ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በኢቦላ ወረርሽኝ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 131 ደረሰ
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተቀሰቀሰ የኢቦላ በሽታ ቢያንስ 131 ሰዎች መሞታቸው እና ከ513 በላይ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል ተብለው መጠርጠራቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
ከሞት ቁጥሩ በተጨማሪ የአገሪቱ መንግሥት ቃል አቀባይ ተጠርጣሪዎች የሚገኙበት አካባቢ መስፋቱን ተናግረዋል።
በኡጋንዳም ሁለት የተረጋገጡ ኬዞች እና አንድ ሞት መመዝገቡን የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከል ማዕከል (ሲዲሲ) ገልጿል።
የዓለም ጤና ድርጅት ከባንዲቡግዮ ቫይረስ የሚነሳውን የአሁኑን የኢቦላ የዝርያ ዓይነት ዓለም አቀፍ ድንገተኛ አደጋ ነው ሲል አውጆታል።
ይህ አስከፊ የኢቦላ ቫይረስ እየተሰራጨ ሲቀጥል፤ የኮንጎ መንግሥት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ቡድን ቫይረሱ የተነሳበትን ስፍራ ለማወቅ እና ለመመርመር ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀው መረበሽ እንደማያስፈልግ ተናግረዋል።
ሆኖም ግን አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች እንደ ኢቱሪ ግዛት፣ በሰሜን ቡቴምቦ እና የጎማ ከተማ አካባቢዎች በመገኘታቸው የነዋሪዎች ጭንቀት እየጨመረ መጥቷል።
በኮንጎ ከሲዲሲ ጋር ሲሰሩ የነበሩ አንድ አሜሪካዊ ሐኪም በቫይረሱ ተይዘዋል ተብለው ከተረጋገጡት ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።
ዶክተሩ ለሕክምና ወደ ጀርመን እንደሚወሰዱ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘግቧል።
ምንም እንኳ ሲዲሲ በኮንጎ ይሰራ የነበውን አሜሪካዊ ሐኪም ስም ባይጠቀስም፤ የሚሲዮናዊ የሕክምና ግብረ ሰናይ ድርጅት፣ ሰርጅ ግን ከአሜሪካ የመጣው ሐኪም ፒተር ስታፎርድ በኢቦላ መያዙን አረጋግጧል።
የቡድኑ ሌሎች ሁለት ሐኪሞች ታካሚዎችን ሲያክሙ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ምንም ምልክት እንዳልታየባቸው እና የለይቶ ማቆያ መመሪያዎችን እየከተሉ እንዳሉ ድርጅቱ ገልጿል።
ሲቢኤስ ኒውስ ቢያንስ ስድስት አሜሪካዊያን በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኢቦላ ዳግም መቀስቀሱን ተከትሎ በቫይረሱ መጋለጣቸውን ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
ሲዲሲ በቀጥታ የተጋለጡ ጥቂት አሜሪካዊያንን "በደኅንነት ለማውጣት" እየደገፈ እንደሆነ ገልጿል፤ ቁጥራቸውን ምን ያህል እንደሆነ ግን ከመግለፅ ተቆጥቧል።
የዓለም የጤና ድርጅት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምሥራቃዊ ኢቱሪ ግዛት ውስጥ የተቀሰቀሰው በሽታ የዓለም የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ነው ያለ ሲሆን፤ ነገር ግን ወረርሽኝ ተብሎ ለመጠራት የሚያስፈልጉትን መመዘኛዎች ለማሟላት አልደረሰም ብሏል።
ድርጅቱ ግን አሁን እየተመዘገበ እና እየተገኘ ካለው በላይ "በጣም ትልቅ የሆነ የመስፋፋት ሁኔታ" ሊኖር እንደሚችል አስጠንቅቋል። በአካባቢያዊ እና በቀጣናዊ ደረጃ የመስፋፋት ከፍተኛ አደጋ እንዳለ ጠቁሟል።
እአአ ከ2014 እስከ 2016 ባሉት ዓመታት ኢቦላ በምዕራብ አፍሪካ ተከስቶ በታሪኩ ከከተገኘበት 1976 ጀምሮ ከተመዘገበው በበለጠ ከ28,600 በላይ ሰዎች ተይዘዋል።
ይህ በሽታ በምዕራብ አፍሪካ ውስጥ እና ውጭ ባሉ በርካታ አገራት እንዲሁም በጊኒ፣ ሴራ ሊዮን፣ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ጣሊያንን ተዳርሶ 11,325 ሰዎችን ገድሏል።