በቅርቡ "በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የተቆጣጠረውን ቡድን አስወግደን" መቀለ እንገባለን የሚሉት ቡድኖች እነማን ናቸው?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

እሁድ ግንቦት 9/2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተመሠረተው የትግራይ "የሰላም እና የለውጥ ምክር ቤት" ከዓላማዎቹ መካከል አንዱ "በመፈንቅለ መንግሥት ትግራይን የተቆጣጠረውን ኃይል ማስወገድ" መሆኑን ስምረት ፓርቲ ለቢቢሲ ተናገረ።

የፓርቲው የሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን አስተባባሪ የሆኑት ብርሃነ ገብረየሱስ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ "የለውጥ ፈላጊዎች እንቅስቃሴ" የተባለ ቡድን ከተለያዩ ፓርቲዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ተውጣጥቶ "በትግራይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት" ላለፉት ሰባት ወራት ሲመክር እንደነበር ተናግረዋል።

እነዚህ የለውጥ ፈላጊዎች በምርጫ ቦርድ እውቅና ያገኙ አራት ፓርቲዎች እንዲሁም ታዋቂ ሰዎች መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

አቶ ብርሃነ አክለውም የለውጥ ፈላጊ ኃይሎች የተባለው ቡድን ወደ ምክር ቤት ሲያድግ በክልሉ የሚገኙ ከተጽዕኖ ፈጣሪዎች፣ ወደ ሰባት የሚሆኑ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የሚዲያ አካላት፣ ማኅበራትን አካትቶ እሁድ ግንቦት 9/2018 ዓ.ም. በይፋ ምክር ቤቱ መመሥረቱን ተናግረዋል።

ስምረት ፓርቲ በትግራይ ክልል ተመዝግበው ከሚንቀሳቀሱት ከባይቶና፣ ከዓረና ትግራይ፣ ከትንሳኤ 70 እንደርታ እና ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ከሲቪክ ማኅበረሰቦች ጋር በመሆን "የትግራይ ሰላም እና ለውጥ" ምክር ቤትን አቋቁመዋል።

"ከአሁን በኋላ የትግራይ ሕዘብ አሁን ባለበት ሁኔታ ረዥም ጊዜ መሄድ አይችልም" ያሉት አቶ ብርሃነ በኢኮኖሚ ጫና መጎዳቱን፣ ከመኖሪያ አካባቢው መፈናቀሉን እንዲሁም "በመልካም አስተዳደር፣ በፀጥታ እጦ፣ በሥራ አጥነት ጠቅላላ ክልሉ ምስቅልቅል ውስጥ" መሆኑን ተናግረዋል።

እሁድ ዕለት በአዲስ አበባ በይፋ የተቋቋመው ምክር ቤት የትግራይ ሕዝብ "በዚህ ደረጃ ረዥም ጊዜ መቆየት የለበትም" ብሎ እንደሚያምን ተናግረው "በአንድ ወር፣ ያ ካልሆነ . . . የለውጥ ፈላጊው በሚያደርገው እንቅስቃሴ ጊዜው ሊያጥርም ሊረዝምም በሚችልበት ሁኔታ" ለውጥ ለማምጣት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

ትግራይ ክልል ከዚህ ቀደም "ከአገሪቱ ክልሎች የተሻለ የሰላም እና መረጋጋት የልማት ጭላንጭል የነበረባት" እንደነበረች ያስታወሱት አቶ ብርሃነ፤ "አሁን ደግሞ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የመጨረሻዋ ነች" ሲሉ የክልሉ ሁኔታ እያሽቆለቆለ ነው ብለዋል።

በክልሉ የፀጥታ ችግር መኖሩን "ሰው በሰላም ወጥቶ የማይገባበት፣ የሚታፈንበት፣ የሚዘረፍበት፣ የጦር መሣሪያ እንደፈለገ የሚንቀሳቀስበት" መሆኑን የሚናገሩት አቶ ብርሃነ፤ "ሕዝቡ የሰላም እጦት ስጋት ውስጥ ስላለ ይህ አፋኝ እና ጠባብ ቡድን በማስወገድ ትግራይ ውስጥ ሁሉን ያካተተ ሥርዓታዊ ለውጥ ለማምጣት" ዓላማ እንዳላቸው አመለክተዋል።

ምክር ቤቱ በክልሉ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዘውን ቡድን "በአጭር ጊዜ ከትግራይ ሕዝብ ጫንቃ ማስወገድ" ዓላማው እንደሆነ ተናግረዋል።

በሁለተኛ ደረጃ "ቡድኑ" ከሥልጣን ሲወገድ ክልሉ "አላስፈላጊ ትርምስ ውስጥ እንዳይገባ የሰላም እና ፀጥታ ማረጋጋት" ሥራ እንደሚሠራም ጠቅሰዋል።

በሦስተኛነት አቶ ብርሃነ የምክር ቤቱ ዓላማ በማለት የጠቀሱት በክልሉ ሁሉንም አሳታፊ የሆነ ሥርዓት መዘርጋትን ነው።

"አንዱ የበይ ተመልካች አንደኛው ደግሞ ተሳታፊ የሚሆንበትን የፖለቲካ ሥርዓት በማስወገድ . . . ሁሉን ያካተተ. . . አቃፊ እና ሁሉንም አሳታፊ የሆነ መንግሥት የመመሥረት ዓላማ ይዘን ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው።"

የዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን አስተባባሪ የሆኑትን አቶ ብርሃነ "ቡድኑ" በማለት በተደጋጋሚ የሚጠሩት አካልን በስምጠርተው ግልጽ እንዲደያርጉ በቢቢሲ ህወሓት እንደሆነ የተጠየቁ ቢሆንም ግልጽ ያለ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

