ለዓመታት አንድ ላይ ሲሠሩ የቆዩት ጓደኛሞች እህትማማች የሆነው የተገኙበት አጋጣሚ

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ጁሊያ ቲናቲ እና ካሳንድራ ማዲሰን ብዙ የሚያመሳስላቸው ነገር አለ። በአንድ መጠጥ ቤት ውስጥ ሲሠሩ ተዋውቀው ጓደኛሞች ሆኑ።

ሁለቱም በአሜሪካ በ1960ዎቹ ነው ተወልደው ያደጉት። ልጅ ሳሉ አይተዋወቁም ነበር። ቤታቸው የ15 ደቂቃ ርቀት ነበረው።

ሁለቱም ያደረጉት በማደጎ ቤተሰብ ውስጥ ነው። ካሳንድራ ልጅ ሳለች ስለ ወላጅ እናቷ አዘውትራ ታስብ ነበር።

ዐይኗ ወይም ፈገግታዋ ከእናቷ ጋር ይሚመሳሰል እንደሆነ ታስባለች። ወላጆቿ ከዶሚኒካን ሪፐብሊክ እንደመጡ ታውቃለች።

"እጅግ በጣም ድሃ ስለሆኑ ለማደጎ ሰጡኝ። እኔን ማሳደግ አይችሉም ነበር" ትላለች።

የልደት ሰርተፍኬት ስላልለነበራት ወላጆቿን ለማግኘት ያደረገችው ጥረት አልተሳካም።

በ19 ዓመቷ የዶሚኒካን ሪፐብሊክ ሰንደቅ ዓላማን ክንዷ ላይ ተነቀሰች። ታሪኳን ለማስታወቅ በሚል ነበር ንቅሳቱን ያሠራችው።

"ለእኔ ዶሚኒካዊት መሆን የሚያኮራ ነው" ትላለች።

ከአምስት ዓመታት በኋላ አስተናጋጅ ሆነች። ከጁሊያ ጋር ተዋወቁ። ጁሊያም ጀርባዋ ላይ ተመሳሳይ የዶሚኒካን ሪፐብሊክ ሰንደቅ ዓላማ ንቅሳት ነበራት።

ጁሊያ ንቅሳቱን የተሠራችው በ22 ዓመቷ ነበር።

እሷም የተወለደችበትን ቦታ ለማስታወስ በሚል ነው ንቅሳቱን የመረጠችው።

ሁለቱ የሥራ ባልደረቦች በማደጎ ቤተሰብ ውስጥ እንዳደጉ አወቁ።

"ከዶሚኒካን ሪፐብሊክ በማደጎ መወሰዴን ነገርኳት። እሷም ተመሳሳይ ታሪክ እንዳላት ነገረችኝ። አስደነገጠኝ" ትላለች ጁሊያ።

ከዚያም ሰዎችን መጠየቅ ጀመሩ። እንመሳሰላለን? ብለው የጠየቋቸው ሰዎች እንደሚመሳሰሉ አረጋገጡላቸው።

እንዲሁ ለቀልድ ያህል እህትማማቾች ነን እያሉ ያወሩ ነበር። እንዲያውም የበለጠ ለመመሳሰል ተመሳሳይ ልብስ መግዛት ጀመሩ።

አብዛኛውን ነገር ለቀልድ ብለው ቢያደርጉትም የእውነት ዝምድና ሊኖራቸው እንደሚችል ጠረጠሩ።

በማደጎ የተወሰዱባቸውን ሰነዶች ማነጻጸር ጀመሩ። እህትማማቾች መሆናቸውን የሚያሳይ መረጃ አላገኙም።

ሰነዶቹ የሚያሳዩት የተለያየ አካባቢ መወለዳቸውን ነው። የትውልድ እናቶቻቸው የአባት ስምም የተለያየ ነው።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሁለቱም የተለያየ ሥራ አግኝተው ተለያዩ።

ካሳንድራ ወደ ቨርጂኒያ ስትሄድ ጁሊያ እዚያው የተዋወቁበት ኮኔክቲከት ግዛት ውስጥ ቀረች።

እንደ ድሮው ባይቀራረቡም ይጠያየቁ ነበር።

ከዓመታት በኋላ ካሳንድራ የዘረ መል መመርመሪያ ለገና ስጦታ ተበረከተላት።

የአክስቷን ልጅ ያገኘችውም በዚህ ምርመራ ነበር። እናቷ በአውሮፓውያኑ 2025 መሞቷን ከአክስቷ ልጅ ሰማች።

መርዶው ቢያሳዝናትም አባቷን ጨምሮ ሌሎችም የቤተሰብ አባሎቿን ማግኘት እንደምትችል አወቀች።

ልጅ ሳለች ወላጆቿ በጣም እንግልት እንደደረሰባቸው ከአክስቷ ልጅ ተረዳች።

አባቷ አድሪኖ ላውና ኮላዶን በስልክ አገኘች። ቤተሰቡ በከፍተኛ ድህነት ምክንያት የሚተኛበት ቦታ እንኳን እንዳልነበረው ነገራት። ቆሻሻ መሬት ላይ እየተኙ ሳለም ለማደጎ ቤተሰብ ሊሰጧት ወሰኑ።

