ንጉሥ ቻርልስ "ውጥረት በበዛበት ዓለም" ከአሜሪካ ጋር ወዳጅነት አስፈላጊ ነው አሉ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ንጉሥ ቻርልስ ሳልሳዊ በዚህ ውጥረት በበዛበት ዓለም ከአሜሪካ ጋር ወዳጅነት አስፈላጊ ነው ሲሉ ተናገሩ።

አሜሪካ ከብሪታኒያ ነጻ የወጣችበትን 250ኛ ዓመት በማስመልከት ንግግር ያደረጉት ንጉሥ ቻርልስ፣ የሁለቱ አገራትን ወዳጅነት "በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በጣም ወሳኝ የሆነ ጥምረት ያላቸው" ሲሉ አወድሰዋል።

ንጉሡ በንግግራቸው አገራት ራሳቸውን ብቻ የሚመለከቱ እንዳይሆኑ እና ከሌሎች ጋር እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙት ንጉሥ ቻርልስ ማክሰኞ ዕለት በአሜሪካ ኮንግረስ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

ቻርልስ ሳልሳዊ እአአ በ2022 ንጉሥ ከሆኑ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ አሜካን ለመጎብኘት ከባለቤታቸው ንግሥት ካሚላ ጋር ዋሺንግተን የደረሱት ሰኞ ዕለት ነበር።

ንጉሥ ቻርልሰ ዩናይትድ ኪንግደም እና ዩናይትድ ስቴትስ ያላቸውን ታሪካዊ እና ባሕላዊ ትስስር በተደጋጋሚ አጉልተው ተናግረዋል።

አገራቱ ጠንካራ እና ዘላቂ ግንኙነት እንዳላቸው የተናገሩት ቻርልሥ የአሜሪካ መሪዎች ከሌሎች አገራት ጋር መስራታቸውን እንዲቀጥሉ እንዲሁም በዓለም ጉዳዮች በአንድነት አንዲቆሙ አሳስበዋል።

ንጉሥ ቻርልስ በአሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም መካከል ያለው ግንኙነት ከዚህ በፊት በነበሩ ስኬቶች ላይ ብቻ አይመሰረትም በማለት ጠንካራ እየሆነ እና እየተሻሻለ ይሄዳል ሲሉ ተናግረዋል።

በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ባለው የኢራን ጦርነት የሁለቱ አገራት ግንኙነት መፈተኑን ያስታወሱት ንጉሡ፣ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር እያካሄደች ላለው እንዲሁም ለሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ኔቶ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

ንጉሡ በንግግራቸው በአሜሪካ የሚታየው የሃይማኖት ብዝሃነትን አወድሰው ይህም "በትራምፕ ዋሺንግተን ውስጥ በልዩነት የታየ" መሆኑን ተናግረዋል።

ንጉሥ ሳልሳዊ በሥልጣን ላይ ያሉ አካላት " ውድ እና የማይተካ ሃብታቸን የሆነችው ተፈጥሮን ለመጠበቅ ስላለብን በጋራ ኃላፊነት" ማሰብ አለባቸው ብለዋል።

ንጉሥ ቻርልስ በንግግራቸው ላይ እአአ በ2015 በንጉሥ ጆን ስለጸደቀው መሠረታዊ የሕግ ሰነድ፣ ማግና ካርታ መገዛት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ዶናልድ ትራምፕ የሚመሩት በራሳቸው አስተሳሰብ ብቻ መሆኑን ተናግረው ነበር።

በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም የፖለቲካ ቅሌት ስላስከተለው የጄፍሪ ኢፕስቴን ፋይሎችም በተዘዋዋሪ ጠቅሰዋል።

ለአራት ቀናት የሥራ ጉብኝት አሜሪካ የሚገኙት ንጉሥ ቻርልሰ የአሜሪካን የነጻነት በዓል ከማክበር ባሻገር ከዩኬ ጋር የተፈጠረውን የግንኙነት መሻከር ይጠግናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ንጉሥ ቻርለስ ከባለቤታቸው ንግሥት ካሚላ ጋር በመሆን ሰኞ ዕለት ዋሺንግተን ሲደርሱ ደማቅ አቀባባል ተደርጎላቸዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ሁለቱ አገራት የሚጋሩትን ታሪክ በማንሳት አወድሰዋል።

ሁለቱ መሪዎች በኦቫል ኦፊስ በነበራቸው የተናጠል ውይይት "በጣም ጥሩ" ውይይት ማድረጋቸውን የተናገሩት ትራፕም ንጉሥ ቻርልስ "ምርጥ ሰው" ነው ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።