ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቀድሞው የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ምክር ቤት በመዋሸት ለቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ አይደለሁም አሉ
የቀድሞው የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ዳይሬክተር ጄምስ ኮሚ ለሕግ አውጭዎች ሐሰተኛ መረጃ ሰጥተዋል በሚል እና የኮንግረስን ሥርዓት በመጣስ በቀረበባቸውን ክስ ጥፋተኛ አይደለሁም ብለዋል።
በቨርጂኒያ አሌክሳንዲሪያ በጠበቃቸው ተወክለው ፍርድ ቤት የቀረቡት የቀድሞው ኃላፊ ለፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ እንዳልሆኑ ተናግረዋል።
ጠበቃቸው ፓትሪክ ፊትዝጀራልድ ደንበኛቸው የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተቺ በመሆናቸው ዒላማ ተደርገዋል በሚል እና በሌሎችም በርካታ ምክንያቶች መዝገቡን እንደሚያዘጉ ተናግረዋል።
ጄምስ ኮሚ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጠቅላይ ዓቃቢ ሕግ እርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ በሰጡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ጠበቃቸው ፈጣን የፍርድ ሂደት መጠየቃቸውን ተከትሎ ዳኛው ከጥቂት ወራት በኋላ ለጥር 5 ቀጠሮ ሰጥተዋል።
ይሁን እንጂ ዓቃቢ ሕግ እና የተከሳሽ ጠበቃ ችሎቱ ከሁለት እስከ ሦስት ቀን የሚፈጅ ነው ብለዋል።
ዕረቡ ዕለት በነበረው ችሎት የኮሚ ጠበቃ ፓትሪክ ፊትዝጀራልድ መዝገቡ ወደ ችሎት ከመሄዱ በፊት ውድቅ ለማድረግ በርካታ አቤቱታዎችን እንደሚያስገቡ ለዳኛው ተናግረዋል።
መዝገቡን የያዙት ዓቃቢ ሕግ ቂም በቀለኛ እና ይህን መዝገብ ለመያዝ በሕገ ወጥ መንገድ የተመረጡ ናቸው ሲሉም ተከራክረዋል።
የቀድሞው የኤፍቢአይ ዳይሬክተርን የክስ መዝገብ ይዘው የነበሩት የቨርጅኒያ ዓቃቢ ሕግ ኤሪክ ሲበርት ከፕሬዝዳንት ትራምፕ በቀረበባቸው ጫና ምክንያት መልቀቃቸውን ተከትሎ ሌንዚ ሃሊገን ተክተዋቸዋል።
ጄምስ ኮሚ ዕረቡ ዕለት ወደ ፍርድ ቤት ሲገቡ ከጠበቃቸው ጋር እያወሩ እና እየተቃለዱ በመልካም መንፈስ ላይ ሆነው ታይተዋል።
ሕጋዊ መብቶቻቸው እና የቀረቡባቸው ሁለት ክሶች የተነበቡላቸው ጄምስ ኮሚ በዳኛው ክሶቹን ተረድተው እንደሆነ ሲጠየቁ፤ "አዎ ክቡር ዳኛ። በጣም አመሰግናለሁ" በሚል ለፍርድ ቤቱ ምላሽ ሰጥተዋል።
ዳኛ ማይክል ናችማንኦፍ ሁለቱ ክሶች እስከ አምስት ዓመት እስራት እና 200 ሺህ ዶላር የሚያስቀጡ ወንጀሎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዓቃቢ ሕግ ሃሊገን መዝገቡን ከመያዛቸው በፊት የነበሩ ዓቃቢያነ ሕግ ጄምስ ኮሚ ላይ ክስ መመስረት የሚያስችል ማስረጃ የለም ቢሉም እርሳቸው በተመደቡ በአንድ ሳምንት ውስጥ ክስ መስርተዋል።
በዚህም የተከሳሽ ጠበቃ ዓቃቢ ሕግ በማስረጃነት ያቀረባቸው ሚስጢራዊ ሰነዶችን ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
ጠበቃ ፊትዝጀራልድ "ከፈረሱ ጋሪው እንደቀደመ ይሰማናል" ብለዋል።
ዳኛ ናችማንኦፍ ዓቃቢ ሕግን መንግሥት መረጃ ባለማጋራቱ ችሎቱን እንደማያዘገዩ ተናግረዋል።
ጄምስ ኮሚ እ.አ.አ ከ2013 እስከ 2017 ድረስ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር የነበሩ ሲሆን፤ ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው ዋይት ሐውስ በገቡ በአራተኛ ወራቸው አባርረዋቸዋል።
ኮሚ የሩሲያን የምርጫ ጣልቃ ገብነት እና በሞስኮ እና በትራምፕ የምርጫ ዘመቻ መካከል ግንኙነት መኖር እና አለመኖሩን እየመረመሩ ሳሉ ነበር ከሥራቸው የተባረሩት።
ጄምስ ኮሚ ከመንግሥት ኃላፊነታቸው ከተሰናበቱ በኋላ የዶናልድ ትራምፕ ብርቱ ትችት አቅራቢ ሆነዋል።