እናቷ እሷን አርግዛ ታላቅ ወንድሟ በጠና ታምሞ ነበር። ስለዚህም በማደጎ ከመስጠት ውጪ አማራጭ እንደሌላቸው አባቷ ወሰነ።

ወደ ዶሚኒካን ሪፐብሊክ አቅንታ መላው ቤተሰቧን ተዋወቀች።

የእሷ ምሥል ያለበት ካናቴራ አሠርተው ነበር የጠበቋት። ልክ አባቷን እንዳየችው አቅፋው ማልቀስ ጀመረች። አባቷም አብሯት አለቀሰ።

ወደ አሜሪካ ስትመለስ በደስታ ተሞልታ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሞሊ ከምትባል ሰው መልዕክት ደረሳት።

ሞሊ የጁሊያ የልጅነት ጓደኛ ናት። የሁለቱ ጓደኛሞች ቤተሰቦች ከዶሚኒካን ሪፐብሊክ ልጆች በማደጎ ለመውሰድ አብረው ነበር የተጓዙት።

የሞሊ እናት እና የካሳንድራ እናት ተመሳሳይ ስም ስላላቸው እህትማማች እንደሆኑ አስባ ነበር።

ሆኖም ግን የዘረ መል ምርመራ ሲያደርጉ እህትማማች እንዳልሆኑ አወቁ። የልደት ሰርተፍኬት ላይ ያለው ስም የተሳሳተ እንደሆነም ደረሱበት።

ሞሊ የካሳንድራ እናት ፎቶ ነበራት። ይህ ፎቶ ከጁሊያ እናት ፎቶ ጋር በጣም ይመሳሰላል።

ስለዚህም ካሳንድራ እና ጁሊያ እህትማማቾች መሆናቸውን ሞሊ ገመተች።

ካሳንድራ ለአባቷ በቪድዮ ደውላ ሌላ ልጅ ለማደጎ ሰጥተው እንደሆነ ጠየቀች አባቷም አውነታቸውን ነገራች።

"አዎን ሌላ ልጅ በማደጎ ሰጥተናል" አላት። "ለምን እስከዛሬ ድረስ አልነገርከኝም" ብላም ተደነቀች።

የዘረ መል መመርመሪያ መሣሪያ ይዛ ስምንት ሰዓታት ነድታ ወደ ቨርጂኒያ ሄደች።

የምርመራው ውጤት ሁለት ሳምንት ተኩል ይወስዳል። ሁለቱም በጉጉት ይጠብቁ ነበር።

በስተመጨረሻም ሲጠብቁት የነበረው የዘረ መል ውጤት መጣ። እህትማማቾች መሆናቸውም ተረጋገጠ።

"እህትማማቾች መሆናችንን ሳናውቅ መቆየታችን በጣም አስገራሚ ነው" ትላለች ጁሊያ።

ካሳንድራ ዜናውን ስትሰማ አለቀሰች። ለአባቷም ደውላ ነገረችው። አባትም ሌላኛውን ልጁን በቶሎ እንድታስተዋውቀው ነገራት።

እህትማማቾቹ አብረው ወደ ዶሚኒካን ሪፐብሊክ ተጓዙ። አሁንም መላው ቤተሰቡ በአንድነት ነበር የጠበቃቸው።

ቤተሰቡ የሁለቱንም እህትማማቾች ምሥል በካናቴራ አሳትሞ ተቀበላቸው።

አባትም ጁሊያን ሲያይ "ልጄ" ብሉ አጥብቆ አቀፋት።

የእህትማማቾቹ የመጀመሪያ የቤተሰብ ጥየቃ ጉዞ በደስታ የተሞላ ነበር። ሙዚቃ ሲሰሙ፣ ሲደንሱ ጥሩ ጊዜን አሳለፉ።

ከልጆቹ ጋር መገናኘት ታላቁ የፈጣሪ ስጦታ እንደሆነ አባትየው ይናገራል።

"በጣም ደስተኛ ነኝ። የእውነት ደስተኛ ነን። ሊጠይቁኝ ሲመጡ ልቤ በሐሴት ይሞላል። ሁሉም ቤተሰብ ማድረግ እንዳለበት በፍቅር እንቀበላቸዋል። ታሪካችን ውብ ነው። ሁሉም ቤተሰብ እንዲህ ያለ ቆንጆ ታሪክ አይኖረውም።"