ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ህወሓት፤ ሌተናንት ጄነራል ታደሰ የሥልጣን "ርክክብ" ካላደረጉ "ስህተት ነው የሚሆነው" ሲል ለቢቢሲ ተናገረ
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ "ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ርክክብ" የማይፈጽሙ ከሆነ "ስህተት" እንደሚሆን የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናገሩ።
የህወሓት ቃል አቀባይ ሚካኤል አስገዶም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርም "እየፈረሰ በመሆኑ" ከፌደራል መንግሥት ጋር ያለው የግንኙነት "ገመድ መበጠሱን" ገልጸዋል።
ከቢቢሲ ጋር አጭር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት ቃለ አቀባዩ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ያስተላለፈውን ውሳኔ በተመለከተ ከተለያዩ አካላት ጋር "ውይይት" እየተካሄደ እንደሆነ ተናግረዋል።
የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ሚያዝያ 11/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከስድስት ዓመት በፊት ክልሉ ውስጥ በተደረገ ምርጫ "የተመረጠው የትግራይ መንግሥት ምክር ቤት ወደ ሥራ" እንዲመለስ መወሰኑን አስታውቆ ነበር።
ህወሓት ይህንን ውሳኔው ያስታወቀው ፌደራል መንግሥት ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ የተቋቋመውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እየመሩ ያሉት ፕሬዝዳንት ታደሰ ወረደን የሥልጣን ቆይታ በአንድ ዓመት ካራዘመ ከሁለት ሳምንት ገደማ በኋላ ነው።
ቃል አቀባዩ ሚካኤል የፌደራል መንግሥት ውሳኔውን ያስተላለፈው ህወሓትን "ሳያስፈቅድ፣ ሳያማክር፣ ለብቻው" ነው ብለዋል። "ጄነራል ታደሰ የመጀመሪያው ዓመት [ላይ] የተሾመው በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት በወጣው ደንብ ነው። አሁን ግን እርሱ ተጥሶ በ2013 በወጣ ደንብ ነው" ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬዝዳንቱ የሥልጣን ዘመን በአንድ ዓመት መራዘሙን ይፋ ባደረገበት የፌስቡክ ልጥፍ ላይ ጠቅሶ የነበረው የትግራይ ጦርነት ከተጀመረ ከወራት በኋላ የወጣውን የጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋሚያ ደንብ ነበር።
ይህ ደንብ ከፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረም በኋላ አሁን በስራ ላይ ያለውን አስተዳደር ለማቋቋም በወጣው ደንብ ተሽሯል። ቢቢሲ ስለዚህ ጉዳይ ጥያቄ ያቀረበላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም የተሻረው ደንብ የተጠቀሰው "በስህተት" እንደሆነ እና እንደሚስተካከል አሳውቀዋል።
ከሰዓታት በኋላም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፌስቡክ ገጽ ላይ የወጣው ጽሑፍ ማስተካከያ ተደርጎበት በ2015 የወጣው ደንብ ተጠቅሷል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ሥልጣን የተራዘመው "ከአንድ ዓመት በፊት ሹመት" በተሰጠበት "[የ2015 ደንብ መሠረት" መሆኑን ለቢቢሲ የገለጹት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊዋ፤ ከዚህም የተነሳ ውሳኔው "ሕጋዊ" መሆኑን ተናግረዋል።
የህወሓት ቃል አቀባይ ሚካኤል በበኩላቸው ከአምስት ዓመት በፊት በወጣው የቀድሞ ሹመት በመሰጠቱ "የፕሪቶሪያ ስምምነት ስለፈረሰ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩም ፈርሷል" ባይ ናቸው።
"ስምምነቱን ያፈረሰው የፌደራል መንግሥት ነው። [ሌተናት ጄነራል ታደሰን] ለብቻው ሹሞ የላከልን ፌደራል መንግሥት ነው። ህወሓት 'ይሄንን አንቀበልም' ብሎ ይፋ አድርጓል። ይህ ግልጽ ነው፤ የሚያሻማ ነገር የለውም" ሲሉ በዚህ ምክንያት የቀድሞው ምክር ቤት እንዲመለስ መወሰኑን ገልጸዋል።
ቃል አቀባዩ፤ "ከፌደራል መንግሥት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት እንዴት ይሆናል የሚለው በቀጣይ የምናየው ይሆናል። እስካሁን ባለው ግንኙነት ግን ጊዜያዊ አስተደዳር እየፈረሰ ስለሆን የነበረን ገመድ ተበጥሷል የሚል ሀሳብ ነው የምንወስደው" ብለዋል።
ይህ ምክር ቤት የተቋቋመበት ምርጫ በፕሪቶሪያ ስምምነት ውድቅ ስለመደረጉ ጥያቄ የቀረበላቸው ቃል አቀባዩ በዚህ ሀሳብ እንደማይስማሙ ተናግረዋል።
በስምምነቱ መሠረት ምርጫው "የማይጸና (void)" እንዳልተደረገ ይልቁንም "ታግዶ" መቆየቱን ገልጸዋል። በወቅቱ የተመሠረተው የክልሉ መንግሥትም "አልፈረሰም ነበር፤ ጊዜያዊ አስተዳደር የተመሠረተው በድርድር ነው" ብለዋል።
"በድርድር የተመረጠውን ምክር ቤት ሰስፔንድድ አድርገን [አግደን]፤ ሳይፈርስ እንዲቆይ አድርገን ለሰላም ስንል [ነው የቆየነው]… [ምርጫው] አልተሰረዘም፤ ምክር ቤቱም አልፈረሰም። ሆልድ አድርገን ነው የቆየነው" ብለዋል።
