ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአዲስ አበባ ትናንት እኩለ ሌሊት ላይ ፍንዳታ መሰማቱን ነዋሪዎች ተናገሩ
በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ እና ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሦስት ግለሰቦች ትናንት ሌሊት ከ6 ሰዓት በኋላ ከባድ ፍንዳታ መስማታቸውን ተናገሩ።
ሮይተርስ የዜና ወኪል በበኩሉ የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ በአዲስ አበባ ረቡዕ እኩለ ሌሊት ፍንዳታ መሰማቱን ዘግቧል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና በጎተራ እና በቤተል አካባቢ የሚኖሩ ግለሰቦች ፍንዳታውን የሰሙት ከእኩለ ሌሊት 6፡20 በኋላ መሆኑን ተናግረዋል።
በጎተራ አካባቢ የሚኖሩ እና ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ነዋሪ ሌሊት 6፡20 ላይ ቁጭ ብው እየሰሩ በነበረበት ሰዓት "የሚኖሩበትን ሕንጻ የነቀነቀ ከባድ ፍንዳታ" መስማታቸውን ተናግረዋል።
"ፍንዳታው ከባድ ነበር፤ የመኪናዎች አላርም እንዲጮህ ሁሉ አድርጓል" ያሉት እኚህ ነዋሪ፣ ፍንዳታውን የሰሙት በግምት ከሌሊቱ 6፡20 እስከ 6፡30 እንደሚሆን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የተፈጠረውን ለማጣራት ከቤታቸው መውጣታቸውን የተናገሩት ግለሰቡ የተለየ እንቅስቃሴ አለማየታቸውን ገልጸዋል።
ፍንዳታው ከጦር ኃይሎች አቅጣጫ ይሁን ከአራተኛ ክፍለ ጦር ግን ለማጣራት ያደረጉት ሙከራም አልተሳካም።
ቤተል አካባቢ 'ጌም እየተጫወትን' ነበር ያለ ሌላ ወጣት በበኩሉ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት እርሱ እና ጓደኞቹ ፍንዳታ መስማታቸውን እና ለመኖሪያ አካባቢያቸው ስለሚቀርብ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዋና ቢሮ ከሚገኝበት፣ ጦር ኃይሎች አካባቢ ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል።
ቢቢሲ ለኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል፣ እንዲሁም ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በስልክ እና በኢሜይል ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ አላገኘም።
የፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ሕዝብ ግንኙነቶች በበኩላቸው ጉዳዮ እነርሱን እንደማይመለከት በመግለጽ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ቢቢሲ ስለፍንዳታው እንዲሁም የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ከገለልተኛ ወገን ለማጣራት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ፍንዳታው የተከሰተው አንድ ጊዜ ብቻ ይሁን ወይም ከዚያ በላይ ማረጋገጥ አልቻሉም።
ፍንዳታው መድረሱ የተሰማው የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት በአዲስ አበባ እና አካባቢው ከረቡዕ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ማንኛውንም ድሮን ለማብረር ፈቃድ እንደማይሰጥ ካስታወቀ በኋላ ነው።
ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት መስከረም 20፣ 2019 ዓ. ም. በማኅበራዊ ድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ የተሰጠውን ማሳሰቢያ በመጣስ "የሚነሱ እንዲሁም በየትኛውም አካባቢ እና ከፍታ የሚበሩ ድሮኖችን በመለየት፣ በመጥለፍ እና ወደ አስፈላጊው ቦታ በማሳረፍ እንዲሁም የአብራሪዎቹን ትክክለኛ መገኛ ቦታ በመለየት እና በቁጥጥር ሥር በማዋል ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል" ብሏል።
ባለፈው ሳምንት ሰባት ታጣቂ ቡድኖች ጥምረት መመስረታቸውን ካስታወቁ በኋላ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተቀሰቀሰ ሲሆን በተለያዩ አካባቢዎች ውጊያዎች እየተደረጉ ነው።
