ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ድምፄን የምትሰሙት ለመጨረሻ ጊዜ ሊሆን ይችላል": ከጦርነቱ ወዲህ እየተባባሰ የመጣው የኢራን ፖለቲካዊ ሞት ቅጣት
መስመሩ ይቆራረጣል፤ የመህራብ አብዶላህዛዴህ ድምጽ ግን ጥርት ያለ ነው። ካለበት ሁኔታ አንጻር ደግሞ በአስገራሚ ሁኔታ ድምጹ መረጋጋት ይታይበታል።
ምዕራብ ኢራን ውስጥ የሞት ቅጣቱ እስከሚፈጸም እየተጠባበቀ ነው። የሚናገረው ቶሎ ቶሎ ነው፤ ጊዜው እያለቀበት እንደሆነ ሁሉ። የሚያስተላልፈው መልዕክት ተስፋ መቁረጥ ያጀበው ነው።
"ድምፄን እየሰማችሁ ያላችሁት ከኦሮሚየህ ማዕከላዊ ማረሚያ ነው፤ ምናልባትም ድምፄን የምትሰሙት ለመጨረሻው ጊዜ ሊሆን ይችላል" ይላል በ'ኩርዲስታን ሂውማን ራይትስ ኔትዎርክ' በኩል የወጣው የድምፅ መልዕክቱ።
"ከታሰርኩባት የመጀመሪያዋ ዕለት አንስቶ በስቅይት እና ዛቻ እንድናዘዝ አስገድደውኛል፤ የሰጠሁት ቃል ሙሉ በሙሉ ውሸት ነው። የቀረቡብኝ አንዳቸውም ክሶች እውነተኛ አይደሉም። እነሱ ያውቁታል፤ ፈጣሪም ያውቀዋል። ንጹህ ሰው ነኝ" ሲል በተማጽኖ ያስረዳል።
መህራብ በአውሮፓውያኑ 2022 የታሰረው ማሻ አሚኒ የተባለች ወጣት ሴት ሂጃብ በአግባቡ አልለበሽም በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሏን ተከትሎ አገር አቀፍ ተቃውሞ በተቀሰቀሰበት ወቅት ነበር። የኢራን ባሲጅ ሚሊሻ ኃይል አባል የሆነ ግለሰብ ግድያ ላይ ተሳትፎ እንዳለው የሚገልጽ ክስ ቀርቦበታል።
ከ42 ወራት ፍርሃት የነገሰባቸው እና እንቅልፍ የለሽ ምሽቶች በኋላ በሚያዝያ መጨረሻ የሞት ቅጣቱ ተፈጽሞበታል።
ኢራን ውስጥ ከፖለቲካ እና ከደኅንነት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ክስ የተፈረደቸባቸው ሰዎች ላይ የሚፈጸመው የሞት ቅጣት እየጨመረ መጥቷል።
አሜሪካ እና እስራኤል በየካቲት ወር ኢራን ላይ ጥቃት ከከፈቱ ጊዜ አንስቶ ቢያንስ 32 የፖለቲካ እስረኞች እንደተገደሉ መረጋገጡን የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል።
ይህ ቁጥር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚፈጸመው ግድያ በከፍተኛ መጠን መጨመሩን ያሳያል። በ2025 ዓመቱን ሙሉ በፖለቲካዊ ክሶች ተፈርዶባቸው የተገደሉ ሰዎች ብዛት 45 እንደነበር የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል መረጃ ያሳያል።
የተባበሩት መንግሥታ የሰብአዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት በበኩሉ የሞት ቅጣት የጨመረው ፖለቲካዊ ተቃውሞዎችን ለማፈን እንደሆነ አስጠንቅቋል።
