ዩናይትድ ኪንግደም በራፍ የጦር ሠፈር የጥቃት ሙከራ የኢራን እጅ እንዳለበት ገለጸች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም መንግሥታቸው፣ ኢራን በራፍ ፌርፎርድ የጦር ሠፈር በተፈጠረው ክስተት ውስጥ ሚና አላት ብሎ እንደሚያምን ገለጹ።

በራፍ የጦር ሠፈር ላይ የሽብር ድርጊት እና የፈንጅ ጥቃት ለመፈፀም በዝግጅት ላይ ነበሩ የተባሉ አምስት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል።

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሦስት አጠራጣሪ ተሽከርካሪዎች ወደ ራፍ የጦር ሠፈር አቅጣጫ ካመሩ በኋላ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።

እሑድ ዕለት ስለክስተቱ ዘገባ ከወጣ በኋላ በግላውሴስተርሻየር ዲስትሪክት፣ ራፍ ፌርፎርድ በተባለው የሮያል አየር ኃይል ጣቢያ አቅራቢያ ያሉ በርካታ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ተደርጎም ነበር።

እድሜያቸው ከ23 እስከ 25 የሆኑት ፣ የዩናይትድ ኪንግደም ዜግነት ያላቸው አምስቱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በዋስ እንደተለቀቁ ተገልጿል።

በርንሃም ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ "ኢራን በተፈጠረው ነገር ሚና እንዳላት ጠንካራ ምልክቶች አሉ" ብለዋል። ሆኖም ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ በበኩላቸው "የተሳሳተ አቅጣጫ እየተከተሉ ነው" በማለት ክሱን አጣጥለውታል።

በለንደን የሚገኘው የኢራን ኤምባሲም ኢራንን ከክስተቱ ጋር የሚያገናኙ ግምቶችን "መሠረተ ቢስ" ሲል አጣጥሏል።

ትራምፕ ሰኞ ዕለት በዋይት ሐውስ ሲናገሩ፣ "እኔ ብሆን ኖሮ 'ዋስትና እንዲሰጣቸው አትፍቀዱ' እል ነበር። እንዲለቀቁ መደረጋቸው አስገርሞኛል። እኔ ብሆን እንዲህ አላደርግም ነበር" ብለዋል።

በርንሃም ግን፣ "ሰዎች 'ተለቀቁ' ሲባል እንደሚታሰበው ቀላል እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል። ጥብቅ በሆኑ የዋስትና ሁኔታዎች ስር መሆናቸው ግልጽ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ሰኞ ዕለት ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ "ይህ የሚያሳየን እውነታውን እንድንጋፈጥ ነው። እየተጋፈጥን ያለነው በዓለም ላይ ያሉ እና በተለይም ኢራንን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የአሜሪካን ጥቅሞች ለማጥቃት በግልጽ የዛቱ አካላትን ነው" ብለዋል።

በርንሃም ክስተቱ ምርመራ ላይ መሆኑን አንስተው ዩናይትድ ኪንግደም ከአሜሪካ ጋር በቅርበት እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የደኅንነት አገልግሎቶች ጉዳዩን በያዙበት መንገድም "ሙሉ እምነት" እንዳላቸው ተናግረዋል።

"በተገቢው ጊዜ ተጨማሪ መረጃ እንሰጣለን፤ ነገር ግን ኢራን በዚህ ጉዳይ ላይ ድርሻ እንዳላት እናምናለን ብለን ማረጋገጥ እንችላለን" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የበርንሃም አስተያየት የተሰማው፣ ከታሰሩት አምስት ሰዎች አንዱ የአደጋ ጊዜ መጥሪያ ወደሆነው 999 ደውሎ እንደነበር ከተገለጸ በኋላ ነው።

በተሽከርካሪዎቹ ላይ በተደረገው ፍተሻም የተወሰነ መጠን ያለው ቤንዚን ቢገኝም፣ ፈንጂ መሣሪያ እንዳልተገኘ ፖሊስ አስታውቋል።

ራፍ ፌርፎርድ ለአሜሪካ አየር ኃይል ወሳኝ የሆነ ቦታ ሲሆን፣ በቅርብ ወራት የአሜሪካ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ከዚህ የጦር ሰፈር ተነስተው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ተንቀሳቅሰዋል ተብሏል።

ኢራን በበኩሏ የጦር ሰፈሩ በኢራን ላይ ጥቃት ለማድረስ ከዋለ ለጥቃት ሕጋዊ ዒላማ እንደሚሆን ቀደም ሲል አስጠንቅቃ ነበር።