ዩናይትድ ኪንግደም ጥገኝነት ጠያቂዎች የወጣባቸውን 10,000 ፓውንድ መልሰው እንዲከፍሉ ልታደርግ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዩናይትድ ኪንግድ ውስጥ የጥገኝነት ፈቃድ የተሰጣቸው ሰዎች ገንዘብ ማግኘት ሲጀምሩ ቆይታቸውን ለመሸፈን እና ለተሰጣቸው ድጋፍ ወጪ የተደረገውን 10 ሺህ ፓውንድ ገደማ ገንዘብ መልሰው መክፈል እንዳለባቸው የአገሪቱ መንግሥት አስታወቀ።
የዩኬ መንግሥት ያዘጋጀው እና ዛሬ ማክሰኞ ለፓርላማ የሚቀርበው የጥገኝነት ጠያቂዎች ረቂቅ ሕግ እንደሚያሳየው፤ በቂ ገንዘብ ያላቸው አዋቂ ሰዎች በሚሰጣቸው ጊዜ ውስጥ ወጪውን መልሰው እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ።
ይህ ሕግ ተግባራዊ የሚሆነው ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የመስራት መብት ባላቸው ሰዎች ላይ ነው። ግለሰቦቹ አገሪቱ ውስጥ በቋሚነት የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ይህንን ገንዘብ ከፍለው ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸዋል።
ይህ አዲስ አሰራር "ለጥገኝነት ጠያቂዎች ድጋፍ ማድረግ ትክክል መሆኑን፤ ነገር ግን ኃላፊነትም ጭምር እንደሆነ" እንደሚያሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሻባና ማህሞድ ገልጸዋል።
"ሰዎች አስተዋጾ ማድረግ እና የብሪታኒያ ሕዝብን በጎነት መልሰው መክፈል መቻል ሲጀምሩ ይህንን እንዲያደርጉ እንጠብቃለን" ብለዋል።
በዚህ እቅድ መሠረት የሚሠሩ እና የተወሰነ የገንዘብ መጠን የሚያገኙ ስተደኞች ቁርጥ ገንዘብ መክፈል ይኖርባቸዋል። ይህ ቁርጥ ገንዘብ 10 ሺህ ፓውንድ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ገንዘቡን መክፈል የሚጀምሩት በወር ምን ያህል ገቢ የሚያገኙ ስደተኞች እንደሆኑ እስካሁን አልተገጸም።
በሕጉ መሠረት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ክፍያውን እና ከፍተኛውን የገንዘብ መጠን የመቀየር ስልጣን ይኖራቸዋል። የሚደረገው ማስተካከያ "የታክስ ከፋዮች ፍትሐዊ መሆን፤ ስደተኞችን ደግሞ ወደ ድህነት የማያስገባ" መሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል።
ያቀረቡት የስደተኝነት ጥያቄ ውድቅ የተደረገባቸው ሰዎች ጭምር ገቢያቸው መንግሥት ያስቀመጠው የገንዘብ መጠን ላይ የደሚርስ ከሆነ ክፍያውን መፈጸም ይኖርባቸዋል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ መስሪያ ቤት መረጃ እንደሚያሳየው ባለፈው ዓመት ጥገኝነት ጠያቂዎችን ለመደገፍ አራት ቢሊዮን ፓውንድ ለስደተኞች ወጪ ተደርጓል።
አንድ ጥገኝነት ጠያቂን መንግሥት በሚያቀርበው ማረፊያ ውስጥ ለማስተናገር በቀን በአማካይ 23.25 ፓውንድ ያስወጣል፤ ሆቴል ውስጥ ከሆነ ደግሞ ይህ ወጪ ወደ 144 ፓውንድ ከፍ ይላል። ግለሰቦቹን ለመደገፍ የሚሰጠው ሳምንታዊ ክፍያ ደግሞ ከ9.95 እስከ 49.18 ፓውንድ ይደርሳል።
የአገሪቱ የስደተኞች ምክር ቤት ይህ አይነቱ "ኢፍትሐዊ፣ ተግባራዊ የማይሆን" እቅድ "ስደተኞች ላይ ተጨማሪ ታክስ" እንደሚጥል ገልጿል። "ቤተሰቦች ሕይወታቸውን መልሶ ለማቋቋም እና በእግራቸው ለመቆም የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚያከብድም" አስታውቋል።
የምክር ቤቱ የውጭ ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት ኢምራን ሁሴን፤ "ብዙ ጥገኝነት ጠያቂዎች ድጋፍ የሚፈልጉበት ምክንያት ራሱ የአገር ውስጥ ጉዳዮች መስሪያ ቤት ማመልከቻቸው እየታየ ያሉ ጥገኝነት ጠያቂዎች እንዳይሰሩ በመከልከሉ ነው" ብለዋል።
"የጥገኝነት ጠያቂዎች ድጋፍ የሚሰጠው ወደ ድህነት የመግባት ስጋት ውስጥ ላሉ ሰዎች ነው፤ ስለዚህ ይሄ አዲስ የገንዘብ ጫና ባዶ እጃቸውን በባሕር የሚመጡ ሰዎች ላይ የሚያመጣው ጉዳት ብቻ ነው" ሲሉም ተችተዋል።














