ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኬንያ አራት ሰዎች ከተገደሉ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ ቢደረግም አድማው ቀጥሏል
በኬንያ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ ተቃውሞ ተቀሰቅሶ አራት ሰዎች ተገድለው በርካቶች ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ የዋጋ ቅናሽ ቢደረግም አድማው ቀጥሏል።
የኬንያ አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ከአድማው ጋር በተያያዘ የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ ቢያንስ 30 ሰዎች ተጎድተዋል እንዲሁም ከ300 በላይ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ውለዋል።
የአገሪቱ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች እና የአሽከርካሪዎች ማኅበራት ከመንግሥት ጋር ባደረጉት ድርድር የ10 ሽልንግ ቅናሽ የተደረገ ቢሆንም ባለመስማማታቸው ተቃውሞው ለሁለተኛ ቀን ማክሰኞ ዕለትም ቀጥሏል።
ሰኞ ዕለት የዋና ከተማዋ ናይሮቢ ጎዳናዎች ጭር ብለው የዋሉ ሲሆን ትምህርት ቤቶች እና ንግዶች ተዘግተዋል።
የተቃዋሚ ሠልፈኞች መንገዶችን በድንጋይ የዘጉ ሲሆን ጎማዎችን ሲያቃጥሉ ታይተዋል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኪፕቹምባ ሙርኮሜን 348 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ጨምረው አስታውቀዋል።
ኬንያውያን ለተቃውሞ አደባባይ የወጡት የነዳጅ ዘይት ላይ ከዚህ በፊት ታይቶ አይታወቅም በተባለ መጠን ከ20 በመቶ በላይ ጭማሪ በመደረጉ ነው።
ኬንያ እንደሌሎች የአፍሪካ አገራት ሁሉ ነዳጅ የምታስገባው ከባሕረ ሰላጤው አገራት ነው።
ከየካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጀምሮ እስራኤል እና አሜሪካ በቴህራን ላይ ጦርነት በመክፈታቸው የተነሳ ከባሕረ ሰላጤው የሚገባ የነዳጅ ዘይት መስተጓጎል ገጥሞታል።
በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተኩስ አቁም ቢደረስም የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ ዘይት የሚተላለፈበት የሆርሙዝ ወሽመጥ እንደተዘጋ በመሆኑ የነዳጅ ዋጋ እንደ ጨመረ ነው።
በናይሮቢ በትናንትናው ዕለት በርካታ መንገደኞች አውቶቡስ አጥተው በእግራቸው ለመጓዝ ተገድደዋል።
ከናይሮቢ ወጣ ብላ በምትገኘው ኪቴንጌላ የሚኖረው ቻርልስ "የትም ማታቱ (ሚኒባሶች) የለም። . . . ከዚህ ቀድም ከ100 እስከ 150 ሺሊንግ እንከፍል ነበር። አሁን ግን 300 ደርሷል። ሕይወትን መቋቋም ከብዶናል፥ ስለዚህ እባክዎን ሩቶ [ፕሬዚዳንት ዊሊያም] የትም ሆኑ የትም ኬንያውያን የሚያዳምጡ ከሆነ የነዳጅ ዋጋን ይቀንሱልን" ሲል መማጸኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
ከታንዛኒያ መንገደኞችን ጭኖ የመጣ አውቶቡስ ወደ ናይሮቢ ተቃዋሚዎች መንገደኞችን በመዝጋታቸው ለመግባት አለመቻሉን ገልጾ ከዋና ከተማዋ 75 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ካጃይዶ ለመቆም መገደዱን ተናግሯል።
የአውቶብሱ ረዳት "አውቶብሱ ሙሉ ነው። አብዛኞቹ መንገደኞች ለሥራ እና ለንግድ ነው የሚንቀሳቀሱት፤ የትራንስፖርት አገልግሎት በመቋረጡ መንገደኞች ቆመዋል፤ ተስፋ ቆርጠዋል" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
አብዲ ሱሌይማን የተባለ አሽከርካሪ ደግሞ በኬንያ ደቡብ ምስራቅ በምትገኘው የድንበር ከተማ ታቬይታ እንደሚሰራ ተናግሮ ከማለዳ ጀምሮ በተቃውሞ ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎት በመቋረጡ ስራውን መስራት አለመቻሉን ተናግሯል።
