ቀጥታ, አሜሪካ እና ኢራንን ወደ ድርድር ለመመለስ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ኳታር ገለጸች

በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚደረገውን ንግግር እንደገና ለመጀመር አደራዳሪ ቡድኑ ለሁለት ሳምንታት ለሚጠጋ ጊዜ በእቅዶች ላይ እየተወያየ መሆኑን ኳታር ገለጸች።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በጃፓን በተከሰተ አውሎ ንፋስ ምክንያት 2 ሚሊዮን ሰዎች ከአካባቢያቸው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተሰጠ

    በጃፓን በተከሰተ ከባድ አውሎ ንፋስ ምክንያት ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከሚኖሩበት አካባቢ ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተላለፈ።

    ዱጁዋን የተባለው ዝናብ የቀላቀለው ከባድ አውሎ ንፋስ በተለያዩ የጃፓን ግዛቶች ጉዳት እንደሚያስከትል ተገልጿል።

    የጃፓን የሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ከባዱ አውሎ ንፋስ “ሕይወትን አደጋ ላይ እንደሚጥል” አስታውቋል። በተለያዩ አካባቢዎች የተሰጠው ማስጠንቀቂያ እየለዘበ ቢመጣም በኦሺማ ከተማ አውሎ ንፋሱ ለሰዎች ሕይወት አስጊ ነው ተብሏል።

    ከፍተኛ መጠን ያለው ንፋስ በመነሳቱ ከ50,000 በላይ ሰዎች መብራት ተቋርጦባቸዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ በረራዎች እና የባቡር ጉዞዎችም ተሰርዘዋል።

    አውሎ ንፋሱ በከፍተኛ ኤል ኒኖ ምክንያት እንደተነሳ እና የንፋሱ ፍጥነት በሰዓት እስከ 130 ኪሎሜትር እንደሚደርስ ተገልጿል።

    ከፍተኛ ዝናብ እንዲሁም የመሬት መንሸራተት እንደሚከሰት ማስጠንቀቂያዎች ተሰጥተዋል።

    ዱጁዋን በጃፓን ዘንድሮ የተከሰተ 25ኛው አውሎ ንፋስ ነው። በርካታ መሰናዶዎች እንዲሰረዙም ምክንያት ሆኗል።

  2. አሜሪካ አደንዛዥ ዕፅ ጭነዋል ባለቻቸው ጀልባዎች ላይ ያደረሰችው ጥቃት ሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል መሆኑን ተመድ ገለጸ

    አሜሪካ አደንዛዥ ዕፅ ጭነዋል ባለቻቸው ጀልባዎች ላይ ያደረሰችው የአየር ጥቃት ዓለም አቀፍ ሕግን እንደሚጥስ እና ሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ተደርጎ እንደሚቆጠር የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው ሪፖርት አስታወቀ።

    የተመድ ልዩ ልዑክ ቤን ሳውል ያዘጋጁት ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ ካለፈው ዓመት መስከረም ጀምሮ በካሪቢያን እና በፓስፊክ ውቅያኖስ አሜሪካ ቢያንስ 68 ጥቃቶች ፈጽማለች።

    አሜሪካ ከግዛቷ ውጭ በሆኑት አካባቢዎች ባደረሰችው ጥቃት ከ220 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

    የተመድ ባለሙያ እንደተናገሩት፤ ዒላማ የተደረጉት ሰዎች የአሸባሪ ቡድን አባላት ናቸው በሚል የተለዩ ቢሆንም እንኳን በአሜሪካ ላይ ጥቃት አልፈጸሙም። ስለዚህም አሜሪካ በዓለም አቀፍ ሕግ ሥር ራሷን የመከላከል መብቷን መተግበር አትችልም።

    ከሁለት ቀናት በፊት የአሜሪካ ጦር በካሪቢያን በሚጓዝ ጀልባ ላይ ባደረሰው ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

    በቀጣናው የአሜሪካን ኃይሎች የሚመራው ሳውዝኮም “ጀልባዎቹ አደንዛዥ ዕፅ እያዘዋወሩ እንደነበር የተረጋገጠ የደኅንነት መረጃ ይጠቁማል” ብሏል።

