ትራምፕ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕጓ ተቀናቃኞቻቸው ላይ ክስ እንዲመሰርቱ ጫና እያደረጉ ነው

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሆኑት ፓም ቦንዲ፤ የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸው ላይ በሚገባ ምርመራ እንዲያደርጉ ጠየቁ።

ትራምፕ በቀጥታ ለቦንዲ በጻፉት የማኅበራዊ ሚዲያ መልዕክት፤ "ከዚህ በላይ ልናቆየው አንችልም ያለነን ተዓማኒነት እና ስም እየገደለው ነው" ብለዋል።

ትራምፕ በቀድሞው የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ጀምስ ኮሚ፣ በ ኒው ዮርክ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሌቲቲያ ጀምስ እንዲሁም በመጀመርያው የስልጣን ዘመናቸው ከፕሬዝዳንትነት እንዲነሱ የተጠየቀበትን የፍርድ ቤት ሂደት በተከታተሉት ዲሞክራቱ ሴናተር አዳም ስቺፍ ላይ የሚደረገው ምርመራ መዘግየቱን አስመልክቶ የተሰማቸውን ብስጭት "ምንም እየተሰራ አይደለም" በማለት ገልጸዋል።

ከዚህ መልዕክታቸው በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቦንዲን "ጥሩ እየሰራች ነው" ሲሉ አሞግሰዋቸዋል።

ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ "ከ30 በላይ መግለጫዎችን እና ልጥፎችን በድጋሚ አይቻለሁ። እንደ እውነቱ ከሆነ እንደ ባለፈው ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ናቸው፤ ሁሉም ወሬ ብቻ፤ አንድም ተግባር የለበትም። ምንም እየተሰራ አይደለም። የኮሚ ጉዳይ፣ የአዳም፥ 'አጭበርባሪው' ስቺፍ፣ ሌቲሺያ??? እነዚህ ሁሉ የለየላቸው ጥፋተኞች ናቸው። ነገር ግን ምንም የተደረገ ነገር የለም" ብለዋል።

የፕሬዚዳንቱ ልጥፍ በተለያዩ የዲሞክራት አባላት ትችት ተሰንዝሮበታል።

ዲሞክራቱ ቸክ ሹመር "ይህ የአምባገነንነት መንገድ ነው" ሲሉ ተችተዋል።

"የፍትህ ቢሮ አባላት ሁል ጊዜም በጣም በጣም ጠንካራ ሠራተኞች ናቸው። በሥልጣን ላይ ያለው ማንም ይሁን ማን፤ ዲሞክራት ሆነ ሪፐብሊካን ያለምንም ፍርሃት እና መደለያ ሕግ የጣሰውን ወደ መከታተል ነው የሚሄዱት" ሲሉ እሁድ ዕለት ለሲኤንኤን ተናግረዋል።

"እርሳቸው ግን ጥፋተኛም ሆኑ አልሆኑ ጠላቶቻቸውን ማሳደጃ መሣሪያ አድረገው ነው መጠቀም የፈለጉት" ሲሉ ፕሬዚዳንቱን ተችተዋል።

ትራምፕ ይህንን አስተያየታቸው በተመለከተ እሁድ ዕለት ተጠይቀው፤ "ወደ ሥራ መግባት አለባቸው። በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት ይኖርባቸዋል" ብለዋል።

የፕሬዚዳንቱ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፍ የመጣው የፌደራል አቃቤ ሕግ የሆነው ኤሪክ ሲበርት የኒውዮርክ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የነበሩትን ሌቲቲያ ጀምስን ከቤት ግዢ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ባለመክሰሳቸው እንዲለቅ እንደሚፈልጉ መናገራቸውን ተከትሎ ሥራቸውን ከለቀቀ በኋላ ነው።

ሲበርት ከፍተኛ የፍትህ ቢሮ ባለሥልናትን ምርምራቸው ጀምስን ለመክሰስ የሚያበቃ በቂ ማስረጃ አለማቅረቡን እንደነገሯቸው ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።

ጄምስ ዲሞክራት ሲሆኑ እአአ በ2023 ትራምፕ ያቀረቡባቸውን የቤት ግዢ ማጭበርበር "መሠረተ ቢስ" እና "በበቀል ላይ የተመሰረተ" በሚል ማሸነፍ ችለዋል።

ቅዳሜ ዕለት ዶናልድ ትራምፕ ሲበርት ተባርሮ እንጂ ከሥራ ለቅቆ አይደለም ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። ሲበርትን ለመተካት እጩ ማዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።

ትራምፕ አክለውም ጠቅላይ አቃቤ ሕጓን ቦንዲን አድንቀዋል።

"በጣም ጥንቁቅ ናት፣ በጣም ጎበዝ፣ አገራችንን የምትወድ፤ ነገር ግን በምስራቃዊ የቨርጂኒያ ዲስትሪክት ጠንካራ አቃቤ ሕግ ያስፈልጋል፣ እንደ እኔ ጥቆማ ከሆነ ሊንዲሲ ሃሊጋን ሥራዎች አንዲቀላጠፉ ታደርጋለች" ብለዋል።

እአአከ1970ዎቹ ጀምሮ የፍትህ ቢሮ ራሱን ከፕሬዚዳንቱ ለማራቅ እና ነጻ ሆኖ ለመንቀሳቀስ ይሞክራል። ነገር ግን ትራምፕ ይህንን የኖረ አሰራር እየፈተኑት ነው።

በመጀመርያው የሥልጣን ዘመናቸው ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጄፍ ሴሺንስን ያባረሩ ሲሆን በመቀጠል ደግሞ ዊሊያም ባር ትራምፕ በምርጫ 2020 ወቅት ማጭበርበር ተፈጽሟል የሚለውን ሐሰተኛ ውንጀላቸውን ተከትሎ ከሥራቸው ለቅቀዋል።