የቀድሞው የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ጀምስ ኮሜይ በሁለት ወንጀሎች ተከሰሱ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የቀድሞውን የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ጀምስ ኮሜይ ከዚህ ቀደም ለኮንግረስ የሰጡትን ምስክርነት ተከትሎ በሁለት ወንጀሎች ተከሰሱ።

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተቺ የሆኑት ኮሜይ እአአ በ2020 መስከረም ወር ላይ ሚስጢራዊ መረጃን ለሚዲያ ተላልፎ እንዲሰጥ ፈቅደዋል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ለኮንግረስ በሰጡት ምስክርነት ላይ ዋሽተዋል ተብሏል።

ለቀረበባቸው ክስ ምላሽ የሰጡት ኮሜይ ነጻ ሰው ነኝ በማለት "በፌደራል የፍትህ ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ እምነት" አለኝ ብለዋል።

የቀድሞ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ጀምስ ኮሜይ የዩናይትድ ስቴትስ ፍርድ ቤት የሐሰት መግለጫዎችን በመስጠታቸው እና ፍትህን በማደናቀፍ ወንጀል መከሰሳቸውን ተከትሎ ነው ነጻ ሰው ነኝ ያሉት።

የኮሜይ ክስ የተሰማው ትራምፕ የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ፓም ቦንዲ የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ኮሜይን ጨምሮ አጥብቀው እንዲመረምሩ ከጠየቁ በኋላ ነው።

ክሱን ያዙት በቨርጂኒያ አቃቤ ሕግ የሆኑት ሊንድሲ ሃሊጋን ሲሆኑ ከዚህ ቀደም የትራምፕ የግል ጠበቃ ነበሩ።

ኮሜይ በቨርጂኒያ በሚገኘው ችሎት ፊት መስከረም 29 2018 ዓ.ም. ቀርበው ክሱ ይነበብላቸዋል ሲል በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘግቧል።

የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በመግለጫቸው ላይ ክሱ "ይህ የፍትህ ቢሮ በሕግ የተሰጣቸውን ሥልጣን አለ አግባብ የሚጠቀሙትን እና የአሜሪካን ሕዘብ የሚያሳስቱትን ተጠያቂ ለማድረግ ዝግጁ ነው" ብለዋል።

ኮሜይ የተከሰሱት ሐሰተኛ መግለጫ በመስጠት እና ፍትህን በማደናቀፍ በሚሉ ሁለት ወንጀሎች ነው።

የፍትህ ቢሮ ችሎቱን ኮሜይ ላይ ሦስት ክሶች እንዲመሰረት የጠየቀ ቢሆንም ሁለቱ ክሶች ብቻ በበቂ ማስረጃ የተደገፉ መሆናቸውተገልጿል።

ሦስተኛው ክስ ሌላ ሐሰተኛ መግለጫ መስጠት የሚል ነበር።

የኮሜይን ክስ የሚመለከቱት በአቃቤ ሕግ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተውጣጥተው የሚመረጡ ግለሰቦች (ጁሪ) ሲሆኑ የሚቀርበው ክስ በፍርድ ቤቱ ለመታየት በበቂ ማስረጃ ተደግፏል የሚለው ላይ በቅድሚያ ይወስናሉ።

ኮሜይ በወንጀል የተከሰሱ የመጀመርያው የኤፍቢአይ የቀድሞ ዳይሬክተር ሲሆኑ ቃለመሃላ ፈጽመው በሰጡት ምስክርነት ላይ አለመዋሸታቸውን በድጋሚ ተናግረዋል።

ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ግን እስከ አምስት ዓመት ድረስ እስር ይጠብቃቸዋል።

የኮሜይ ጠበቃ ፓትሪክ ፊዝጄራልድ "ጂሚ ኮሜይ ዛሬ የተመሰረተውን ክስ ሙሉ በሙሉ ክደዋል። በችሎት የሚኖረውን የፍትህ ሂደት እንጠብቃለን" ብለዋል።

ኮሜይ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት "እኔ እና ቤተሰቤ ዶናልድ ትራምፕን መገዳደር ዋጋ እንደሚያስከፍል ለዓመታት እናውቃለን" ብለዋል።

"ተንበርክከን አንኖርም፤ እናንተም አንደዛው" ብለዋል፤

አክለውም "ነጻ ሰው ነኝ፤ ስለዚህ የፍርድ ሂደቱን እናያለን።"