    የተመድ የሰብአዊ መብቶች ካውንስል በበኩሉ “እንዲህ ያሉ ጥቃቶች ከሕግ ውጭ ከሚፈጸሙ ግድያዎች ጋር ይስተካከላሉ” ብሏል።

    “በዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት፣ በዓለም አቀፍ ራስን የመከላከል መብት፣ በዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ፣ በፀረ አደንዛዥ ዕፅ ድንጋጌ እና በዓለም አቀፍ ፀረ ሽብር ሕግ ተቀባይነት ስለሌላቸው በሕይወት የመኖር መብትን ይጋፋሉ” ሲልም አክሏል።

    አሜሪካ ባደረሰቻቸው 68 ጥቃቶች 223 ሰዎች መገደላቸው “በዓለም አቀፍ ሕግ ሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል” እንደሆነ የተመድ ሪፖርት ይጠቁማል።

    ቢቢሲ ከዋይት ሀውስ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ ጠይቋል።

  3. በሁሉም የኢራን አየር መንገዶች ላይ የተጣለው ማዕቀብ ከነገ ጀምሮ እንደሚተገበር ተገለጸ

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሳንት ከነገ ጀምሮ “ሁሉም የኢራን አየር መንገዶች በረራ ማከናወን አይችሉም” ሲሉ አስታወቁ።

    ከሁለት ሳምንት በፊት የአሜሪካ ግምጃ ቤት 27 የኢራን አየር መንገዶች ላይ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል።

    ከኢራን ጋር የሚደረገው ውጊያ እስከመቼ እንደሚቀጥል እንደማያውቁ የተናገሩት ኃላፊው፤ ማዕቀቡን በተመለከተ ከቻይና ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።

    የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንግፒንግ ከሁለት ቀናት በኋላ ወደ አሜሪካ ተጉዘው በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ይመክራሉ።

    የሁለቱ አገራት መሪዎች ኢራን ላይ ስለተጣለው ማዕቀብ እንዲወያዩ ለማመቻቸት የቻይና ምክትል ፕሬዝዳንት ዋንግ ይ እና የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሳንት እንደሚነጋገሩ ተገልጿል።

    የአሜሪካ መንግሥት ኢራን ላይ የምጣኔ ሃብት ጫና ለማሳደር ባንኮች፣ የንግድ ተቋማት፣ የቴክኖሎጂ እና በረራ ዘርፎች ላይ ማዕቀብ እንደሚጥል ከሳምንታት በፊት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

  4. ትራምፕ ወደ ዋይት ሀውስ እንዳይገቡ ያገዷቸው መገናኛ ብዙኃን ክስ ሊመሠርቱ ነው

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሀውስ እንዳይገቡ ያገዷቸው መገናኛ ብዙኃን ክስ እንደሚመሠርቱ አስታወቁ።

    ሲኤንኤን፣ ፖለቲኮ እና ኤምኤስ ናው ወደ ዋይት ሀውስ እንዳይገቡ በፕሬዝዳንቱ የታገዱት ባለፈው ሳምንት አርብ ነበር።

    ትራምፕ መገናኛ ብዙኃኑ ስለ አስተዳደራቸው “የፈጠራ እና ሐሰተኛ” መረጃ አውጥተዋል ሲሉ ወንጅለዋል።

    ቅዳሜ ዕለት ጋዜጠኞች ወደ ዋይት ሀውስ ለመግባት ሲሞክሩ እንዳልተፈቀደላቸው እና የይለፍ ካርዳቸውን እንደተነጠቁ መገናኛ ብዙኃኑ ገልጸዋል።

    ሦስቱ መገናኛ ብዙኃን ዛሬ በጋራ ባወጡት መግለጫ “የመጀመሪያው አንቀጽ የሚሰጠንን መብት ለማግኘት እና ይህ መንግሥት ጋዜጠኞች ምን እንደሚዘግቡ እንደማይወስን ለማሳየት ክስ እንከፍታለን” ብለዋል።

