የደቡብ አፍሪካ ፀረ ስደተኞች ቀነ ገደብ መድረሱን ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ተቃዋሚዎችን አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
ደቡብ አፍሪካን ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ ስደተኞችን በተመለከተ ሰልፍ ለማካሄድ ያቀዱ ዜጎች ተቃውሟቸውን ማሰማት ያለባቸው ያለ "ማስፈራሪያ፣ ዛቻ ወይም ቀነ ገደብ" መሆን እንዳለበት አስጠነቀቁ።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉትን ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው የውጭ አገር ዜጎች ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው እንዲወጡ በፀረ ስደተኛ ቡድኖች የተቀመጠው ይፋዊ ያልሆነ ቀነ ገደብ አንድ ቀን ሲቀረው ትናንት ሰኞ ባወጡት መግለጫ ነው።
ይህንን ተቃውሞ ተከትሎ ሊመጣ የሚችለው የኃይል እርምጃ ስጋት ውስጥ የከተታቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ የሌሎች የአፍሪካ አገራት ዜጎች ባለፉት ሳምንታት ውስጥ ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው ወጥተዋል።
ሕጋዊ ሰነድ የሌለው አንድ የማላዊ ዜጋ አራት ህጻን ልጆቹን ጥሎ በመሄዱ "ልቡ ቢሰበርም" ወደ አገሩ "ለመመለስ ደስተኛ መሆኑን" ለቢቢሲ ተናግሯል።
ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ ስደተኞች ላይ የሚነሱ ተቃውሞዎች ጎልተው ታይተዋል። ፕሬዝዳንት ራማፎሳ የስደተኞች ጉዳይ ላይ ሪፎርም እንደሚያስፈልግ ተቀብለው፤ ሰልፈኞች ግን በሰላማዊ እና ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ እንዲንቀሳቀሱ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ በሳምንታዊው መግለጫቸው ለአገሪቱ ዜጎች ባስተላለፉት መልዕክት፤ "ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚኖሩ አንዳንድ የውጭ አገር ዜጎች እዚህ ያሉት በሕጋዊ መንገድ ነው" ብለዋል።
"ይሰራሉ፣ ይማራሉ፣ ቤተሰብ ያስተዳድራሉ፣ በኢኮኖሚያችን ላይ ኢንቨስት ያደርጋሉ እንዲሁም ለማህበረሰባችን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። እነሱም ቢሆኑ በሕጋችን እና በሕገ መንግሥታችን የመጠበቅ መብት አላቸው" ሲሉ አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ "የመቃወም መብት እና የመናገር ነፃነት ሰዎች ሌሎችን እንዲያስፈራሩ፣ ጫና እንዲፈጥሩ ወይም በዘረፋ እና በኃይል ድርጊቶች ላይ እንዲሳተፉ አይፈቅድም" በማለት ጽፈዋል።
ይፋዊ ቁጥሮች እንደሚያሳዩት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው የውጭ አገር ዜጎች አሉ።
ስደተኞች ላይ ተቃወሞ ያነሱ አካላት ባስቀመጡት ቀነ ገደብ ምክንያት ለደኅንነታቸው የሰጉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በጊዜያዊ መጠለያዎች ለመመዝገብ እየተጠባበቁ ነው።
ትላልቅ ሰልፎች በተካሄዱባት ደርባን ከተማ የሚገኙ እና የማላዊ ዜጎችን መጠለያ የሆኑ የነጭ ድንኳን መጠለያዎች እየፈረሱ ነው። ባለሥልጣናቱ ጊዜያዊ መጠለያዎቹን ለማጽዳት የሚያደርጉትን ጥረት እያፋጣኑ ነው።
ደማቅ ቀለሞች ያሉት የባሕላዊ ልብሶችን ያደረጉ የማላዊ ዜጎች ወደ አገራቸው የሚመልሳቸውን ባስ በሰልፍ ሲጠብቁ ታይቷል።
በዛሬው ዕለት በደርባን፣ ጆሃንስበርግ እና ሌሎች ከተሞች ለሚደረጉት ፀረ ስደተኞች ሰልፎች ፈቃድ ተሰጥቷል።
በሰልፉ ላይ ምንም አይነት የኃይል እርምጃ እንዳይኖር ለአዘጋጆቹ ማስጠንቀቂያ የሰጡት የአገሪቱ ባለሥልጣናት፤ ሊኖር የሚችል ማንኛውም ሁከት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ባሕላዊ መሣሪያዎችን መያዝም የተፈቀደ እንዳልሆነ ፖሊስ ቢያስታውቅም፤ ይህ ሁኔታ በሰልፈኞቹ እና ፖሊስ መካከል ውጥረት እንዳይፈጥር ተሰግቷል። ምክንያቱም ተቃውሞው ላይ የሚሳተፉት የዙሉ ብሔረሰብ ተወላጆች ወደ ሰልፎች ሲሄዱ ጋሻ፣ ጅራፍ እና ዱላ የመያዝ ልማድ አላቸው።
የመንግሥት መረጃ እንደሚያሳየው፤ በ2026 መጀመሪያ ተቃውሞ መነሳት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ12 ሺህ በላይ ስደተኞች ተባርረዋል ወይም ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
ባለፉት ሳምንታት ውስጥ ጋና፣ ማላዊ፣ ሞዛንቢክ፣ ናይጄሪያ እና ዚምባብዌ ዜጎቻቸውን በአውሮፕላን ወይም በባስ ለማስወጣት ጥረት አድርገዋል። የእነዚህ አገራት ዜጎች የሆኑ 3,500 ገደማ የውጭ አገር ዜጎች ለመውጣት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።















