ወደ ሩሲያ የተጓዙት የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድርድሩ ላለመሳካቱ አሜሪካ ያቀረበቻቸውን ጥያቄዎች ወቀሱ
ወደ ሩሲያ ያመሩት የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በፓኪስታን ሲደረግ የነበረው የሰላም ድርድር ያልተሳካው አሜሪካ ባቀረበቻቸው ከልክ ያለፉ ጥያቄዎች ምክንያት ነው ሲሉ ውስጥ ለመገናኛ ብዙኃን ተናገሩ።
በሩሲያዋ ሴንት ፒተርስፐርግ ከተማ ያረፉት አራግቺ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚደረገውን ጦርነት በተመለከተ ከሩሲያ አጋሮች ጋር እንደሚነጋገሩ በፐርሺያ ቋንቋ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ገልጸዋል።
ከሩሲያ በፊት ወደ ፓኪስታን አቅንተው የነበሩት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢስላማባድ የነበራቸው ቆይታ በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ድርድሩ ሊቀጥል ይችላል የሚለው ላይ ያተኮረ እንደነበር አስረድተዋል።
አራግቺ በቃለ መጠይቃቸው በኢራን ስለተዘጋው የሆርሙዝ ወሽመጥ አንስተዋል። በወሳኙ የባሕር መስመር በኩል ደኅንነቱ የተጠበቀ ጉዞ ማድረግ ዓለም አቀፍ ጉዳይ ሆኖ መቀጠሉን የጠቀሱት ጠቅሰዋል።
እንደ ኦማን ያሉ ጎረቤት አገራት ወሽመጡን በተመለከተ ከኢራን ጋር ባላቸው የጋራ ፍላጎት ላይ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
ኢራን እና ኦማንን የሚያስማሙ በርካታ ነጥቦች መኖራቸውን ጠቁመውም፤ ሁለቱ አገራት ሆርሙዝን በተመለከተ ተጨማሪ ንግግር ለማድረግ ስምምነት ላይ እንደደረሱ ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሩሲያ ቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር እንደሚገናኙ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።
የፓኪስታን ቆይታቸውን “እጅግ ውጤታማ” ሲሉ የገለጹት አራግቺ፤ “ኢራን ላይ የተከፈተውን ጦርነት በዘላቂነት ለመቋጨት የሚያስችል ማዕቀፍን በተመለከተ የኢራንን አቋም” ማሳወቃቸውን ጠቅሰዋል።
“እውነትም አሜሪካ ዲፕሎማሲን በቁም ነገር ትወስደው እንደሆነ እናያለን” ሲሉ ቅዳሜ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጽፈዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ኢራን መደራደር ከፈለገች በስልክ መነጋገር እንደሚቻል እና ልዑካኖቻቸውን ወደ ፓኪስታን እንደማይልኩ ተናግረዋል።