በቀድሞዎቹ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር እና የኒው ዮርክ ዐቃቤ ሕግ ላይ በፍርድ ቤት የቀረቡ ክሶች ውድቅ ተደረጉ

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ምርመራዎችን ሲያካሂዱ የነበሩት የቀድሞው የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ጄምስ ኮሚ እና የቀድሞዋ የኒው ዮርክ ዐቃቤ ሕግ ሌቲሺያ ጄምስ የቀረበባቸው ክስ በፍርድ ቤት ውድቅ ተደረገ።

የአሜሪካ ፍርድ ቤት በቀድሞዎቹ ኃላፊዎች ላይ የተመሠረተውን ክስ ያልተቀበለው ጉዳዩን የሚከታተሉት ዐቃቤ ሕግ የተሾሙት በሕገ ወጥ መንገድ እንደሆነ በመግለጽ ነው።

የቀድሞው የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ኮሚ፤ ከኃላፊነታቸው የተባረሩት በፕሬዝዳንት ትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን ነበር። ኮሚ ከኃላፊነት ሲነሱ ትራምፕ ባሸነፉበት የአውሮፓውያኑ 2016 ምርጫ ላይ በሩሲያ ጣልቃ ገብነት ስለመኖሩ ምርመራ እያደረጉ ነበር።

ባለፈው መስከረም ወር ላይ ደግሞ ለኮንግረስ ሐሰተኛ የምስክርነት ቃል በመስጠት ፍትሕ እንዲጓደል አድርገዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። ትራምፕ የቀድሞው የኤፍቢአይ ዳይሬክተር እንዲታሰሩ ትዕዛዝ ከሰጡ በኋላ የቀረበውን ይህንን ክስ የተመራውም ፕሬዝዳንቱ ለዚሁ ብለው በሾሟቸው አዲስ የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ነው።

ሌላኛው ተከሳሽ የቀድሞ የኒው ዮርክ ዐቃቤ ሕግ ሌቲሺያ ጄምስም በተመሳሳይ ከትራምፕ ጋር ጥሩ ግንኙነት የላቸውም። የቀድሞዋ ዐቃቤ ሕግ ትራምፕ በድጋሚ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ቀቦባቸው የነበረውን የሲቪል ማጭበርበር ክስ ምርመራ ሲመሩ ነበር።

ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ የፕሬዝዳንትነት ሥልጣኑን ከተረከቡ በኋላ ዒላማ ውስጥ የገቡት ሌቲሺያ፤ በባንክ ማጭበርበር እና ለፋይናንስ ተቋም ሐሰተኛ መረጃ በመስጠት ወንጀሎች ክስ ተመሥርቶባቸዋል። ኮሚም ሆነ ሌቲሺያ የቀረበባቸው ክስ ፖለቲካዊ ባህሪ ያለው እንደሆነ በመግለጽ ጥፋተኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

በሁለቱ የቀድሞ ኃላፊዎች ላይ የተመሠረተው ክስ ትራምፕ መስከረም ላይ በሾሟቸው አዲሷ ዐቃቤ ሕግ ሊንዚ ሀሊገን የተመራ ነው። ሊንዚ የተሾሙት የቀድሞ ጊዜያዊ ዐቃቤ ሕግ ኤሪክ ሲበርት በሁለቱ የቀድሞ ኃላፊዎች ላይ ክስ እንዲመሠርቱ በትራምፕ አስተዳደር የደረሰባቸውን ጫና ተከትሎ ከኃላፊነት ከለቀቁ በኋላ ነው።

ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ ካሜሮን ከሪ ባስተላለፉት ውሳኔ ክሱን እንዲመሩ በትራምፕ የተመረጡት ዐቃቤ ሕግ የኃላፊነት ቦታው ላይ ለመቀመጥ ብቁ እንዳልሆኑ አስታውቀዋል።

የቀድሞ የዋይት ሐውስ ረዳት የነበሩት ዐቃቤ ሕግ ሊንዚ ከዚህ ቀደም ክስ መርተው የማያውቁ በመሆናቸው የአሁኑን ጉዳይ በጁሪ ፊት ይዘው እንዲቀርቡ እንዳልተፈቀደላቸው ዳኛው በውሳኔያቸው ላይ አስፍረዋል።

በዳኛዋ ገለጻ መሠረት የሊንዚ ሃሊገን ሹመት ጊዜያዊ ዐቃቤ ሕጎች የሚሾሙበትን መንገድ የሚደነግገውን የአገሪቱን ሕግ የጣሰ ነው። ሕጉ፤ ፕሬዝዳንቱ በሴኔት ፊት አቅርበው የሚያስሾሙትን ዋና ዐቃቤ ሕግ እኪመርጡ ድረስ ባለው 120 ቀናት ውስጥ መሾም የሚችሉት አንድ ዐቃቤ ሕግ ብቻ እንደሆነ ደንግጓል።

ይህ የ120 ቀናት ቀነ ገደብ የቀድሞው ዐቃቤ ሕግ በተመረጡበት የአውሮፓውያኑ ጥር 21 መጀመሩን ያስታወሱት ዳኛዋ፤ ግንቦት 21 ላይ ቀኑ በመጠናቀቁ አዲስ ጊዜያዊ ዐቃቤ ህግ መሾም እንደማይቻል አስታውቀዋል። መስከረም 22 ላይ የተሾሙት ሊንዚም "ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ቦታው ላይ ሲያገለግሉ" መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም ምክንያት ክሱ ውድቅ ተደርጓል። ይሁን እንጂ የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ በኋላ ላይ በድጋሚ መዝገቡ እንዲከፈት ማድረግ ይችላል።

የዋይት ሀውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮላይን ሌቪት፤ ውድቅ የተደረገው የሁለቱ ቀድሞ ኃላፊዎች ክስ "በጣም በቅርቡ" ይግባኝ እንደሚቀርብበት ገልጸዋል።

የትራምፕ አስተደዳር፤ ዐቃቤ ሕጓ የተሾሙበት መንገድ ሕጋዊ ነው በሚለው አቋሙ እንደሚጸናም ተናግረዋል። ካሮላይን አክለውም ዳኛዋ ኮሚ እና ሌቲሺያን "ለመከላከል እየሞከሩ" ነው በማለት ከስሰዋል።