በሕይወት ለመቆየት ልጆቻቸውን እስከመሸጥ የደረሱት የአፍጋኒስታን አባቶች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ጀንበር እንደወጣች በአፍጋኒስታን የጎር ግዛት ዋና ከተማ ቻግቻራን በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንዶች አቧራ በሸፈነው አደባባይ ይሰብሰባሉ።

ሰዎች መጥተው ማንኛውንም ሥራ ይቀጥሩን ይሆናል በሚል ተስፋ ከመንገዱ አጠገብ ተሰልፈው ይቆማሉ። ይህም በዚያች ቀን ቤተሰቦቻቸው ምግብ እንደሚመገቡ እና እንደማይመገቡ ይወስናል።

ነገር ግን ይህ የመሆኑ ዕድል እጅግ ዝቅተኛ ነው።

የ45 ዓመቱ ጁማ ካን በካብ በስድስት ሳምንታት ውስጥ በቀን 150 እስከ 200 አፍጋኒ (ከ2.35 እስከ 3.13 ዶላር) የሚከፈል ሥራ ሦስት ቀናት ብቻ አግኝቷል።

"ልጆቼ ለሦስት ቀናት በተከታታይ እንደራባቸው አድረዋል። ባለቤቴ እያለቀሰች ነበር፣ ልጆቼም እንዲሁ። ስለዚህ ዱቄት ለመግዛት ጎረቤቴ ገንዘብ እንዲያበድረኝ ለመንኩት" ይላል።

"ልጆቼ በረሃብ ይሞታሉ ብዬ በፍርሃት እኖራለሁ።"

የኩማ ታሪክ የአንድ ሰው ታሪክ አይደለም።

ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ጽሑፍ ሊረብሹ የሚችሉ ዝርዝሮችን ይዟል

ዛሬ በአፍጋኒስታን እንደ መንግሥታቱ ድርጅት ከሆነ ከአራት ሰዎች ሦስቱ መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ማሟላት አይችሉም።

ሥራ አጥነት በስፋት ተፈጥሯል፤ የጤና አገልግሎት ጭንቅ ውስጥ ነው፤ ከዚህ ቀደም ለሚሊዮኖች መሠረታዊ ግብዓቶችን ያቀርብ የነበረው እርዳታ አሁን ሽርፍራፊው ነው የሚቀርበው።

አገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ረሃብ የተመታች ሲሆን፤ ከጠቅላላ ሕዝቡ 10 በመቶው ማለትም 4.7 ሚሊዮን ሰዎች በቸነፈር ለመመታት ጫፍ ላይ እንደሆኑ ይገመታል።

ጎር ክፉኛ ከተጎዱ ግዛቶች አንዱ ነው።

በዚህ አካባቢ ወንዶች ተስፋ ቆርጠዋል።

ራቢኒ ሳግ እየተናነቀው "ልጆቼ ሁለት ቀን ምግብ እንዳልቀመሱ ተደውሎ ተነግሮኛል" ይላል።

"ራሴን ማጥፋት እንዳለብኝ ተሰምቶኛል። ከዚያ ግን ይህ ቤተሰቤን እንዴት ሊረዳ ይችላል ብዬ አሰብኩ። ለዚህ ነው ሥራ ለመፈለግ እዚህ የተገኘሁት" ይላል።

ክዋጃ አህመድ እንባ ሳይተናነቀው ጥቂት ቃላት እንኳ ከአፉ አይወጡም።

"እየራበን ነው። ትልቅ ልጆቼ ሞተዋል። ስለዚህ ቤተሰቤን ለመመገብ መሥራት አለብኝ። ግን አርጅቻለሁ፤ እናም ማንም ሥራ ሊሰጠኝ አይፈልግም" ይላል።

በአደባባዩ አጠገብ ያለ ዳቦ ቤት ሲከፈት ባለቤቱ ለተሰበሰቡት ሰዎች የተበላሸ ዳቦ ያከፋፍላል። በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ ዳቦውን ተሻምተው ይወስዳሉ። ግማሽ የሚሆኑት ሰዎች በእጃቸው ዳቦ ይዘው ይታያሉ።

