ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ሐሙስ ከሰዓት ከመኖሪያ ቤታቸው መወሰዳቸውን ቤተሰቦቻቸው አረጋገጡ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ጠባቂዎቻቸው ተቀይረው፣ መኖሪያ ቤታቸው ከረቡዕ ምሽት አንስቶ በከፍተኛ ጥበቃ ሥር የዋሉት የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተደዳር ፕሬዝዳንት ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ በትግራይ ኃይሎች ከቤታቸው መወሰዳቸውን ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ አረጋገጡ።

ቢቢሲ በጄነራሉ ቤት ከሚኖሩ ምንጮች እና የቅርብ ሰዎቻቸው ሌ/ጄነራል ታደሰ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ከቤታቸው በታጣቂዎች መወሰዳቸውን አረጋግጧል።

ሌ/ጄነራል የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ የተቋቋመውን እና ለሁለት ዓመት የቆየውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን ከአቶ ጌታቸው ረዳ ተረክበው ለአንድ ዓመት ከመሩ በኋላ ሥልጣናቸው ለተጨማሪ ዓመት መራዘሙን ተከትሎ በህወሓት መሪዎች አስተዳደራቸው እንዲፈርስ መደረጉ ይታወሳል።

ከረቡዕ ሌሊት ጀምሮ በጄነራሉ መኖሪያ ቤት ዙሪያ የነበሩት የፀጥታ ኃይሎች ከሰዓት በኋላ "ይዘነው መሔድ አለብን፣ ታዝዘናል" ማለታቸውን ቢቢሲ ከቅርብ ምንጭ የሰማ ሲሆን፣ ሌ/ጄ ታደሰ ከቤት ሲወሰዱ ምንም ዓይነት የኃይል እርምጃም ሆነ ማንገላታት አልነበረም ብለዋል።

አክለውም ሌ/ጄነራል ታደሰ በራሳቸው ሾፌር እንዲቆዩ ይደረግበታል ወደተባለ ሆቴል መወሰዳቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል።

የሌ/ጄ ታደሰ የቤተሰብ አባል ለቢቢሲ እንደተናገሩት በሆቴሉ ሌሎች ሦስት የክልሉ ጊዘያዊ አስተደዳር የቀድሞ ባለሥልጣናት በተመሳሳይ ከቤታቸው ተወስደው ጥበቃ እየተደረጋላቸው እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ሌ/ጄ ታደሰን ቤተሰባቸው ማግኘት ይችል እንደሆነ የተጠየቁት ምንጫችን፣ ይዘዋቸው የሔዱት ኃይሎች "የእኛ ግዴታ ይዞ ወደ ሆቴል መውሰድ ብቻ ነው፣ ከዚህ በኋላ ያለው ጉዳይ የትግራይ ፖሊስን የሚመለከት ነው" የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው አስረድተዋል።

ጨምረውም ቤተሰብ ሌ/ጄነራል ታደሰን ጨምሮ በፀጥታ ኃይሎች ከቤታቸው የተወሰዱትን ሰዎች መጠየቅ ይችል እንደሆነ የሚታወቀው ከነገ አርብ ጀምሮ ነው ብለዋል።

ከረቡዕ ሌሊት አንስቶ በሌ/ጄነራል ታደሰ ቤት ዙሪያ የነበረው ከፍተኛ ጥበቃ ሐሙስ ከሰዓት ከወሰዷቸው በኋላም በአዳዲስ የፀጥታ ኃይሎች እየተጠበቀ መሆኑን እና አሁንም የውጭ ሰው ወደ መኖሪያ ቤታቸው መግባት እንደማይችል የቤተሰብ አባሉ ገልጸዋል።

ከሌ/ጄነራል ታደሰ በተጨማሪ ሌሎችም የቀድሞ የትግራይ ክለል ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሥልጣናት እና ወታደራዊ መኮንኖች ከቤታቸው ተወስደው በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ የቢቢሲ ምንጮች ተናግረዋል።

ይህ የቀድሞውን የክልሉን ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት በቁጥጥር ሥር የማዋል እንቅስቃሴ የተጀመረው ለወራት በውጥረት ውስጥ የነበረው የፌደራል መንግሥቱ እና የህወሓት ግንኙነት ወደ ግልጽ ወታደራዊ ግጭት ከተሸጋገረ ከሰዓታት በኋላ ነው።

ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ መስከረም 13/2019 ዓ.ም. ሌሊት በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ግጭቶች ከተቀሰቀሱ በኋላ የትግራይ ኃይሎች በክልሉ የሚገኙ ዋነኛ የአየር ማረፊያዎችን በቁጥጥራቸው ስር ማደረጋቸው የተሰማ ሲሆን ጦርነትም ያንን ተከትሎ መጀመሩ ታውቋል።

ህወሓት ለሁለት ዓመት በትግራይ ለተደረገው ደም አፋሳሽ ጦርነት አንድ ምክንያት በሆነው እና በፕሪቶሪያው ስምምነት ውድቅ በሆነው የተናጠል ምርጫ የተቋቋመውን ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ሚያዝያ መጨረሻ ላይ ወደ ሥልጣን መልሶ የክልሉን አስተዳደር መቆጣጠሩ ይታወሳል።

ሌ/ጄ ታደሰ በዚህ ሂደት ላለፉት አምስት ወራት ከአጠቃላይ የክልሉ አስተዳደር ተገልለው በአብዛኛው በቤታቸው ውስጥ ተወስነው እንደነበር ቢቢሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በህወሓት ሊቀመንበር በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው ካቢኔ የመጀመሪያውን ስብሰባ ባደረገበት ዕለት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ የጊዜያዊ አስተዳደሩ "ሥልጣን በጉልበት እየተያዘ" መሆኑን መናገራቸውም ይታወሳል።

ከወራት በፊት ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሌተናንት ጄነራል ታደሰ ቤተሰቦች "በቁም እስር ላይ ያሉ ያህል" እንደሚሰማቸው ገልጸው ነበር።

ከጥቂት ወራት በፊት የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ወደ መቀለ ተጉዘው ከሌተናንት ጄነራል ታደሰ ጋር እንዲነጋገሩ ቀጠሮ ይዘው የነበረ ቢሆንም "ከበላይ አካል የተላለፈ" በተባለ ትዕዛዝ ሳይገናኙ መቅረታቸው ተነግሯል።