የዓለም ጤና ድርጅት በዴሞክራቲክ ኮንጎ የተከሰተውን ኢቦላ በዓለም አቀፍ የኅብረተሰብ ጤና አደጋነት አወጀ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዓለም ጤና ድርጅት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምሥራቃዊ ኢቱሪ ግዛት የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝ አሳሳቢ ዓለም አቀፍ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ሲል አወጀ።

የተባበሩት መንግሥታት የጤና ተቋሙ እንዳስታወቀው እስካሁን 246 ገደማ ሰዎች በበሽታው እንደተያዙ የተጠረጠሩበት እና የ80 ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈበት ይህ ክስተት የዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ምድብ ውስጥ ለመግባት መስፈርቱን አያሟላም።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም በአሁኑ ሰዓት "በበሽታው የተያዙ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር እና በሽታው የተስፋፋበት ጂኦግራፊያዊ ስርጭት ላይ በከፍተኛ መጠን እርግጠኝነት እንደሚጎድል" አስጠንቅቀዋል።

እንደ ተቋሙ ገለጻ፤ አሁን የተከሰተው የኢቦላ ዝርያ "በቡንዲቡግዮ ቫይረስ" አማካኝነት የመጣ ሲሆን እስካሁን ለዚህ ዝርያ የጸደቀ መድኃኒትም ሆነ ክትባት የለም።

አሁን ላይ ከቫይረሱ ጋር የተያያዙ ስምንት ኬዞች በላብራቶሪ ተረጋግጠዋል። የኢቱሪ ግዛት ዋና ከተማ የሆነችው ቡኒያ እንዲሁም ሞንግዋሉ እና ራምፓራ የተባሉት የወርቅ ማውጫ ከተሞችን ጨምሮ በሦስት አካባቢዎች ውስጥ በበሽታው የተጠረጠሩ እና የሞቱ ሰዎች እንዳሉ ተገልጿል።

በሽታው ከዴሞክራቲክ ኮንጎ እንዳለፈ እና በአጎራባቿ ዩጋንዳ ውስጥ ሁለት የተረጋገጡ ኬዞች መመዝገባቸውን ዓለም አቀፉ የጤና ተቋም አስታውቋል።

እንደ የኡጋንዳ ባለሥልጣናት ገለጻ፤ ሐሙስ ዕለት ሕይወቱ ያለፈው የ59 ዓመት ግለሰብ በሽታው ተገኝቶበታል።

ከኮንጎ ጋር የሚዋሰኑ አገራት በአካባቢው በሚደረገው የሕዝብ እንቅስቃሴ፣ ንግድ እና ጉዞ ምክንያት ወረርሽኙ ይበልጥ ሊስፋፋባቸው የሚችል ከፍተኛ ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች ተብለው ተለይተዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ኡጋንዳ ወረርሽኙን ለመከታተል፣ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን ለመለየት እና የኢንፌክሽን መከላከያ እርምጃዎችን ለመተግበር የሚያስችሉ የአስቸኳይ ጊዜ ማዕከላትን እንዲያቋቁሙ መክሯል።

ስርጭቱን ለመግታት እንዲቻል በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች፤ በ48 ሰዓታት ልዩነት በሚደረጉ ሁለት የቡንዲቡግዮ ቫይረስ ምርመራዎች ነፃ መሆናቸው እስከሚረጋገጥ ድረስ ወዲያውኑ ለብቻ ሊለዩ እና ሕክምና ሊደረግላቸው እንደሚገባ ተቋሙ ገልጿል።

በሽታው መግባቱ የተረጋገጠባቸውን አገራት የሚያዋስኑ ጎረቤት መንግሥታት የቅኝት እና የጤና ሪፖርት ሥራቸውን እንዲያጠናክሩ ተነግሯቸዋል።

ወረርሽኙ ከተከሰተበት ቀጣና ውጭ ያሉ አገራት ድንበሮቻቸውን መዝጋት ወይም የጉዞ እና የንግድ እግድ መጣል እንደሌለባቸው የዓለም ጤና ድርጅት አስረድቷል። እንዲህ ዓይነቱ እርምጃዎች "ብዙውን ጊዜ ከፍርሃት በመነሳት የሚተገበሩ እንጂ ሳይንሳዊ መሠረት እንደሌላቸው" ገልጿል።

ኢቦላ በአውሮፓውያኑ 1976 ለመጀመሪያው ጊዜ የተገኘው አሁን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተብላ በምትታውቀው አገር ግዛት ውስጥ ሲሆን የተሰራጨውም ከሌሊት ወፎች እንደሆነ ይገመታል። በዓለም ላይ ከተከሰቱ ወረርሽኞች ውስጥ በገዳይነቱ 17ተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው ከሰውነት ከሚወጣ ፈሳሽ እንዲሁም ከተሰነጠቀ ቆዳ ጋር በሚኖር ቀጥታ ንክኪ ነው። በሽታው ከፍተኛ የደም መፍሰስ እና የሰውነት አካላት ከጥቅም ውጪ መሆንን ያስከትላል።

ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት 15,000 ገደማ ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸው አልፏል።