ወዲያውኑ ሌላ ሁኔታ ተፈጠረ። የሞተር ሳይክል የሚያሽከረክር ሰው ድንጋይ የሚሸከም አንድ የቀን ሠራተኛ ለመቅጠር ይመጣል። በጣም ብዙ ወንዶች ይህን ሥራ ለመቀጠር ግርግር ይፈጥራሉ።

ለሁለት ሰዓት በሥፍራው ስንቆይ፣ ሦስት ሰዎች ብቻ ሥራ አግኝተዋል።

በአቅራቢያው ባሉ ማኅበረሰቦች ዘንድ የሥራ አጥነት አስከፊ ተፅዕኖው ግልጽ ሆኖ ይታያል።

አብዱል ራሺድ አዚሚ የሰባት ዓመት የሆኑ መንታ ልጆቹን ሮቂያ እና ሮሂላ የገጠመውን ከባድ ውሳኔውን ለማብራራት ቀረብ አድርጎ በጉጉት ይናገራል።

"ሴት ልጆቼን ለመሸጥ እንኳን ዝግጁ ነኝ" እያለ ነፍርቆ ያለቅሳል። "ደሃ ነኝ፣ ብድር ያለብኝ እና ረዳት ያጣሁ።

"ከሥራ ደረቅ ከንፈሬን ይዤ፣ በረሃብ፣ በጥማት፣ በጭንቀት እና ግራ በመጋባት ወደ ቤት እመጣለሁ። ልጆቼ 'አባ፣ እባክህ ዳቦ ስጠን' ብለው ይመጣሉ። ግን ምን እሰጣቸዋለሁ? ሥራ የት አለ?"

ሮሂላን እያቀፈ፤ እየሳመ ያለቅሳል። "ልቤን ይሰብረዋል፤ ግን ሌሎች ልጆቼን ለመመገብ ይህ ብቸኛ መንገድ ነው።"

"ለመመገብ ያለን ነገር ዳቦ እና ሙቅ ውሃ ብቻ ነው፤ ሻይ እንኳ የለም" ትላለች እናታቸው ካይሃን።

ሁለቱ ታዳጊ ልጆቿ ጫማ መጥረግ ይሰራሉ። ሌላኛው ልጅ ቆሻሻ ይሰበስባል፤ ቆሻሻውን ካይሃን እንደ ማገዶ ምግብ ለማብሰል ትጠቀማለች።

ሳይድ አህመድ የአምስት ዓመት ሴት ልጁ ሻይቃ ትርፍ አንጀት እና ጉበቷን ካመማት በኋላ ለመሸጥ እንደተገደደ ይናገራል።

"የሕክምና ወጪውን ለመክፈል ገንዘብ አልነበረኝም። ስለዚህ ልጄን ለዘመድ ሸጥኩ" ይላል።

የሻይቃ ቀዶ ሕክምና የተሳካ ነበር። የሕክምና ወጪው ከተሸጠችበት ገንዘብ ነበር የመጣው።

ሻይቃ በትናንሽ እጆቿ አንገቱን ትነካካለች። በመካከላቸው ያለው ግንኙነት ቅርብ ለመሆኑ ግልጽ ነው። ግን ከአምስት ዓመታት በኋላ ወደተሸጠችበት ቤተሰብ ትሄዳለች።

"ገንዘብ ቢኖረኝ ኖሮ ይህን ውሳኔ በፍጹም አልወስንም ነበር" ይላል።

"ግን ያለ ቀዶ ሕክምናው ብትሞት ምን ይሆናል? ብዬ አስባለሁ። በዚህ መንገድ ቢያንስ በሕይወት ትቆያለች።"

