ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአፋር ክልል የኤርትራ ወታደሮች ድንበር አልፈው በመግባት ውጊያ ከፍተዋል ሲል ከሰሰ
የአፋር ክልል መንግሥት የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያ ድንበርን አልፈው በመግባት ከህወሓት ታጣቂዎች ጎን ተሰልፈው እየተዋጉ ነው ሲል ለቢቢሲ ተናገረ።
የኤርትራ መንግሥት ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ በመንግሥታቸው ላይ የሚቀርበውን ክስ አስተባብለዋል።
የኤርትራ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ ስለመግባቱ እና እየተደረገ ባለው ጦርነት ላይ በቀጥታ ስለመሳተፉ የፌደራል መንግሥቱ እስካሁን ድረስ ያለው ነገር የለም።
የአፋር ክልል ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ መሃመድ አሊ ለቢቢሲ በክልሉ እየተዋጉ ነው ያሏቸው የኤርትራ ወታደሮች እንዲሁም ወታደራዊ ቁሳቁሶች መማረካቸውን ጨምረው አስታውቀዋል።
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ለቢቢሲ ትግርኛ በሰጡት ምላሽ "የብልጽግና መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ እየተፈጠሩ ካሉት በርካታ ግጭቶች ላይ ትኩረት ለማስቀየር ጎረቤት አገራትን መወንጀል ልማዱ ሆኗል" በማለት የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በዚህ ሳምንት ለአልጀዚራ በሰጡት መግለጫ የኤርትራ ጦር በክልሉ ላይ ቀጥተኛ ወታደራዊ ጥቃት እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ኤታማዦር ሹሙ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "እየተዋጋን ያለነው የውጪ ኃይሎችን ፍላጎት ለማስፈጸም ከተሰባሰቡ እና ከተደራጁ ኃይሎች ጋር ነው" ብለው ነበር።
አክለውም "ሻዕቢያ [ኤርትራ] እና ቲፒኤልኤፍ [ህወሓት] ያለ ሱዳን፣ ያለ ግብፅ እና ከዚያም ባሻገር ያሉ ኃይሎች ካልደገፏቸው ብቻቸውን ተጣምረውም ቢሆን ዋጋ የላቸውም። ሲነጣጠሉ ደግሞ ትርጉም የላቸውም" ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የኤርትራ፣ የሱዳን እና የግብፅ መንግሥታት የኢትዮጵያ አማፂያንን ያስታጥቃሉ የሚለውን ውንጀላ አስተባብለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተቀሰቀሰው ህወሓትን ጨምሮ ሰባት አማፂያን "ትብብር ለኅልውና" የሚል ጥምረት መመስረታቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ ነው።
የጥምረቱን ይፋ መሆን ተከትሎ የተለያዩ ወገኖች ድጋፍ እና ተቃውሞ ሲያሰሙ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቃል አቀባይ ቢለኔ ስዩም ቡድኖቹ ከኤርትራ ድጋፍ የሚያገኙ መሆናቸውን እና ይፋ መሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ሲል የነበረውን የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ ለሮይተርስ ገልጸዋል።
ከ2012 እስከ 2014 ዓ.ም. በተካሔደ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የኤርትራ መንግሥት ከፌደራል መንግሥት ወግኖ ተሰልፎ ነበር።
የኤርትራ እና ኢትዮጵያ መንግሥት ግንኙነት መሻከር የጀመረው የሁለት ዓመቱን ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ሥምምነት ከተፈረመ በኋላ ነበር።
ከዚያ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል የባሕር በር ልታገኝ ይገባል የሚለውን አቋማቸውን በይፋ መግለጻቸውን ተከትሎ የአገራቱን ግንኙነት አካርሮታል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአፋር ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ የኤርትራ ወታደሮች ድንበር አልፈው ከህወሓት ታጣቂዎች ጋር በመሆን በክልሉ የተለያዩ ከተሞች እየተዋጉ ነው ብለዋል።
ኃላፊው በአሁኑ ወቅት የክልሉ ፀጥታ ኃይሎች ከመከላከያ ጋር በመሆን እየተዋጉ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
"ሻዕቢያ [ኤርትራ] የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ በአፋር ክልል አብዓላ መጋሌ፣ ወሰመና እና ኤረብቲ ላይ ጦርነት ከፍቷል።"
የኮሚኒኬሽን ኃላፊው የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው "እየወጉን ነው" ካሉ በኋላ፣ የኤርትራ ጦር አዛዦች በተለያየ ግንባር በመሆን ጦርነቱን እየመሩ ናቸው ሲሉም ከስሰዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የኤርትራን ድርጊት እንዲያወግዝ የጠየቁት የአፋር ክልል ኮሚኒኬሽን ኃላፊ "የአፋር ሕዝብም እና የአፋር የፀጥታ ኃይልም ይህንን ጦርነት ለመመከት ከሻዕቢያ መንግሥት [ከኤርትራ] ጋር ነው እየተዋጋን ያለነው" ብለዋል።
የኮሚኒኬሽን ኃላፊው የኤርትራ ጦር ከህወሓት ታጣቂዎች ጋር በመሆን እየተዋጋ ስለመሆኑ ሲያስረዱ "የተማረኩ ወታደሮች አሉ፤ የእነሱ [ኤርትራ ጦር] ወታደራዊ መሣሪያዎችም የተማረኩ ስላሉ ነው" በማለት ማስረጃ አለን ብለዋል።
"ክልሉ የተከፈተበትን ጦርነት የመመከት እና አጸፋ ምላሽ በመውሰድ ላይ ነው" ያሉት ኃላፊው የፌደራል መንግሥቱ ከክልሉ ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በኒው ዮርክ በተካሄደው ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ "የውጭ ጣልቃ ገብነቶች" ቢኖሩም እንኳን "በከፍተኛ ሁኔታ ተቆጥባ" እንደቆየች እና ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት "እንዳሻሻለች" ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን የተናገሩት በፌደራል ኃይሎች እና በትግራይ ታጣቂዎች መካከል ግጭት እንደ አዲስ በተቀሰቀሰ በጥቂት ቀናት ውስጥ ነው።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ማህሙድ አሊ ይሱፍ ሁሉም የኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች "ውጥረቱን የበለጠ ሊያባብሱ ከሚችሉ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ" አሳስበዋል።