ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኔታንያሁ ከዱባይ ወደ ቴል አቪቭ በነበረው በረራ ላይ ጥቃት የተሰነዘረበትን ምክንያት ለማወቅ ጊዜው ገና ነው አሉ
ከዱባይ ወደ ቴል አቪቭ በነበረው በረራ ላይ ጥቃት ስለተከሰተበት ምክንያት ለመናገር "ጊዜው ገና ነው "ሲሉ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናገሩ።
ኔታንያሁ ኢራን በጉዳዩ ውስጥ ተሳትፎ እንዳላት ፍንጭ አለ ወይ ተብለው በፎክስ ኒውስ ለቀረበላቸው ጥያቄ "ለመናገር ጊዜው ገና ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በበረራው ወቅት አንደኛው አብራሪ ሌላኛውን በስለት ከወጋ በኋላ በእስር ላይ እንደሚገኝ የገለፁት ኔታንያሁ ይኸው አብራሪ "አውሮፕላኑን ለመከስከስ ሞክሮ ሊሆን ይችላል" ብለዋል።
ተሳፋሪዎችና የበረራ ሠራተኞች አጥቂውን በመቆጣጠር የአውሮፕላኑን ደህንነት መልሰዋል።
አውሮፕላኑ በሳዑዲ አረቢያ ታቡክ አየር ማረፊያ በሰላም ሲያርፍ፣ ጥቃቱን የፈጸመው አብራሪ በቁጥጥር ሥር ውሏል።
ኔታንያሁ አብራሪው አውሮፕላኑ በረራውን ወደ ጀመረበት የተባበሩት የአረብ ኤሚሬትስ ሊወሰድ እንደሚችል ጠቁመዋል።
በስለት የተወጋው አብራሪ የሕንድ ዜግነት ያለው ካፒቴን ስሚት ማችሃር ሲሆን፣ ሆስፒታል ገብቶ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል። ኔታንያሁ እና የሕንዱ ፕሬዚዳንት ናሬንድራ ሞዲ ዋና አብራሪውን "ጀግና" ብለው አወድሰዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር የሆኑት እስራኤል ካትዝ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም ክስተቱን "የጂሃዲስት የሽብር ጥቃት ሙከራ" ብለውታል።
በረራው 174 ሰዎችን ይዞ ከዱባይ ተነስቶ ወደ እስራኤል እየበረረ ነበር።
በሳዑዲ አረቢያ ላይ ከ17 ሺህ ጫማ በላይ በፍጥነት ወደታች ከወረደ በኋላ የአደጋና የጠለፋ ምልክቶችን አሳይቷል።
ሁሉም እስራኤላውያን የሆኑት ተሳፋሪዎች በኋላ ላይ በልዩ በረራ ወደ ቴል አቪቭ ተጉዘዋል።
አንዳንዶቹ ተሳፋሪዎች በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበረውን ክስተት "ከፍተኛ አሰቃቂ ሁኔታ" ሲሉ ገልጸዋል።
ከዱባይ ወደ ቴል አቪቭ እየተጓዘ በነበረ አውሮፕላን ላይ ፓይለቶች በመጣላታቸው በረራው ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንዲለወጥ ተደርጓል።
ከዱባይ የተነሳው የፍላይዱባይ አውሮፕላን በረራውን በጀመረ በሁለት ሰዓታት ውስጥ የድንገተኛ ጊዜ ምልክት ማሳየቱን በረራዎችን የሚከታተለው ፍላይትራዳር24 ድረ ገጽ ጠቁሟል።
ከሁለት ደቂቃ በኋላ ደግሞ አውሮፕላን ሲጠለፍ የሚሰጠውን ምልክት አውሮፕላኑ ማሳየት ጀምሯል።
ዋና አብራሪው እና ምክትሉ "መጋጨታቸውን" የእስራኤል መከላከያን ጠቅሰው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በኤፍዜድ1073 በረራ ላይ 174 ተሳፋሪዎች የነበሩ ሲሆን አብዛኞቹ እስራኤላውያን ናቸው።
ልጇ ሚርያም በረራው ላይ እንደነበረች የተናገረችው ያስሚን አቡካሲስ፣ ስለት የያዘ ግለሰብ ከፓይለቶቹ አንዱ መሬት ላይ እንዲወርድ እንዳስገደደው ገልጻለች። አውሮፕላኑ ውስጥ ደም ይታይ እንደነበርም ተናግራለች።
ጀሩሳሌም ፖስት ያነጋገረው ተጓዥ እንዳለው አንደኛው ፓይለት ሌላኛውን በስለት ወግቶታል። አውሮፕላኑ ፊት ወንበር ላይ ተቀምጠው የነበሩ ተሳፋሪዎች ጥቃት አድራሹን ከጀርባው እንዳነቁትም ተናግረዋል።
አውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ሌሎች ሁለት ፓይለቶች አውሮፕላኑን በማሳረፍ እንደተባበሩ ተገልጿል።