ሳይድ አህመድ እንደ ሚሊዮኖች አፍጋናዊያን ሁሉ ከሁለት ዓመት በፊት እርዳታ ያገኝ ነበር።

ዱቄት፣ ዘይት፣ ምስር እና ለሕፃናት ልዩ ምግቦች ይሰጣቸው ነበር።

ግን ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ የእርዳታ ቅነሳ ብዙዎች ይህን የሕይወት አድን ድጋፍ አስቀርቶባቸዋል።

የአፍጋኒስታን ከፍተኛ የእርዳታ አቅራቢ የነበረችው አሜሪካ ባለፈው ዓመት አብዛኛውን እርዳታዋን አቋርጣለች። ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ ሌሎች ቁልፍ እርዳታ አቅራቢዎችም እንዲሁ እርዳታቸውን ቀንሰዋል።

በመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ መሰረት በዚህ ዓመት ያለው እርዳታ ከ2025 ጋር ሲነጻጸር በ70 በመቶ ያነሰ ነው።

በአገሪቱ ከግማሽ በላይ በሆኑ ግዛቶች የተከሰተው ከባድ ድርቅ ችግሩን የበለጠ አባብሶታል።

"ከመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች አንድም እርዳታ አላገኘንም" ይላል አብዱል ማሊክ።

እ.አ.አ በ2021 አገሪቱን የተቆጣጠረው የታሊባን መንግሥት የቀውሱን ኃላፊነት የውጭ ኃይሎች ሲወጡ ተገዶ በወጣው በቀደመው አስተዳደር ላይ ይጥላል።

"በ20 ዓመታት የወረራ ጊዜ ሐሰተኛ ኢኮኖሚ ተፈጥሯል" ይላሉ የታሊባን መንግሥት ምክትል ቃል አቀባይ ሃምዱላህ ፊጥራት።

"ከወረራው በኋላ ድህነት፣ ችግር፣ ሥራ አጥነት እና ሌሎች ችግሮችን ወረስን።"

ይሁን እንጂ የታሊባን ፖሊሲዎች በተለይም በሴቶች ላይ የሚያደርገው ክልከላ የረድኤት ድርጅቶች ፊታቸውን እንዲያዞሩ ያደረገ ዋነኛ ምክንያት ነው።

ታሊባን ግን ይህን አይቀበልም። "ሰብዓዊ እርዳታ ፖለቲካዊ መሆን አይገባውም" ይላል።

መንግሥት ድህነትን ለመቀነስ እና ሥራ ለመፍጠር መሠረተ ልማት እና ማዕድን የመሰሉ የኢኮኖሚ ፕሮጀክቶች እንዳሉት ይናገራል።

እነዚህ የረጅም ጊዜ እቅዶች አንድ ቀን ፍሬ ሊያፈሩ ቢችሉም፤ አስቸኳይ እርዳታ ካላገኙ በሕይወት መቆየት የማይችሉ ሚሊዮን ሰዎች ግን አሉ።

ከእነዚህ ሰዎች መካከል የ14 ወር እድሜ ያላት ሴት ልጁ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የሞተችበት መሐመድ ሀሽም አንዱ ነው።

"ልጄ በረሃብ እና በመድሃኒት እጥረት ሞተች። . . . ሕፃን ሲታመም እና ሲራብ መሞቱ አይቀሬ ነው" ይላል።

በአካባቢው ሽማግሌ የሆኑ አንድ ነዋሪ የሕፃናት ሞት ባለፉት ሁለት ዓመተት በተለይም ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ "በጣም ከፍ ብሏል" ይላሉ።

ነገር ግን እዚህ አካባቢ ሞት በይፋ አይዘገብም። የሕፃናት ሞት ከፍ ለማለቱ ማስረጃ የሚገኝበት ብቸኛ ስፍራው መቃብር ቤት ነው። ትንሽ እና ትልቅ መቃብሮችን በማነፃፀር ስንቆጥር፤ ትንሽ መቃብሮች ከትልቁ እጥፍ ሆነው አግኝተናቸዋል። ይህም ማለት የሕፃናት ሞት ከአዋቂዎች በሁለት እጥፍ ይበልጣል።