በዚህ ግጭት ውስጥ የኤርትራ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ በመግባት በቀጥታ መሳተፉን የአፋር ክልላዊ መንግሥት እና ከፌደራል መንግሥቱ ጎን በመሆን እየተዋጋ የሚገኘው የትግራይ የሰላም ኃይል የተባለው ታጣቂ ቡድን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኤርትራ መንግሥት ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ግን ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ በመንግሥታቸው ላይ የቀረበውን ክስ አስተባብለዋል።
የትግራይ የሰላም ኃይል ምክትል አዛዥ የሆኑት ኮሎኔል በርኸ ባራኺ (ወዲ ራያ) "የሜካናይዝድ የውጊያ ድጋፍ የሚሰጥ ኃይል አለ። . . . ሌላኛው ደግሞ ከአፋሩ ኡጉጉሙ ኃይል ጋር የተቀላቀለ ከሻዕቢያ [ከኤርትራ] ጋር የሚተባበር እና የሚመሩ ኃይሎች አሉ" ብለዋል።
የኤርትራ መንግሥት ማስታወቂያ ሚኒስትር ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ " የብልጽግና መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ እየተፈጠሩ ካሉት በርካታ ግጭቶች ላይ ትኩረት ለማስቀየር ጎረቤት አገራትን መወንጀል ልማዱ ሆኗል" በማለት የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።
በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች ከዚህ በፊት ድሮኖችን እንደሚጠቀሙ የሚታወቅ ነገር የለም፤ ነገር ግን ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ የሚወጡ የተለያዩ ዘገባዎች የመጠቀም አቅም እንዳላቸው የሚያሳዩ ናቸው።
ማክሰኞ ዕለት ከመንግሥት ጎን ተሰልፈው የሚዋጉት ታጣቂ ቡድኖች የህወሓት ንብረት ነው ያሉትን የድሮን ባትሪዎች መማረካቸውን ገልጸዋል።
ቢቢሲ ታጣቂ ቡድኖቹ ማረክን ያሉትን የድሮን መለዋወጫዎች በገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።
በአደጋዎች ላይ ትንተና በሚያቀርበው 'ቬሪስክ ሜፕልክሮፍት' ኩባንያ የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ተንታኝ የሆኑት ኤድዋርድ ባክ፣ የተቃዋሚ ኃይሎች በአዲስ አበባ ላይ ጥቃት የመፈጸም አቅም ማዳበራቸው "የፖለቲካ ሁኔታውን በእጅጉ የሚቀይር ክስተት" እንደሚሆን ለሮይተርስ ገልጸዋል።
ይህ ሁኔታ ዋና ከተማዋ ከጦርነቱ ተጽዕኖ ውጭ ናት የሚለውን የመንግሥት አቋም የሚያዳክም ከመሆኑም በላይ፣ የፌዴራል ኃይሎች የነበራቸውን ወሳኝ የአየር ላይ የበላይነታቸውን ይገድባል ሲሉ ተናግረዋል።
ለሁለት ዓመት የተካሄደው እና በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ከተቋጨ በኋላ ለአራት ዓመታት አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖ ነበር።
የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ አመራሮች በየጊዜው በሚያወጧቸው መግለጫዎች መካረራቸው ሲባባስ ግን በመቀለ እና በሌሎች የትግራይ አካባቢዎች የድሮን ጥቃቶች መፈጸማቸው ተዘግቧል።
ባለፈው ሳምንት ህወሓት ከስድስት ታጣቂ ቡድኖች ጋር በመሆን "ትብብር ለኅልውና" የተሰኘ ጥምረት መመስረቱን ይፋ ካደረገ በኋላም በአፋር እና አማራ አዋሳኝ አካባቢዎች ጦርነት ተቀስቅሷል።
በትግራይ ክልል የኢትዮ ቴሌኮም የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል።
የፌደራል ኃይሎች በደቡብ ትግራይ የሚገኙ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸውን ሲገልጹ የህወሓት ታጣቂዎች እና አጋሮቻቸው ደግሞ የአፋር ክልል ከተሞችን በእጃቸው ማስገባታቸው ተሰምቷል።
የህዋሓት ኃይሎች በተቆጣጠሯቸው የአፋር ከተሞች በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የሰብዓዊ ድርጅቶች ገልጸዋል።
የአፋር ክልል መንግሥት በትግራይ ክልል አዋሳኝ የሚገኙትን ኤርበቲ እና አብዓላ ከተሞችን መልሰው በቁጥጥራቸው ስር ማስገባቱን ገልጿል።
ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ግጭቱ መቀስቀሱ እንዳሳሰባቸው በመግለጽ በውይይት እንዲፈታ ጥሪ እያቀረበ ነው።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማሕሙድ አሊ ዩሱፍ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ውጥረት እና ወታደራዊ መካረር "እጅግ እንዳሳሰባቸው" ገልጸው፤ ግጭቱ "በአፋጣኝ እንዲቆም" አሳስበዋል።