ሴቶች ከወንዶች በላይ ረዥም ዕድሜ የሚኖሩበት ምክንያት ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, MStudioImages/Getty Images
ሴቶች ከወንዶች አንጻር በአማካይ ከአምስት ዓመት የበለጠ የመኖር ዕድላቸው ሰፊ ነው።
የሴቶች ዕድሜ የአምስት ዓመት ብልጫ ያሳያል የተባለው ዓለም አቀፍ አማካዩ ተወስዶ እንደሆነ አጥኚዎች ይናገራሉ።
በእርግጥ ሴቶች ከወንዶች በበለጠ ለምን ለረዥም ዓመት እንደሚኖሩ ሳይንቲስቶች በትክክል አላወቁም።
ሌሎች ፍጥረታትን እንደ ማነጻጸሪያ ብንወስድ ወንድ ወፎች ከሴቶች በበለጠ ይኖራሉ።
በዩናይትድ ኪንግደም የሥነ ሕዝብ እና ዕድሜ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ሳራ ሀርፐር "በሁሉም አገራት ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ይኖራሉ" ይላሉ።
ቁጥሩ ከአገር አገር ቢለያይም ጠቅለል ባለ ሁኔታ ሴቶች ከወንዶች ዘለግ ላለ ጊዜ ይኖራሉ።
በሩሲያ፣ ዩክሬን እና ቬትናም ሴቶች ከወንዶች በበለጠ ለ10 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ይኖራሉ።
በናይጄሪያ ደግሞ ያለው ልዩነት ጠባብ እንደሆነ 'አወር ወርልድ ኢን ዳታ' ያወጣው አሃዝ ያሳያል።
ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ይህ ልዩነት የተፈጠረው ግላዊ ባህሪን ጨምሮ በማኅበራዊ ልዩነት ነው።
ፕሮፌሰር ሳራ በሩሲያ ወንዶች ዘንድ መጠጥ እና ሲጋራ በጣም መዘውተራቸው ልዩነት አምጥቷል።
በሌሎችም አገራት ወንዶች "ሕይወትን የሚያሳጥር" ባህሪ እንዳላቸው ይናገራሉ።
"አመጋገባቸውም ጤናማ አይደለም" ይላሉ ፕሮፌሰር ሳራ።
ወንዶች አዘውትረው ወደ ሕክምና አለመሄዳቸውን ባለሙያዋ ይጠቅሳሉ።
"ባለትዳር ወንዶችን አጋሮቻቸው ሆስፒታል ስለሚወስዷቸው የተሻለ ሕይወት አላቸው" ይላሉ።
በብዙ ማኅበረሰቦች ውስጥ ወንዶች "አደገኛ" የሚባል ሥራ እንደሚያከናውኑ እና ወንድነት "ራስን ለአደጋ ከማጋለጥ" ጋር እንደሚተሳሰር ይናገራሉ።
"ወንዶች በከፍተኛ መጠን በመኪና አደጋ፣ በግጭት፣ በግድያ፣ ራስን በማጥፋት ሕይወታቸውን ያጣሉ" ይላሉ።
በዩናይትድ ኪንግደም በአውሮፓውያኑ በ1960ዎቹ እና በ1970ዎቹ የፀረ ሲጋራ ንቅናቄ መደረጉ የሚሞቱ ወንዶችን ቁጥር ቀንሶ ነበር።
በወቅቱ በወንዶች እና በሴቶች መካከል ያለው በሕይወት የመኖር ልዩነት ጠብቦ እንደነበር ፕሮፌሰር ሳራ ያስረዳሉ።
የሰዎች አኗኗር ሊለወጥም በፆታዎች መካከል ያለው ልዩነት ከተፈጥሯዊ አወቃቀር ጋርም የተያያዘ እንደሆነ ይናገራሉ።
በወንዶች እና በሴቶች መካከል ያለው ልዩነት የሚቀየር እንዳልሆነ ያክላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Quynh Anh Nguyen/Getty Images
ኤስትሮጂን እና ቴስቴስትሮን
በሴቶች እና ወንዶች መካከል ያለው አንድ ልዩነት የሆርሞን ነው።