በዚህ ዓመት ከተገደሉት ውስጥ በርካታዎች ለእስራኤል ወይም ለሲአይኤ ትሰልላላችሁ የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። የተወሰኑት ደግሞ ስደት ላይ ካሉ ተቃዋሚ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል ተከስሰዋል።
ከተገደሉት ውስጥ 14 ያህሉ የታሰሩት ባለፈው ጥር ላይ ከተከሰተው እና መንግሥት በወሰደው እርምጃ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከተገደሉበት ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ነው።
በአምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢራን ጉዳዮች ላይ የሚሰሩት ናሲም ፓፓያኒ፤ "ኢራን ውስጥ ባለሥልጣናት ግድያ የሚፈጽሙት በስቅላት ነው። የሚፈጽሙትም ንጋት ላይ ነው" ይላሉ። "ኢራን ውስጥ ሰዎች በየቀኑ በሚባል ደረጃ ከእንቅልፋቸው የሚነቁት በሞት ቅጣት ዜና ነው" ሲሉም ይናገራሉ።
ከሚፈጸሙት የሞት ቅጣቶች ውስጥ አንዳንዶቹ በይፋ የሚገለጹ ቢሆንም ሌሎች ግድያዎች በምስጢር እየተፈጸሙ ነው የሚል ስጋት መኖሩን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኢራን መንግሥት ባለፈው ዓመት 2,159 የሞት ቅጣቶችን የፈጸመ ሲሆን ይህ ቁጥር ከአውሮፓውያኑ 1989 ወዲህ ከፍተኛው እንደሆነ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገልጿል። እንደ አምነስቲ ገለጻ አብዛኞቹ ቅጣቶች ከአደንዛዥ ዕፅ ወይም ሕይወት ማጥፋት ወንጀሎች ጋር የተያያዙ ናቸው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዚህ ዓመት ቁጥሩ ከዚህም ሊበልጥ ይችላል የሚል ስጋት አለው።
በ 'ኩርዲስታን ሂውማን ራይትስ ኔትዎርክ' የሚሰሩት ካቬህ ኬርማንሻሂ እንደሚናገሩት፤ በጥር ወሩ ተቃውሞ እና በጦርነቱ ምክንያት ገጽታው የጠለሸው የኢራን መንግሥት የሚፈጽማቸውን ሞት ቅጣቶች በመጨመር ሥልጣኑን ለመመለስ እየሞከረ ነው።
"በበርካታ የውስጥ እና የውጭ ቀውሶችን እየተጋፈጠ በሚገኝበት በዚህ ጊዜ፤ ጭቆናውን በማጠናከር እና የሞት ቅጣቶችን በመጨመር ኃይሉን የሚያሳይበት መድረክ ለመፍጠር እየሞከረ ነው" ብለዋል።
የአገሪቱ መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ባለፈው ወር መጨረሻ የኢስፋሃን ከተማ ነዋሪ በሆነው የ21 ዓመቱ የካራቴ ሻምፒዮን ሳሳን አዛድቫር ላይ የሞት ቅጣት ስለመፈጸሙ ዘግቧል። የ21 ዓመቱ ወጣት ከቀረቡበት ክሶች አንዱ "ሞሃራቤህ" ወይም "ፈጣሪ ላይ ጦርነት ማወጅ" የሚል ነው።
ጥር ላይ በተነሳው ተቃውሞ ወቅት የፖሊስ ኃይሎች ማጥቃት እንዲሁም "ከጠላት ጋር ውጤታማ ትብብር ማድረግ" የሚሉ ክሶች ቀርበውበትም ተፈርዶበታል። በቴሌቪዥን ጣቢያው የተላለፈው ቪዲዮው ላይ የፖሊስ መኪና መስኮትን በዱላ መስበሩን እና መኪናውን ለማቃጠል ነዳጅ መጠየቁን ሲያምን ይታያል።
