ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በድጋሚ የተሾሙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር " ግጭት እንዲቆም እና ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ" ጥሪ አቀረቡ
በድጋሚ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተሾሙት አቶ አረጋ ከበደ በክልሉ የሚካሄዱ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥሪ አቀረቡ።
አቶ አረጋ ጥሪውን ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዛሬ መስከረም 21፣ 2019 ዓ.ም. ባካሄደው የመስራቾች ጉባዔ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ከተሾሙ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት ነው።
በዚህ ንግግራቸውም "በክልሉ የሚካሄደው ግጭት እና ደም መፋሰስ በአስቸኳይ እንዲቆም እና ችግሮች በውይይት እና በሰለጠነ መንገድ እንዲፈቱ" በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጥሪ አቅርበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የአሁኑን የሰላም ጥሪያቸውን ያቀረቡት በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) ታጣቂ ቡድን ህወሓትን ጨምሮ ከሌሎች በአገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ ስድስት ቡድኖች ጋር ጥምረት መመስረቱን ካስታወቀ እና በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ነው።
ታጣቂ ቡድኖቹ "ትብብር ለኅልውና" በሚል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን አስተዳደር ለመጣል ያለመ ጥምረት መመስረታቸውን ያስታወቁት ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ትግራይን የሚያስተዳድረው ህወሓት ኃይሎች በክልሉ የሚገኙ ሦስት የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ከተቆጣጠሩ በኋላ ጦርነት ተቀስቅሷል::
ህወሓት እና የፌዴራል መንግሥቱ ጦርነቱን በመጀመር እርስ በእርስ ተወነጃጅለዋል።
አማራ ክልል ከዓመታት በፊት በትግራይ በተቀሰቀሰውና በፕሪቶሪያ ስምምነት በተቋጨው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት የደረሰበት ሲሆን ከጦርነቱ በኋላ የፌዴራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎች ፈርሰው በሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች እንዲዋቀሩ ማድረጉን ተከትሎ ዳግም ግጭት ውስጥ ገብቷል።
ክልሉ ላለፉት ሦስት ዓመታት በመንግሥት ኃይሎች በታጣቂዎች መካከል በሚካሄድ ግጭት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የትምህርት፣ የጤና ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያው ቀውሶች አጋጥመዋል።
አሁን የተቀሰቀሰው ጦርነትም ክልሉን ወደባሰ ቀውስ ይከተዋል የሚሉ ስጋቶችን ፈጥሯል።
በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆናቸው እየተዘገበ ሲሆን በታሪካዊቷ ላሊበላ ከተማ የሚደረግ የአውሮፕላን በረራ ከተቋረጠም ቀናት ተቆጥረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ሹመታቸውን ተከትሎ ባስተላለፉት መልዕክትም ክልሉ ላለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ማለፉን ጠቅሰው፣ ከዚህም "በጥላቻ እና በግጭት አሸናፊ አለመኖሩን" ትምህርት መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
"በጠመንጃ ድምጽ ፣ የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት መውደም እንዲሁም የሕዝብ መፈናቀል የትኛውንም ያህል ምክንያት ቢቀርብም እንኳን ዘላቂ መፍትሔ ነው ብለን አናምንም" ብለዋል።
ጨምረውም "ግጭት ተስፋን የሚያስቆርጥ፣ የእድገት እና የመለወጥ እድልን የሚዘጋ የእናቶችን ጉልበት በሃዘን የሚያርድ ብሎም የክልሉን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሠረት የሚያፈርስ መሆኑን እንገነዘባለን" ሲሉ ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ እና ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ አረጋ በንግግራቸው ታጣቂዎች "ለአገራችን እና ለክልላችን ጠላት የሆኑ" ካሏቸው አካላት ጋር መተባበራቸው "በታሪክ ፊት የሚያዋርድ ነው" ሲሉም በማሳሰብ ታጣቂዎቹ ቆም ብለው እንዲያስቡበት መክረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ "ጠላት" ሲሉ የገለጿቸውን ኃይሎች በስም አልጠቀሱም።
"በውስጣችሁ ቅሬታዎች እና ጥያቄዎች ቢኖራችሁ እንኳን ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኘው በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ውይይት ነው ብለን እናምናለን" ሲሉም አክለዋል።
ወጣቶች ሰላባ መሆን እንደሌለባቸው በመጥቀስም በግጭቱ ከመሳተፍ እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።
አቶ አረጋ ከበደ በመጭው የሥልጣን ዘመናቸው በክልሉ ሰላም እና የፖለቲካ መረጋጋት እንዲመጣ ጠንክረው ለመስራት ቃል ገብተዋል።