በቻግቻራን ባለው ዋና ሆስፒታልም ተጨማሪ ማስረጃ አለ።

የጨቅላ ሕፃናት ክፍሉ በጣም የተጨናነቀ ነው። አልጋዎች ሁሉ ተሞልተዋል፣ አንዳንዶቹ ሁለት ሕፃናት አስተኝተዋል። አብዛኞቹ ሕፃናት ክብደታቸው ቀንሷል፤ ብዙዎቹ ደግሞ በራሳቸው መተንፈስ ይቸገራሉ።

አንዲት ነርስ መንታ ልጆችን ታንቀሳቅሳለች። ከሁለት ወር ቀደም ብለው የተወለዱ ናቸው። አንዷ 2 ኪሎ ትሆናለች፣ ሌላኛዋ 1 ኪሎ ብቻ ናት።

ሕፃናቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ ሲሆኑ ወዲያውኑ ኦክስጅን ተሰጥቷቸዋል።

የ22 ዓመቷ እናታቸው ሻኪላ በእናቶች ክፍል እያገገመች ነው።

"ነፍሰ ጡር እያለች በቂ ምግብ ባለማግኘቷ ደካማ ናት። ዳቦ እና ሻይ ብቻ ነው ያገኘችው" በማለት የመንታዎቹ አያት ጉልባዳን ትገልለፃች። "ለዚህ ነው ሕፃናቱ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያሉት።"

ከሆስፒታሉ ከወጣን ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ከሁለቱ ሕፃናት በክብደት ከፍ ያለችው ሕፃን ስም እንኳ ሳይወጣላት ሕይወቷ አልፏል።

"ትንሽ ሰውነቷን ጠቅልየ ወደ ቤት ወሰድኳት። እናቷ እንደሞተች ስታውቅ ራሷን ስታ ወደቀች" ትላለች ጉልባዳን። "ቢያንስ እሷ [እናትየዋ] ትተርፋለች ብዬ እመኛለሁ።"

ነርስ ፋጢማ ሁሴን በቀን እስከ ሦስት ሕፃናት የሚሞቱባቸው አንዳንድ ቀናት እንዳሉ ትናገራለች።

"በመጀመሪያ ጊዜ ሕፃናት ሲሞቱ ማየት በጣም ከባድ ነበር። ግን አሁን እንደ መደበኛ ሁኔታ ተላምደነዋል" ትላለች።

የጨቅላ ሕፃናትን ክፍል የሚመራው ዶ/ር መሐመድ ሞሳ የሕፃናት የሞት መጠን እስከ 10 በመቶ ድረስ ከፍ እንዳለ ይናገራሉ። ይህንም "ተቀባነይት የሌለው" ነው በማለት ይገልፁታል።

"በድህነት ምክንያት የታካሚዎች ቁጥር ከቀን ቀን እየጨመረ ነው" ይላል። "እዚህም [ሆስፒታል] ሕፃናቱን በተገቢ መንገድ ለማከም የሚያስፈልጉ ግብዓቶች የሉንም።"

የገንዘብ እጥረት ብዙ ቤተሰቦችን ከባድ ውሳኔዎች እንዲወስኑ አስገድዷል።

የጉልባዳን በሕይወት የተፈረችው የልጅ ልጅ አሁን ትንሽ ክብደት ጨምራለች፤ አተነፋፈሷም ተስተካክሏል። ግን ከጥቂት ቀናት በኋላ ቤተሰቧ በገንዘብ ምክንያት ሆስፒታል ማቆየት ባለመቻሉ ወደ ቤት ወስዷታል።

ህፃን ዘሚርም በተመሳሳይ ምክንያት ወላጆቹ ወደ ቤት መልሰውታል።

ያልጠነከረ አካላቸው ያለእርዳታ ለመቆየት ከባድ ትግል ማድረግ ይኖርበታል።