በዩኬ በተደራጀ የኢሚግሬሽን ወንጀል ላይ በተወሰደ እርምጃ ከ300 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዩናይትድ ኪንግደም ፖሊስ ሕገ ወጥ ንግድ እና የኢሚግሬሽን ወንጀል ላይ በወሰደው እርምጃ 57 ስደተኞችን ጨምሮ ከ300 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።
የአገሪቱ ብሔራዊ ፖሊስ አዛዦች ምክር ቤት ለአምስት ቀናት በዘለቀው ተልዕኮ አንድ ሚሊዮን ፓውንድ ጥሬ ገንዘብ መያዙንም አስታውቋል።
ተልዕኮው ወንጀልን ለመከላከል በፀጉር ቤቶች፣ የሲጋራ ሱቆች፣ የመኪና ማጠቢያ ስፍራዎች፣ ምግብ ማብሰያ እና የውበት ሳሎኖች ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን፤ ምክር ቤቱ እንደዚህ አይነት የንግድ ስፍራዎች በወንጀለኞች ዒላማ የሚሆኑ ናቸው ብሏል።
በተለይም ለተደራጁ የማፍያ ቡድኖች "በሕገ ወጥ መንገድ እንዲሰሩ ለመደበቅ፣ ተጋላጭ የሆኑ ስደተኞችን ለመበዝበዝ እና በወንጀል የተገኘን ሕገ ወጥ ገንዘብ ሕጋዊ ለማስመሰል" ዕድል ይሰጣሉ ሲልም አክሏል።
ተልዕኮው የዩናይትድ ኪንግደም አብዛኞቹን የፖሊስ ኃይሎች፣ የአገር ውስጥ መስሪያ ቤት እና የኢሚግሬሽን እና ንግድ ደረጃዎች ባለሥልጣንን ያሳተፈ ነው የተባለ ሲሆን፤ በዚህም በአጠቃላይ 362 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የድንበር ደኅንነት እና የጥገኝነት ሚኒስትር አሌክስ ኖሪስ ተልዕኮውን "ፖሊስ፣ የኢሚግሬሽን አስፈፃሚዎች እና ሌሎች አጋሮች የታለመ ትብብር ያደረጉበት" ተምሳሌት የሚሆን እርምጃ ነው ብለዋል።
የፀጥታ ኃይሎች እርምጃ የቢቢሲ የምርመራ ዘገባን ተከትሎ ባለፈው መጋቢት በ30 ሚሊዮን ፓውንድ የተደራጁ ወንጀሎች ክፍል ይፋ ከሆነ በኋላ የተወሰደ ነው።
እስከ ሰኔ ድረስ ባለ መረጃ በዚህ ዓመት ብቻ በአነስተኛ ጀልባዎች 11,638 ስደተኞች ወደ ዩኬ ገብተዋል። ይህም በ2025 ከተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ37 በመቶ ዝቅተኛ ነው።
የብሔራዊ ፖሊስ የተደራጁ የኢሚግሬሽን ወንጀሎች መሪ ምክትል አዛዥ ወንዲ ገኒይ በበርካታ የፀጥታ ተቋማት የተወሰደው እርምጃ ሕግ አስከባሪዎች ሕገ ወጥ ንግድን ለመከላከል እና ፍትሕን ለማስፈን በትብብር እየተሰሩ እንደሆነ ግልፅ መልዕክት ነው ብለዋል።
የንግድ ባለቤቶች እና ስደተኞችን በሕገ ወጥ መንገድ የቀጠሩ ሰዎችም በፍትሐ ብሔር ለመክሰስ እንደታሰበ አክለው ተናግረዋል።