በናይሮቢ እና በሌሎች ከተሞች መንገድ የዘጉ፣ ጎማ የሚያቃጥሉ እና አሽከርካሪዎችን በማስቆም የሚያጉላሉ ተቃዋሚ ሠልፈኞችን ለመበተን አስለቃሽ ጋዝ ተጠቅሟል።
የናይሮቢ ፖሊስ አዛዥ ኢሳ ሞሐሙድ ስድስት የፖሊስ ባልደረቦች መጎዳታቸውን እንዲሁም አምስት የፖሊስ እና የአንድ የነዋሪ መኪኖች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።
ከተቃውሞው በፊት ፖሊስ ኬንያውያንን ጸጥታ በማስከበር ረገድ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጾ ተቃዋሟቸውን የሚገልጹ ሠልፈኞች ማኅበረሰቡን ከሚያውክ ተግባር እንዲታቀቡ አስጠንቅቆ ነበር።
ሰኞ ምሽት ለጋዜጠኞች አስተያየታቸውን የሰጡት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኪፕቹምባ ሙርኮሜን "እንዳለመታደል ሆነ ዛሬም ተቃዋሚ ሠልፈኞች የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት በሚያስቡ ፖለቲከኞች ተጠልፈዋል" ብለዋል።
"ንብረቶች መዝረፍ እና የሕዝብ ንብረት ማውደም የነዳጅ ዋጋን አይቀንስም" ማለታቸውን የኬንያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
"የትራንስፖርት አገልግሎትን ማስተጓጎል እና ሕይወትን ማወክ የሚያደርገው ኬንያውያን የሚጋፈጡትን ማባባስ ብቻ ነው" ብለዋል።
ሙርኮሜን አክለውም አብዛኞቹ መንገዶች ለትራንስፖርት ክፍት መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአሽከርካሪዎች እና ተሽከርካሪዎች ማኅበራት ቀደም ሲል የግል አሽከርካሪዎች፣ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች እና የጭነት መኪና አሽከርካሪዎችን ጨምሮ ሁሉም የተሽከርካሪ ተጠቃሚዎች አድማውን እንዲቀላቀሉ እና ከእንቅስቃሴ አንዲቆጠቡ አስጠንቅቀው ነበር።
"ይህ እርምጃ ለትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ብቻ ሳይሆን ለእያንዳንዱ የኬንያ ዜጋ ጭምር ነው" ሲል የትራንስፖርት ሴክተር አሊያንስ (ቲኤስኤ) በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ጥምረቱ መንግሥት በዚህ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት በተከሰተበ ጊዜ ኬንያውያንን ከነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ለመከላከል በቂ ጥረት አላደረገም ሲል ከስሷል።
ባለፈው ሳምንት የተገለጸውን የዋጋ ጭማሪ እንዲቀለበስ እና የነዳጅ ዋጋ በ35 በመቶ እንዲቀንስ ጥሪ አቅርቧል።
የኢነርጂ እና የነዳጅ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ናፍጣ እና ቤንዚን በአንድ ሊትር ወደ 242 ሽልንግ (1.8 ዶላር እና 1.65 ዶላር) ከፍ አድርጓል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ ጆን ምባዲ ሰኞ ዕለት ለኤንቲቪ እንደተናገሩት የነዳጅ ዋጋ መጨመር "አሳዛኝ" መሆኑን ገልጸው ይህም ኢኮኖሚውን እየጎዳ መሆኑን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ተቃውሞውን "ፈጽሞ አላስፈላጊ" ሲሉ ጠርተው መንግሥት "ከስሜት ይልቅ በመረጃ ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎችን" ብቻ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
"ለምን አንድን ዓለም አቀፍ ችግር በአገር ውስጥ መንገዶች ለመፍታት እንሞክራለን?" ሲሉም ጠይቀዋል።
የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ የምግብ እና ለሌሎች መሠረታዊ ሸቀጦች እና አገልግሎቶች ዋጋ እንዲጨምር ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ የሕዝብ አገልግሎት ተሽከርካሪዎች የመጓጓዣ ዋጋን አስቀድመው ጨምረዋል።
ባለፈው ወር መንግሥት እስከ ሐምሌ ወር ድረስ በነዳጅ ላይ ያለውን የተጨማሪ እሴት ታክስ ከ16 በመቶ ወደ 8 በመቶ የቀነሰ ቢሆንም ተጨማሪ እርምጃዎችን እንዲወስድ ተጠይቋል።