110 ኪሎ ግራም ካናቢስ በሻንጣቸው ውስጥ የተገኘ የሲሪላንካ መነኮሳት በቁጥጥር ስር ዋሉ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በሲሪላንካ በሻንጣቸው ውስጥ 110 ኪሎ ግራም ካናቢስ ደብቀው ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ሲሞክሩ የተገኙ 22 መነኮሳት በአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋሉ።

የጉሙሩክ ባለሥልጣናት ቅዳሜ ዕለት መነኮሳቱ በዋና ከተማዋ ኮሎምቦ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ እያንዳንዳቸው 5 ኪሎ ግራም የሚመዝን 'ኩሽ' የተባለ አደንዛዥ ዕጽ በሻንጣቸው ውስጥ ደብቀው መገኘታቸውን ገልጸዋል።

በዋናነት ተማሪዎች ናቸው የተባሉት መነኮሳት በቁጥጥር ስር ሲውሉ በስም ያልተገለጸ ግለሰብ ለአራት ቀናት ወጪያቸውን ሸፍኖ የእርፍት ጊዜያቸውን በታይላንድ እንዲያሳልፉ አድርጎ እየተመለሱ ነበር።

ጉዞውን ያዘጋጀው 23ኛው መነኩሴ በኮሎምቦ ከተማ ዳርቻ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ ለቢቢሲ ሲንሃላ ተናግሯል።

እንደ ተጠባባቂ የፖሊስ ቃል አቀባይ ገለጻ፣ በጉዞው ያልተሳተፈው መነኩሴ ለሌሎች መነኮሳት "እነዚህ እቃዎች በልገሳ የተገኙ ናቸው" በማለት አንድ መኪና እቃዎቹን ለመውሰድ እንደሚመጣ ነግሯቸዋል።

ምረምራውን የያዘው ፖሊስ ከስሪላንካ ቤተመቅደሶች የመጡት አንዳንድ መነኮሳት በሞባይል ስልኮቻቸው ላይ መደበኛ ልብሶቻቸውን ለብሰው የእረፍት ጊዜያቸውን ሲያሳልፉ የሚያሳይ ምስል እና ቪዲዮዎች አግኝቷል።

22ቱ መነኮሳት እሁድ ዕለት ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ለተጨማሪ ምርመራ ለሰባት ቀናት በእስር ቤት እንዲቆዩ ተደርገዋል።

ፖሊስ ለቢቢሲ ሲንሃላ መነኮሳቱ ምን እንደያዙ እንደማያውቁ ተናግሯል።

እጾቹ የተገኙት በትምህርት ቤት ቁሳቁሶች እና ጣፋጭ ነገሮች መካከል ነው።

በአውሮፕላን ማረፊያ በኩል ወደ አገሪቱ በድብቅ አደንዛዥ ዕፅ በማዘዋወር ወንጀል የተጠረጠሩ መነኮሳቶች ሲያዙ የመጀመርያው ጊዜ ነው።