"ታጣቂዎች እና የጦር መሣሪያ አሰባስቦ ትግራይ ውስጥ እየዘረፈ እና እያመጸ፣ እየገዛ ያለ በዝባዥ ቡድን አለ። ስም እስካሁን የሰጠው አካል የለም" ብለዋል።

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፓርቲነት ዕውቅናው ተሰርዞ ያለው ህወሓት ከጥቂት ሳምንታት በፊት በትግራይ የተካሄደውን ጦርነት ባስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት የተመሠረተውን ጊዜያዊ መንግሥት የሚተካ ነው ያለውን የቀድሞ አስተዳደር መመለሱን መግለጹ ይታወቃል።

ይህም የህወሓት ውሳኔ ፕሪቶሪያ ስምምነትን በማፍረስ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ፍጥጫ ውስጥ የሚያስገባ ድርጊት ነው ሲሉ አንዳንዶች እየተቃወሙት ሲሆን፣ የህወሓት አመራሮች ሌላ ዙር ድርድር እንዲደረግ እየጠየቁ ባሉበት ወቅት ነው ሌሎች የክልሉ ኃይሎች አዲስ ስብስብ የመሠረቱት።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በህወሓተ ውስጥ በተፈጠረው ክፍፍል አመራሮቹ እና አባላት ከፓርቲው ወጥተዋል። አቶ ብርሃነም ፓርቲው ተከፋፍሎ እርቸሳውን ጨምሮ ሌሎች አባላቱ የተለያዩ ፓርቲዎችን መመሥረታቸውን ገልጸዋል።

ክልሉን "መሣሪያ ይዞ እየመራ ያለው አካል" ራሱን የሚጠራበት ስም ቢኖረውም፣ እርሳቸው ግን ስም የጠቅሰው መጥራት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።

"ትግራይን ወደ ጦርነት እና ወደ አላስፈላጊ ትርምስ ለማስገባት በመፈንቅለ መንግሥት ትግራይን የተቆጣጠረ የሆነ ኃይል አለ። ይህንን ኃይል ለማስወገድ ነው እኛ እየሠራን ያለነው።"

ስለዚህም እየተንቀሳቀሱ ያሉት ህወሓትን ለመጣል ስለመሆኑ በቢቢሲ የተጠየቁት አቶ ብርሃነ ". . .ህወሓትን ለመጣል አይደለም። ህወሓትማ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ተሰርዟል። አሁን ያለው በህወሓት ስም የሆነ የተደራጀ ቡድን ነው" ሲሉ መልሰዋል።

ይህ አቶ ብርሃነ 'ቡድን' ሲሉ የሚጠሩት አካል በፌደራል መንግሥቱ ሥልጣናቸው ለአንድ ዓመት የተራዘመላቸውን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዝዳንት "በመፈንቅለ መንግሥት አስወግዶ የተቆጣጠረው ሥልጣን አለ። ይህ ሕጋዊ ያልሆነ የጦረኛ ቡድን ነው። እኔም ድርጅቴም የምናምነው ይህንን ነው" ሲሉ አክለዋል።

ይህንን ቡድን ለማስወገድ ሁሉን አቀፍ የትግል ስልት እንደሚጠቀሙ የሚናገሩት አቶ ብርሃነ፣ "ክልሉን ወደ አላስፈላጊ ትርምስ፣ ወደ አላስፈላጊ ደም መፋሰስ ላለማስገባት፣ ወይንም እርሱን የሚቀንስ አቅጣጫ" እንደሚከተሉም ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀደም የለውጥ ፈላጊዎች እንቅስቃሴ፣ አሁን ደግሞ የለውጥ ፈላጊዎች ምክር ቤት በመባል የተቋቋመው ይህ አካል በፌደራል መንግሥት ድጋፍ ተቋቋመ ነው ስለመባሉ ሲጠየቁም "አሉባልታ ነው" በማለት ውድቅ አድርገውታል።

የተወሰኑ አባላቱ እና አመራሮቹ በአዲስ አበባ የሚገኙት በትግራይ ውስጥ በፈለጉት የፖለቲካ አመለካከት እና ዓላማ በነጻነት ተደራጅተው አባላትን መመልመል እና ማደራጀት ባለመቻላቸው መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

ነገር ግን የለውጥ ፈላጊዎች እንቅስቃሴ አመራሮች ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ትግራይ ውስጥ የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዴት መተግበር አለበት፣ የትግራይ ሕዝብ አሁን ከገባበት ችግር እንዴት ይውጣ፣ የፌደራል መንግሥቱ ትግራይ ውስጥ ምን አስተዋጽኦ እና ድጋፍ ነው ማድረግ ያለበት? በሚለው ዙሪያ ንግግር ሲደርጉ እንደነበር አስረድተዋል።

"በተለየ ሁኔታ የፌደራል መንግሥት እኛን እንደፈለገው የሚዘውር ነው የሚባለው ነገር 'የጠባቡ ቡድን' ፕሮፖጋንዳ ነው። እኛ የገንዘብ ምንጫችንም የምንንቀሳቀሰውም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ካሉ አባሎቻችን እና ደጋፊዎቻች በምናገኘው ድጋፍ ነው።"

ጊዜያዊ አስተዳደሩን የሚተካ ምክር ቤት እና ፕሬዝዳንት በማዋቀር የቀድሞውን አስተደዳር በትግራይ ስለመመለሱ አስካሁን ከፌደራል መንግሥቱ በይፋ የተባለ ነገር የለም።

እንዲሁም አዲስ ከተመሠረተው የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማኅበረሰብ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ከትግራይ በኩልም ሆነ ከፌደራል መንግሥቱ የተሰማ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ የለም።