ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለመጀመርያ ጊዜ በሰሜን ወሎ በኩል የተከፈተበትን ጥቃት መመከቱን ተናገረ
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ህወሓት ማክሰኞ መስከረም 12/2019 ዓ.ም. በይዞታ ቀጣናው ላይ የከፈተውን ጥቃት ማክሸፉን አስታወቀ።
ሠራዊቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ባጋራው መረጃ እንዳለው ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ ከሌሊቱ 9 ሰዓት ጀምሮ የህወሓት ታጣቂዎች በሰሜን ምሥራቅ ዕዝ የግዳጅ ቀጣና ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።
የሰሜን ምሥራቅ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀነራል አሰፋ ቸኮልን የጠቀሰው መረጃ "ህወሓት እና መሰል ተጣማሪ ቡድኖች በቀጣናው ሰብረው ለመግባት" ሙከራ ማድረጋቸውን እና መክሸፉን አመልክቷል።
ጥቃቱ በሰሜን ወሎ ዞን ተኩለሽ፣ ድልድይ፣ ቀይ አፈር፣ በረሃ ማርያም፣ ባይብዋ፣ በጭሮ እና ኩቤ ቀረንሳ በሚባሉ አካባቢዎች በኩል መሞከሩን ገልጿል።
ይህ ሠራዊቱ ያጋራው መረጃ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ ከተለያዩ ወገኖች መግለጫ እና ዘገባ ሲወጣ ቆይቶ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ምንም ሳይባል ከቆየ በኋላ ነው።
ረቡዕ ዕለት ክልሉን እያስተዳደረ የሚገኘው የህወሓት ታጣቂዎች በመቀለ፣ አክሱም እና ሽረ የሚገኙትን ሦስት አውሮፕላን ማረፊያዎች ተቆጣጥረዋል።
ህወሓት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ስላወጣው መረጃ ያለው ነገር የለም። ቢቢሲም ከትግራይም ሆነ በአካባቢው እየተካሄዱ ስላሉ ውጊያዎች እና የድሮን ጥቃቶች የሚወጡ ዘገባዎችን ማረጋገት አልቻለም።
የህወሓት ኃይሎች በአፋር እና በአማራ ክልሎች በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ጥቃት መክፈታቸውን የሚገልጹ ያልተረጋገጡ ዘገባዎች ተሰምተዋል።
ኤኤፍፒ የዜና ወኪል በአፋር ክልል የሚንቀሳቀስ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ምንጭን ጠቅሶ ሐሙስ ዕለት የትግራይ ኃይሎች በክልሉ ድንበር አቅራቢያ የምትገኘውን የያሎን ከተማ ለመቆጣጠር ከባድ የጦር መሳሪያ ጥቃቶችን መክፈታቸውን ዘግቧል።
ለዜና ወኪሉ "አሁን ሙሉ በሙሉ ጦርነት ውስጥ ነን" ሲሉ የህወሓት ምክትል ፕሬዝዳንት አማኑኤል አሰፋ ተናግረው ነበር።
በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት የተቀሰቀሰው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር እና የህወሓት ባለሥልጣናት ለወራት ባለመግባባት እና መካሰስ ውስጥ ከቆዩ በኋላ ነው።
ለሁለት ዓመት የተካሄደው ደም አፈሳሽ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢቋጭም ከቅርብ ወራት ወዲህ ግን የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት አንዳቸው ሌላኛቸው ስምምነቱን በመጣስ ሲካሰሱ ተደምጠዋል።
በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት ጦርነቱ ሲቋጭ ወደ 600,000 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።
እሁድ ዕለት ህወሓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን መንግሥትን ለመጣል ከሌሎች ስድስት የታጠቁ ቡድኖች ጋር ጥምረት መመስረቱን አስታውቋል።
ረቡዕ ዕለት ማለዳ በክልሉ የሚገኙ ሦስት አውሮፕላን ማረፊያዎች በህወሓት ወታደሮች ቁጥጥር ስር መግባታቸው ከተሰማ በኋላ በረራዎች ተቋርጠዋል።
በመቀለ የሚገኙ ነዋሪዎች ረቡዕ ዕለት የህወሓት ታጣቂዎች በከተማዋ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መቆጣጠራቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በክልሉ ከነሐሴ ወር መጀመርያ ጀምሮ የድሮን ድብደባዎች ሲፈጸሙ ነበር።
የመቀለ ከተማ ነዋሪ ቢቢሲ ኒውስዴይ ፕሮግራም በዋና ከተማዋ ምንም ዓይነት ግጭት አለመኖሩን ተናግረዋል።
ለደኅንነታቸው ሲባል ፍጹም ተብለው የተጠቀሱት ነዋሪ "በሕዝቡ ውስጥ ካለው ጭንቀት በስተቀር መቀለ ሰላማዊ ናት" ሲሉ ተናግረዋል። ዋናው ችግር ኢኮኖሚያዊ እንደሆነና ሕዝቡ በቂ ጥሬ ገንዘብ እንደሌለውም አክለዋል።
"ሁኔታው እጅግ አስቸጋሪና ከባድ በመሆኑ ሕዝቡ በጭንቀት ውስጥ ይገኛል። ባለፉት ሰባት ወይም ስምንት ወራት መንግሥት ለሠራተኞች በጀት አልለቀቀም፤ እንዲሁም በሁሉም ባንኮች ውስጥ የነበረው ጥሬ ገንዘብ እያለቀ ነበር።"
ፍጹም ሰዎች በሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ላይ ጥገኛ መሆናቸውን አስረድቶ ነገር ግን የመገናኛ መስመሮች የመቋረጥ ስጋት ስላለ እና "በእጅ ላይ ጥሬ ገንዘብ ፈጽሞ ስለሌለ" ነዋሪዎች ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ይወድቃሉ ብሏል።
ጦርነቱ በመጀመሩ ነዋሪዎች እንቅስቃሴያቸውን ቀንሰዋል፤ ከተማዋም ሙሉ በሙሉ ጸጥ ብላለች "ልክ የሰዓት እላፊ የእንቅስቃሴ ገደብ የተጣለባት ያህል ነው" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።