የኒው ዮርኩ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ አናት ላይ ወጥተው ቀለበት ያሰሩት ጥንዶች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ኢቫን በሕንጻው አናት ላይ ሳሉ ተንበርክኮ አንጅላ እንድታገባው ጠይቋታል

የፎቶው ባለመብት, US Pool

የምስሉ መግለጫ, ኢቫን በሕንጻው አናት ላይ ሳሉ ተንበርክኮ አንጅላ እንድታገባው ጠይቋታል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በአሜሪካ፣ ኒው ዮርክ የሚገኘው 'ኢምፓየር ስቴት' ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ አናት ላይ የወጡት ጥንዶች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋሉ።

102 ፎቅ ያለው ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ አናት ላይ የወጡት ጥንዶች መነጋገሪያ ሆነዋል።

የሕንጻው ጫፍ ላይ የወጡት ሩሲያውኑ ጥንዶች የ32 ዓመቱ ኢቫን በርኩስ እና የ33 ዓመቷ አንጄላ ኒኮላው ናቸው። ኢቫን በሕንጻው አናት ላይ ሳሉ ተንበርክኮ አንጄላ እንድታገባው ጠይቋታል።

ጥንዶቹ ቀለበት ካሰሩ በኋላ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የሕንጻው አናት ላይ ሙሉ ጥቁር ልብስ አድገው ከወጡ በኋላ በጥቁር ጨርቅ ላይ የተጻፈ መፈክር አውለብልበዋል።

ጽሁፉ በግርድፉ ወደ አማርኛ ሲመለስ "ፍቅር የሥልጣን ጥምን ካሸነፈ ዓለም ሰላም ያገኛል" የሚል ትርጓሜ ያለው መፈክር ነው።

በእንግሊዘኛው "When the power of love beats the love of power the world knows peace"።

ጥንዶቹ ከሕንጻው ጫፍ ከመውረዳቸው በፊት ሲሳሳሙ ታይተዋል።

102 ፎቅ ያለው ሰማይ ጠቀስ አናት ላይ የወጡት ጥንዶች መነጋገሪያ ሆነዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, 102 ፎቅ ያለው ሰማይ ጠቀስ አናት ላይ የወጡት ጥንዶች መነጋገሪያ ሆነዋል

ጥንዶቹ 1,454 ጫማ (443 ሜትር) በሚረዝመው ሕንጻ አናት ላይ ወጥተው ቢያንስ ለ10 ደቂቃ ቆይተዋል።

ሁለቱ ፍቅረኛሞች በሌሎች አገራትም ተመሳሳይ ድርጊቶች በመፈጸም ይታወቃሉ።

ታሪካቸውን መነሻ በማድረግ በአውሮፓውያኑ 2024 'ስካይዋከርስ፡ ኤ ላቭ ስቶሪ' የተባለ ዘጋቢ ፊልም ተሠርቷል።

የኒው ዮርክ ፖሊስ ጥንዶቹ መታሰራቸውን ለቢቢሲ አረጋግጧል።

ሰብሮ በመግባት፣ በግድ የለሽነት ለአደጋ በመጋረጥ፣ በወንጀል ድርጊት፣ የተከለከለ ሥፍራ በመግባት እና ባልተገባ ድርጊት ሊከሰሱ እንደሚችሉ የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ዘግቧል።

የሕንጻው ቃል አቀባይ "ያልተፈቀደው ድርጊት" ነዋሪዎች፣ ጎብኚዎች እና እንግዶች ላይ ምንም ጉዳት እንዳላስከተለ ተናግረዋል።

በኒው ዮርክ ታወቂ ከሆኑ እና ብዙዎች ከሚጎበኟቸው ሕንጻዎች አንዱ የሆነው ኢምፓየር ስቴት ለጋብቻ ጥያቄ ለማቅረብ መዳረሻ በመሆን ይታወቃል።

ጥንዶቹ በሕንጻው 103ኛ ፎቅ በኩል ለእድሳት በተዘጋጀ መወጣጫ አድርገው ወደ ጫፉ እንደደረሱ ተገልጿል።

ጥንዶቹ የወጡበት የሕንጻው ክፍል ለሕዝብ ክፍት ስላልሆነ ከ10ኛ ፎቅ ወደ 103ኛ ፎቅ እንዴት እንደተሻገሩ ግልጽ አይደለም።

በሕንጻው አናት ላይ የሚገኘው የቴሌኮምዩኒኬሽን አንቴና ድረስ ወጥተው ወርደዋል።

ኢቫንስ ለአንጄላ የታገቢያኛለሽ ጥያቄውን ተንበርክኮ ሲያቀርብ የፊት ጭምብሏን አውልቃ ደስታዋን ገልጻለች።

ከዚያም ያደረገላትን ቀለበት ፎቶ ስታነሳ ታይታለች።

ከሕንጻው እንደወረዱም የኒው ዮርክ ፖሊስ "ሰላም እንዴት ናችሁ? እዚህ ላይ መውጣት አትችሉም" ሲላቸው ይደመጣል።

አንጅላ እጇን ከፍ አድርጋ "ደኅና ነኝ" ትላለች።

ፖሊስ ምን ቋንቋ እንደሚናገሩ ሲጠይቃቸው "ሩሲያኛ" ብለው ምላሽ ሰጥተዋል።