በስፔን፣ ቫሌንሺያ ዩኒቨርስቲ የዕድሜ መግፋት ላይ ጥናት የሚሠሩት የሥነ ልቦና ባለሙያ ፕሮፌሰር ኮንሱዌሎ ቦራስ "ኤስትሮጂን ሴቶችን የመጠበቅ ሚና አለው" ይላሉ።
ይህ ሆርሞን የኮሌስትሮል መጠንን የመቆጣጠር፣ የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም የማስተካከል፣ ከሽንት ትቦ ጋር የተያያዙ ኢንፌክሽኖችን የማስቆም እንዲሁም የአንጎል እና አጥንት ጤናን የመጠበቅ ሚና አለው።
ኤስትሮጂን፤ የሰውነት ሕዋሳት የሚደርስባቸውን ጉዳት የሚከላከሉ (antioxidant) ንጥረ ነገሮች በማምረትም ጠቀሜታ ይሰጣል።
ፕሮፌሰር ኮንሱዌሎ "በማረጥ ወቅት ኤስትሮጂን ማጣት የሰውነትን አሠራር የሚጎዳ ነው" በማለት ያስረዳሉ።
የአጥንት መዳከም (osteoporosis) በኤስትሮጂን መጠን መቀነስ ምክንያት ከሚከሰቱ እክሎች አንደኛው ነው።
ሰውነት ውስጥ ያለውን ተፈጥሯዊ የሆርሞን መዋዠቅ ለማስተካከል ተጨማሪ ሆርሞን በመስጠት የሚከናወነው ሕክምና (hormone replacement therapy) እንደ አማራጭ ይወሰዳል።
ማረጥ በሚጀምርበት ወቅት ይህ የሆርሞን ሕክምና ሲሰጥ የሴቶችን የሰውነት እንቅስቃሴ ለማደስ እንደሚረዳ ባለሙያዋ ያስረዳሉ።
በወንዶች ሰውነት ውስጥ ያለው የቴስቴስትሮን ሆርሞን፤ ራስን ለአደጋ ከሚያጋልጡ ባህሪዎች ጋር የሚተሳሰር ነው።
ሆርሞኑ በሰውነት ውስጥ አሉታዊ ጫና እንዳለው ፕሮፌሰር ኮንሱዌሎ ቢያምኑም ትክክለኛ ጉዳቱ ምን እንደሆነ በትክክል እንደማይታወቅ ይናገራሉ።
በአውሮፓውያኑ 2012 የወጣ ጥናት የተሠራው የዘር ፍሬያቸው እንዲመክን የተደረጉ ኮሪያውያን ላይ ነው።
እነዚህ ወንዶች ሰውነታቸው ውስጥ ቴስቴስትሮን ባለመመረቱ ምክንያት ካልመከኑ ወንዶች በበለጠ ከ14 እስከ 19 ዓመት ኖረዋል።
የጥናቱ ውጤት ውስንነት ቢኖረውም እንሰሳት ላይ የተሠሩ ሌሎች ምርምሮች ተመሳሳይ ግኝት አላቸው። እነዚህ ግኝቶች ወንዶች ሲመክኑ ዕድሜያቸው እንደሚረዝም ያሳያሉ።
ለረዥም ዓመት የመኖር ምሥጢር የሚፈታው በሆርሞን ብቻ አይደለም። ከግምት ከሚገቡት መካከል ዝግመተ ለውጥ ይጠቀሳል።

የፎቶው ባለመብት, Half point images/Getty Images
ዝግመተ ለውጥ
ሳይንቲስቶች ከሰዎች ባለፈ እንሰሳትንም በማጥናት መልስ ለማግኘት እየሞከሩ ይገኛሉ።
በሰዎች ዘንድ ብቻ ሳይሆን ከአጥቢ እንሰሳት መካከልም ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ይኖራሉ። አንበሳ፣ በግ እና አይጥን እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን።
አእዋፍትን ስንመለከት ግን ወንዶች የበለጠ ዕድሜ አላቸው።
በጀርመን በማክስ ፕላንክ ተቋም የሚሠሩት የዝግመተ ለውጥ አጥኚ ዶ/ር ጆአና ስታርክ እንደሚሉት ልዩነቱ የሚፈጠረው በክሮሞዞም ምክንያት ሊሆን ይችላል።
"በአጥቢ እንሰሳት ዘንድ ሴቶች ሁለት ኤክስ ክሮሞዞም አላቸው። ወንዶች ደግሞ አንድ ኤክስ እና አንድ ዋይ ክሮሞዞም አላቸው" ይላሉ።