ይሁን እንጂ ሳሳን አዛድቫር የቀረቡበት ክሶች የዓለም አቀፍ ሕግ በሚያስቀምጠው ደረጃ ሲታይ የሞት ፍርድ የሚያስፈርዱ አይደሉም።
ቢቢሲ፤ የኢራን ባለሥልጣናት የሚፈጽሙትን የሞት ቅጣት ስለመጨመራቸው እና ስለሚቀርብባቸው ስቅይት ይፈጸማል የሚል ክስ የሰሚጡትን አስተያየት ለማካተት ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ አላገኘም።
የኢራን ፍርድ ቤቶች ኃላፊ የሆኑት ጎላምሆሴን ሞህሴኒ ኤጂ ሚያዝያ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ ከጥር ወሩ ተቃውሞ ጋር ተያይዞ በተሰጡት የሞት ፍርዶች ላይ የቀረበውን ዓለም አቀፍ ትችት ውድቅ አድርገዋል። ኃላፊው የሚመሯቸው ፍርድ ቤቶች ሸብረክ እንደማይሉም ተናግረዋል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እጅግ የሚረብሽ አካሄድ እየታየ መሆኑን ይገልጻሉ። ባልተመጣጠነ ሁኔታ የሞት ፍርድ የሚተላለፈው በአገሪቱ ሕዳጣን ማኅበረሰቦች ላይ ነው።
የኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ የማስተርስ ተማሪ የነበረው የ29 ዓመቱ ኤርፋን ሻኩርዛዴህ ባለፈው ሳምንት በስቅላት ተቀጥቷል። የኢራን ፍርድ ቤት እንደሚናገረው፤ ኤርፋን ሻኩርዛዴህ የተፈረደበት ምስጢራዊ መረጃዎችን ለእስራኤል እና ለአሜሪካ የስለላ ድርጅቶች በማጋራት ወንጀል ነው።
በኖርዌይ የሚገኘው ሄንጋው የተሰኘው የሰብአዊ መብት ተቋም ኤርፋን ከመሞቱ በፊት ጽፎታል በሚል ያወጣው ማስታወሻ ላይ ግን ንጹህነቱን አስረድቷል።
ማስታወሻው፤ "የታሰርኩት በፈጠራ የስለላ ክሶች ነው፤ ስምንት ወር ከግማሽ ከቆየ ስቅይት እና የብቻ እስር በኋላ በሐሰት እንድናዘዝ ተገድጃለሁ። የሌላ ንጹህ ሰው ሕይወት በዝምታ እንዲነጠቅ አትፍቀዱ" ይላል።
የሰብአዊ መብት ተቋሙ ሄንጋው፤ የፍርድ ሂደቱ የሚከናወንበት፣ ፍርድ የሚተላለፍበት እንዲሁም የሞት ቅጣት ተፈጻሚ የሚደረግበት ፍጥረት እጅግ እንዳሳሰበው ገልጿል። የፍርድ ቤት ሂደቶች "ሙሉ ግልጽነት እንደሚጎድላቸውም" አንስቷል።
መህራብ አብዶላህዛዴህ ከመገደሉ በፊት ያስተላለፈው የድምፅ መልዕክትም የሞት ቅጣት እከስሚፈጸም መጠበቅ ያለውን ስቃት ገልጾ ነበር።
"የሞት ፍርድ የተላለፈበት ሰው በማንኛውም ሰዓት ሊጠራ እና ተወስዶ ሊገድል እንደሚችል በእያንዳንዷ ምሽት እና ቀን ያስባል።
የሞት ፍርድ የተላለፈበት ሰው ትንሽ ሰላም ማግኘት የሚችለው ከሌሊቱ 7 ሰዓት በኋላ ብቻ ነው። ምናልባት የዛኔ የሚመላለሱበትን ሀሳቦች ትቶ ለሁለት ወይም ለሦስት ሰዓታት መተኛት ይችላል" ብሏል።
'ኩርዲስታን ሂውማን ራይትስ ኔትዎርክ' እንደሚገልጸው፤ የ29 ዓመቱ ኩርዲሽ የሱቅ ባለቤት ለዘመዶቹም ሆነ ለጠበቆቹ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ተገድሏል። አስከሬኑም ወደ ቤተሰቡ አልተመለሰም።