የአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት ለተማሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ማንበብን ግዴታ አደረገች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት የትምህርት ምክር ቤት በግዛቲቱ የሚገኙ አምስት ሚሊዮን የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ማንበባቸውን ግዴታ የሚደርግ ዕቅድ አጸደቀ። ይህ ውሳኔ በሃይማኖት እና በመንግሥት መካከል ያለውን መለያየት የተመለከተ ውዝግብ አስነስቷል።
የቻርልስ ዲከንስ እና የዊሊያም ሼክስፒርን ታሪኮችን ማንበብን ጭምር ግዴታ የሚያደርገው ይህ እቅድ ከሦስት ዓመት በኋላ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።
አዲሱ የንባብ መስፈርት የሃይማኖት ነፃነትን የሚጥስ እና ብዝሃነትን የሚሸረሽር ነው የሚል ትችት ከአንዳንዶች ቀርቦበታል።
በሪፐብሊካኖች ቁጥጥር ስር ያለው የግዛቲቱ የትምህርት ምክር ቤት ውሳኔውን 9 ለ 5 በሆነ ድምጽ ሲያጸድቀው፤ አንድ ሪፐብሊካን ከዴሞክራቶች ጋር በመተባበር ተቃውሞ አስመዝግበዋል።
የግዛቲቱ የትምህርት ምክር ቤት እና የሪፐብሊካን ፓርቲ አባል የሆኑት ብራንደን ሆል "መጽሐፍ ቅዱስን ከ60 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትምህርት ቤቶች እየመለስን ነው" ሲሉ በዚህ ሳምንት ተናግረው ነበር።
የውሳኔው ደጋፊዎች፤ ለአገሪቱ ምሥረታ አስፈላጊ እንደሆኑ የሚገልጿቸውን የአይሁድ-ክርስቲያን ባሕሎችን ተማሪዎች መማር እንዳለባቸው ይናገራሉ።
አዲሱ የተማሪዎች የንባብ ዝርዝር በቴክሳስ የሚገኙ ተማሪዎች ማንበብ ያለባቸውን መጽሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ አዘጋጅቷል።
ዝርዝሩ የቻርለስ ዲከንስን 'ግሬት ኤክስፔክቴሽንስ' እና የዊሊያም ሼክስፒር 'ዘ ትራጄዲ ኦፍ ጁሊየስ ሲዛር' የመሳሰሉ ዘመን አይሽሬ የእንግሊዝ ሥነ ጽሑፍ ሌሎችንም ያካትታል።
ነገር ግን ከትምህርት እና ከሲቪል ነጻነት ቡድኖች ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው አስገዳጅ የሃይማኖት ጽሑፎች በዝርዝሩ ውስጥ መካተታቸው ነው።
ተማሪዎች በአዲስ ኪዳን ውስጥ ስለ ኢየሱስ የሚናገሩትን ክፍሎች የሚማሩ ሲሆን፣ የጠፋው ልጅ ምሳሌም በሥርዓተ ትምህርቱ ይካተታል።
በቴክሳስ ግዛት 'ፍሪደም ኔትወርክ' የተባለው የግራ ክንፍ አክቲቪስት ቡድን ዋና ዳይሬክተር የሆነችው ፌሊሺያ ማርቲን ከድምጽ አሰጣጡ ቀደም ብላ የውሳኔ ሐሳቡ "ከሌሎች የሃይማኖት እምነቶች እና ወጎች ሁሉ በላይ ክርስትናን ማዕከል ያደረገ ነው" ብላ ነበር።
"ይህ በጣም ምዕራባዊያንን ማዕከል ያደረገ አመለካከት ያለው ሲሆን፣ ለአጠቃላይ የታሪካችን ግንዛቤ ወሳኝ የሆኑትን የተለያየ ቀለም ያላቸውን፣ ቀደምት የአሜሪካ ዜጎችን እንዲሁም ሌሎች ሃይማኖታዊ እምነቶች እና ወጎችን አስተዋጽኦ እና ታሪክን ችላ ያለ ነው" ስትል ተችታለች።
ሌሎች ደግሞ ውሳኔው መምህራን ተማሪዎቸቻውን በመምራት በኩል ያላቸውን ነፃነት ሊያዳክም እንደሚችል ስጋታቸውን ጠቅሰዋል።
"የቴክሳስ መምህራን የንባብ ዝርዝሩ መብዛት እና የትኞቹ ለተማሪዎቸቻው ተገቢ እንደሆኑ እና አስፈላጊ እንደሆኑ በመወሰን ረገድ ነፃነትን ሊጠፋ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል" ሲሉ ከቴክሳስ መምህራን ማኅበር ክሌር ሃፍነር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የምክር ቤቱ ውሳኔ የመጨረሻ ፈቃድ የሚፈለገውን ዝርዝር የቀነሰው ቢሆንም፣ ማኅበሩ ግን አሁንም ዝርዝሩ በጣም ብዙ እንደሆነ ይናገራል።
ቢቢሲ የቴክሳስ ግዛት የትምህርት ምክር ቤትን አስተያየት ለማግኘት ጥያቄ አቅርቧል።
አሁን በመጽደቀው በቴክሳስ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የክርስትና እምነትን ለማጠናከር የግዛቲቱ ወግ አጥባቂዎች ከወሰዷቸው እርምጃዎች መካከል የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ነው።
ባለፈው ዓመት ግዛቲቱ በትምህርት ክፍሎች ውስጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚወሰዱትን የአሥርቱ ትዕዛዛትን ዝርዝር እንዲሰቅሉ በማድረግ ቴክሳስ ትልቋ የአሜሪካ ግዛት ሆናለች።
ውሳኔውን በተመለከተ ተቃውሞ የቀረበለት የፌዴራል ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በሚያዝያ ወር ላይ የአሥርቱ ትዕዛዛት በክፍሎች ውስጥ መሰቀላቸውን ሕጋዊነት በመቀበል አጽንቶታል።
የቴክሳስ ግዛት ውሳኔን በተመለከተ አርብ ዕለት አስተያየት የሰጡት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እርምጃው በአሜሪካ ውስጥ የሃይማኖት እሴቶችን ማስፋፋት መሆኑን በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ፕሬዝዳንቱ "ሃይማኖት ከብዙ ዓመታት በፊት ከነበረው የበለጠ ትልቅ እና ጠንካራ ሆኖ ወደ አገራችን ተመልሷል" ሲሉ በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደ የሃይማኖት ነፃነት ዝግጅት ላይ ተናግረዋል።