ሁለት የኤክስ ክሮሞዞም ሴቶችን የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ መላ ምቶች ተቀምጠዋል።
"አንደኛው ክሮሞዞም ላይ ለውጥ ቢፈጠር ሌላ ተጨማሪ ክሮሞዞም አላቸው" ይላሉ ዶ/ር ጆአና።
ወንዶች ግን አንድ ኤክስ ክሮሞዞም ብቻ ስላላቸው በዚህ ክሮሞዞም ላይ የሚፈጠር ለውጥ ይጎዳቸዋል።
ወንድ ወፎች ሁለት ዜድ ክሮሞዞም ሲኖራቸው ሴቶቹ ዜድ እና ዋይ አላቸው።
"አጥቢ የሆኑ እንሰሳት ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ሲኖሩ ወንድ ወፎች ከሴቶች የበለጠ ዕድሜያቸው የሚረዝምበት ምክንያት ይሄ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ያስረዳሉ።
በ2025 ይፋ የተደረ ጥናት እንደሚጠቁመው አንድ የትዳር አጋር ያላቸው እንሰሳት "በፆታዎች መካከል ልዩነት" እንደሚታይባቸው ይጠቁማል።
ዶ/ር ጆአና በሠሩት በዚህ ጥናት እንደ ዝንጀሮ እና አንበሳ ያሉ እንሰሳት ላይ የፆታ ልዩነቱ እንደሚጎላ ያሳያል።
"በእነዚህ እንሰሳት ዘንድ ወንዶች ብዙ ሴቶች ለማግኘት ይፎካከራሉ" ይላሉ ባለሙያዋ።
ወንዶች ጉልበት የሚጠይቅ ሥራ ለማከናወን እና የሴቶችን ትኩረት ለመሳብ በዝግመተ ለውጥ ሰውነታቸውን እየፈረጠመ መምጣቱን ይናገራሉ። ይሄንን የሚያደርጉት በሕይወት የመኖር ዕድላቸውን በመቀነስ ነው።
ልጆችን የመንከባከብ ኃላፊነት ያለባቸው ሴቶች (ሰዎች እና ዝንጀሮዎችን ጨምሮ) ረዥም ዕድሜ መኖር ይጠበቅባቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, The Good Brigade/Getty Images
ረዥም ዓመታት መኖር
ሴቶች ከወንዶች በበለጠ ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ለሞት የማያጋልጡ በርካታ ሕመሞች ይገጥሟቸዋል።
ከእነዚህ መካከል የጀርባ ሕመም፣ ድባቴ እና ራስ ምታት ይጠቀሳሉ።
ባለሙያዋ እንደሚያስረዱት ሴቶች ጠንካራ በሽታን የመከላከል አቅም ቢኖራቸውም ሰውነት ጤናማ ሕዋስ አደገኛ መስሎት የሚያጠቃበት ሁኔታ (anti-inflammatory diseases) ይገጥማቸዋል።
በዚህ ምክንያትም የጡንቻ እና አጥንት መዳከም ይከሰታል።
"ወንዶች የሰውነት መዋቅራቸው ለሞት ተጋላጭ ያደርጋቸዋል። ሴቶች ደግሞ በሰውነት መዋቅራቸው ምክንያት ለአካል ጉዳት ይጋለጣሉ" ይላሉ።
የሰውነት መዋቅር ብቻውን ረዥም ዕድሜ መቆየትን የሚያረጋግጥ እንዳልሆነ ተመራማሪዎቹ ያስረዳሉ።
ፕሮፌሰር ኮንሱዌሎ "የሰውነት መዋቅራችን በአካባቢያችን እና በባህሪያችን ይወሰናል" ይላሉ።
ወንዶችም ሆኑ ሴቶች አመጋገባቸውን ማስተካከል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ጭንቀት መቀነስ እና የተሻለ እንቅልፍ ማግኘት አለባቸው።
እነዚህ መንገዶች ረዥም ብቻ ሳይሆን ጤናማ ሕይወትን ለመግፋትም መሠረታዊ ናቸው።