የሁለት ዓመቱን ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ለትግራይ ክልል የምክር ቤት እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እስከሚደረግ ድረስ በክልሉ "አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር" እንደሚቋቋም ደንግጓል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በ2012 ዓ.ም. ትግራይ ክልል ውስጥ የተካሄደው ምርጫ "እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸና እና ተፈጻሚነት የሌለው" እንደሆነ ውሳኔ ያስተለላፈው ድምጽ ከመሰጠቱ አስቀድሞ ነበር።
የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ቀድሞው ምክር ቤት እንዲመለስ ውሳኔ ሲያስተላለፍ የተነሳው ሌላኛው ጉዳይ ምርጫው ከተካሄደ አምስት ዓመት ማለፉን የሚመለከት የሕጋዊነት ጥያቄ ነበር። ስለዚህ ጉዳይ ጥያቄ የቀረበላቸው ቃል አቀባዩ ሚካኤል፤ "ሕጋዊ ነው" ሲሉ ተከራክረዋል።
"መጀመሪያው የተዋቀረው መንግሥት በትንኮሳ፣ በጦርነት እንዲፈረስ ተደርጓል። ወደ ስራም አልገባም ነበር። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ወደዚያ እንመለሳለን ብለን ስናስብ፤ አሁን ምርጫ ማድረግ አንችልም፤ በውሳኔያችን አረጋግጠናል" ብለዋል።
እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ አሁን ምርጫ መካሄድ የማይችለው "40 ፐርሰንት እና ከዚያ በላይ የትግራይ መሬት እና የትግራይ ሕዝብ ተበታትኖ" ስላለ ነው።
አክለውም፤ በዚህ ሁኔታ "እንደ አዲስ መርጠን መንግሥት ልናቋቁም ስለማንችል፤ አሁን ያለውን፣ በ2012 የተመረጠውን ምክር ቤት ካሸጋገርን በኋላ፣ ሕጋዊ መንግሥት ከመሠረትን በኋላ የሚመጣውን ነገር ምንድነው የሚሆነው የሚለውን ቀጣይ እናያለን" ሲሉ ተናግረዋል።
በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ መሠረት ምክር ቤቱን ወደ "ሥራ እንዲመለስ" ከተደረገ በኋላ "አዲስ አስፈጻሚ ካቢኔ" እንደሚዋቀር ቃል አቀባዩ ገልጸዋል። በተጨማሪም ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት እንደሚመርጥ ተናግረዋል።
ውሳኔውን በተመለከተ የሚደረገው "ውይይት" እንደተጠናቀቀ ይህ ተግባር እንደሚከናወን፤ እስካሁን ግን ቀን "አለመወሰኑን" ተናግረዋል።
ህወሓት ምክር ቤቱ እንዲመለስ መወሰኑን ካስታወቀ በኋላ መግለጫ ሰጡት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ታደሰ፤ ውሳኔውን ተቃውመውታል። ውሳኔው "የፕሪቶሪያ ስምምነትን ውድቅ የሚያደርግ ነው" እንደሆነ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህንን እርምጃ "ተከትሎ ሊመጣ የሚችለው ጦርነት እንደሚሆን" ተናግረዋል።
ይህንን ተከትሎም ሌተናንት ጄነራል ታደሰ እንደ ቀድሞው የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ የክልሉን መዋቅር በኃይል ሊነጠቁ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ሥልጣናቸውን በምክር ቤቱ ለሚመረጠው ፕሬዝዳንት ለማስረከብ ተስማምተው እንደሆነ የተጠየቁት የህወሓት ቃል አቀባይ ሚካኤል "እርሱን በቀጣይ የምናየው ይሆናል" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ህወሓት ፕሬዝዳንቱ በመግለጫቸው የተናገሩትን "እንደማያምንበት" የተናገሩት ሚካኤል "መፈንቅለ መንግሥት አይደለም፤ መደረግ ያለበት ርክክብ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ ርክክብ እንደሚያደርጉ እምነቱ አለን። ከዚህ ውጭ የሚሄድ ሰው ካለ ወይም ከዚህ ውጪ ከሄዱ ግን ስህተት ነው የሚሆነው። ትክክል አይሆንም" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ሥልጣን ለማስረከብ ፈቃደኛ ካልሆኑ የህወሓት ቀጣይ እርምጃ ምን እንደሚሆን ቃል አቀባዩ ተጠይቀዋል።
"ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ማን እንደሚሆን አሁን መናገር አንችልም። ሥልጣን ያለው አካል ምክር ቤት ስለሆነ ማንን ፕሬዝዳንት ያደርጋል የሚለውን ነገር ቀጣይ የምናየው ነገር ነው የሚሆነው" ብለዋል።
አክለውም፤ ፕሬዝዳንት ታደሰ "በሰላማዊ ሥልጣን ያስረክባሉ አያስረክቡም የሚለው አሁን አከራካሪ ነጥብ ሊሆን አይችልም። ያኔ ስንደርስ የምናየው ነገር ነው የሚሆነው" ሲሉ ተናግረዋል።
"ጊዜያዊ አስተዳደር አሁን ፈርሷል፤ ምክር ቤቱ ወደ ሥልጣን ይመጣል" ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ፕሬዝዳንት የመሾም እና ካቤኒ የመዋቀር ሥልጣን ያለው ይኸው ምክር ቤት መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም በክልሉ ሁለት መንግሥት ይኖራል ሊባል እንደማይችል ጠቅሰዋል።
የህወሓት ውሳኔ በተመለከተ እስካሁን ድረስ ከፌደራል መንግሥት በኩል ይፋ የተሰጠ አስተያየት የለም።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ታደሰ በበኩላቸው ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ የሚመሩት ካቢኔ ሥራውን እንደሚቀጥል እና የክልሉ መንግሥት መሥሪያ ቤቶችም መደበኛ ተግባራቸውን ማከናወን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።