታታዩ ፍላይትራዳር24 ገልጿል።

6.9 ሜትር ርዝመት እና 8.6 ሜትር ስፋር ያለው ሲሆን፤ ከአውሮፕላን ላይ ሆኖ ፎቶ ለማንሳት ወይም ለመዝናናት የተሠራ ነው።

የአውሮፕላን አደጋው በአሜሪካ፣ ኒው ዮርክ መስከረም 11/2001 የደረሰውን እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሞቱበትን ጥቃት ያስታወሳቸውም አሉ።

በካርኒጌ ቻይና አጥኚ የሆኑት ቾንግ ጃን ኢን እንዳሉት ክስተቱ በአውሮፓውያኑ 1987 ከተፈጠረው ጋር ይመሳሰላል።

የቀዝቃዛው ጦርነት ሊያከትም አካባቢ ጀርመናዊው ጀማሪ አብራሪ ማቲያስ ረስት በሞስኮ ሬድ ስኩዌር አውሮፕላን አጋጭቷል።

"አደጋው የሶቪየት የመከላከያ ሥርዓትን ክፍተት ያሳየ ነበር። የአየር ደኅንነት ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል" ይላሉ።

በቤይጂንግም ተመሳሳይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ጠቁመዋል።

"አነስተኛ አውሮፕላን ኢአይቲአይሲ ታወርን ገጭቷል ማለት ተመሳሳይ ድርጊት በድሮን ወይም ሚሳዔል ሊፈጸም ይችላል ማለት ነው። ይሄም ለቤይጂንግ የደኅንነት ሠራተኞች አሳፋሪ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።