የጣሊያን ሚኒስትሮች በትምህርት ቤቶች ቡርቃ እና ኒቃብ እንዲከለከል ተስማሙ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የጣሊያን መንግሥት በትምህርት ቤቶች ውስጥ ቡርቃና ኒቃብ እንዲከለከል እንዲሁም በአንድ ክፍል ውስጥ ጣሊያንኛን በበቂ ደረጃ የማይናገሩ ተማሪዎች ቁጥር ላይ ገደብ እንዲጣል ወሰነ።

በውሳኔው መሠረት፣ በአንደኛ ዓመት የመጀመሪያ ደረጃ፣ የመካከለኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ክፍሎች ውስጥ የጣሊያን ዜግነት የሌላቸው ወይም የጣሊያን ቋንቋ እውቀታቸው ደካማ የሆኑ ልጆች መጠን ከ30 በመቶ እንዳይበልጥ ይደረጋል።

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ እርምጃውን "ሰዎችን የማይከፋፍል ይልቁንም ውህደትን የሚያግዝ" ሲሉ ገልፀዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን መንግሥት በመጪው ዓመት ከሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ በፊት የቀኝ-አክራሪው 'ፉቱሮ ናዚዮናሌ' ፓርቲ ፖሊሲዎች ደጋፊ መስሎ ለመታየት እየሠራ ነው በማለት ይወቅሳሉ።

የትምህርት ሚኒስትሩ ጁሴፔ ቫልዲታራ ገደቡ "ከዜግነት ይልቅ በቋንቋ ችሎታ ላይ የተመሠረተ" ነው ብለዋል። የኒቃብና የቡርቃ እገዳውን ደግሞ ከሥርዓተ-ፆታ እኩልነት ጋር በማያያዝ ለማስረዳት ሞክረዋል።

ሜሎኒ እሁድ ዕለት ስለ ዕቅዶቹ ሲገልፁ "ወደ ትምህርት ቤት ስትሄዱ ፊታችሁ ክፍት መሆን አለበት" ብለዋል። በተጨማሪም፣ በባህል ስም አንዲት ወጣት ሴት ራሷን እንድትሸፍን ማንም ሊወስንላት አይገባም ብለዋል።

አዋጁ ሐሙስ በተካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ከመጽደቁ በፊት፣ የተለያዩ ረቂቆች የተዘጋጁ ቢሆንም ዋና ዋና ዝርዝሮቹ ግልፅ ነበሩ።

የፊት መሸፈኛ ልብስ እገዳው በቡርቃ እና በኒቃብ ላይ ብቻ የሚተገበር ሲሆን፣ ፊትን ግልፅ አድርጎ የሚያሳየውን ሂጃብ ግን አይመለከትም።

ኒቃብ ፊትን የሚሸፍን መሸፈኛ ሲሆን በዓይኖች ዙሪያ ያለውን ክፍል ግን ግልፅ ያደርጋል። ሆኖም ከዚህ የፊት መሸፈኛ ጋር ተጨማሪ የዓይን መሸፈኛ ሊደረግበት ይችላል። ብዙውን ጊዜም ከራስ መሸፈኛ (ስካርፍ) ጋር ይለበሳል።

ቡርቃ ደግሞ ፊትን ጨምሮ መላ ሰውነትን የሚሸፍን ልብስ ነው። ብዙ ጊዜ በዓይን አካባቢ ለማየትየሚያስችል ወንፊት መሰል ይኖረዋል።

እንደ ፎንዳዚዮኔ የምርምር ተቋም መረጃ ከሆነ፣ በጣሊያን ትምህርት ቤቶች ከሚማሩ ተማሪዎች መካከል የጣሊያን ዜግነት የሌላቸው 11.6 በመቶ ናቸው።

ጣሊያንኛን በበቂ ደረጃ በማይናገሩ ተማሪዎች ላይ የተጣለው 30 በመቶ ገደብ በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች በተለያየ መንገድ የሚተገበር ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ይህ ገደብ የሚመለከተው የጣሊያን ዜግነት የሌላቸውና በጣሊያን ያልተወለዱ ወይም ቢያንስ ለሁለት ዓመታት የቅድመ መደበኛ ትምህርት (ነርሰሪ) ያልተከታተሉ ሕፃናትን ነው።

በዝቅተኛና በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ፣ ገደቡ የሚመለከታቸው የጣሊያን ዜግነት የሌላቸውን እና በጣሊያን የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ቢያንስ ሠስት ዓመታት በተሳካ ሁኔታ ያላጠናቀቁ ተማሪዎችን ነው።

የአካባቢ ትምህርት ቤት ቢሮዎች የጣሊያን ቋንቋ እውቀታቸው ውስን የሆኑ ተማሪዎችን በአካባቢው ባሉ ትምህርት ቤቶች አመጣጥነው እንዲያከፋፍሉ ይደረጋል። ይህ የማይቻል ከሆነ ግን ተጨማሪ የጣሊያንኛ ትምህርት በመስጠት የተለየ ፈቃድ ሊሰጥ ይችላል።

የትምህርት ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፣ የዚህ እርምጃ ዋና ዓላማ አንድ ዓይነት ማኅበረሰብ ብቻ ተሰባስቦ የሚማርባቸው ክፍሎች እንዳይፈጠሩ መከላከል ነው።

ይህ እርምጃ በአዋጅ መልክ የቀረበ ስለሆነ ወዲያውኑ ተፈጻሚ ሊሆን ይችላል። ሆኖም በ60 ቀናት ውስጥ በፓርላማው መጽደቅ ይኖርበታል።

ተቃዋሚዎች በበኩላቸው እቅዱ ከትምህርት ጉዳይ በላይ ፖለቲካዊ ዓላማ እንዳለው ይከራከራሉ።

ተቃዋሚዎች ሜሎኒ ለገዥው ጥምረት ስጋት ተደርጎ የሚታየውን እና የአክራሪ ቀኝ ዝንባሌ ያለውን የፉቱሮ ናዚዮናሌ ፓርቲ መሪ የሆኑትን የቀድሞ የጦር ጄኔራል ሮቤርቶ ቫናቺን ለማስደሰት እየሠሩ ነው ሲሉ ይከሳሉ።

ቫናቺ እርምጃዎቹን እንደሚደግፉ ተናግረዋል። እነዚህ እርምጃዎች ዓመታት በፊት መወሰድ ነበረባቸው ብለዋል።