    የአገሪቱ ሕገ መንግሥት የመጀመሪያ አንቀጽ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃንን ነጻነት እንዳያፍን ያግዳል።

    መገናኛ ብዙኃን በዘገባቸው ምክንያት መድልዎ እንዳይደርስባቸውም ከለላ ይሰጣል።

    መገናኛ ብዙኃኑ ባወጡት መግለጫ “ያለ ማስጠንቀቂያ ወይም ሒደቱን ሳይከተል ዋይት ሀውስ የጋዜጠኞቻችን ፈቃድ ሰርዟል” ብለዋል።

    አክለውም “ዝም ከተባለ የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት እና ሕዝብ ነጻ መረጃ የማግኘት መብቱ በመንግሥት ይጣሳል” ብለዋል።

    ቢቢሲ ከዋይት ሀውስ ምላሽ ጠይቋል።

  5. በምዕራብ ወለጋ በታጣቂዎች ታግተው የነበሩ አሽከርካሪዎች መለቀቃቸውን ማኅበሩ ገለፀ

    በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጊምቢ ከተማ አቅራቢያ በታጣቂዎች ታግተው የነበሩ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች መለቀቃቸውን ማኅበሩ ለቢቢሲ ገለፀ።

    የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ዘውዱ፣ እሑድ ጳጉሜ 1/2018 ዓ.ም. በተፈፀመው ጥቃት የታገቱ አሽከርካሪዎች መለቀቃቸውን ስለማረጋገጠቻው ተናግረዋል። የተለቀቁት የማኅበሩ አባላት የነበሩት የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ዘጠኝ መሆናቸውን አቶ ሰለሞን ገልፀዋል።

    የማኅበሩን አባላት ጨምሮ በወቅቱ የታገቱት አጠቃላይ ታጋቾች ቁጥር ከ13 እስከ 14 እንደሚደርስ አስታውሰው ሁሉም ስለመለቀቃቸው መረጃ የደረሳቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

    ታጋቾቹ እንዴት ሊለቀቁ እንደቻሉ ወይም ለታጣቂዎች ገንዘብ ተከፍሎ እንደሆነ የጠየቅናቸው አቶ ሰለሞን፣ ስለዚህ ጉዳይ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

    ታጣቂዎች ከሁለት ሳምንት በፊት ፈፀሙት በተባለው የምዕራብ ወለጋው ጥቃት ከዘጠኝ ያላነሱ ነዳጅ ጫኝ ከባድ ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል መቃጠላቸውን ቢቢሲ ከምንጮች እና ከሳተላይት ምሥል አረጋግጧል።

    ታጣቂዎቹ መኪኖቹን በተኩስ አስቁመው አሽከርካሪዎቹን አፍነው እንደወሰዷቸው እና ተሽከርካሪዎቹን በእሳት እንዳቀጣጠሉ ምንጮቻችን ገልፀዋል።

    የታገቱት አሽከርካሪዎች ከሁለት ሳምንታት ያህል እገታ በኋላ ከሦስት ቀናት በፊት ዓርብ መስከረም 8/2019 ዓ.ም መለቀቃቸውን ነው የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበርፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ዘውዱ የተናገሩት።

    አካባቢው “የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንዲሁም በይፋ የሚታወቅ ስም የሌላቸው በቡድን የተደራጁ ታጣቂዎች” የሚንቀሳቀሱበት እንደሆነ አንድ የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣን የገለፁ ሲሆን፣ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል ግን የለም።

  6. የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የትግራይ ቴሌቪዥንን ማገዱን አስታወቀ

    የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የትግራይ ቴሌቪዥን “የአገርን እና የሕዝብን ደኅንነት”፣ “ብሔራዊ ጥቅምን አደጋ ላይ የሚጥሉ”፣ “ወደ ግጭት የሚገፋፉ” እንዲሁም “ጽንፈኝነትን የሚያበረታቱ መልዕክቶች” እያስተላለፈ መሆኑን በመግለጽ ማገዱን አስታወቀ።

    ባለሥልጣኑ ሰኞ መስከረም 11/2019 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከዚህ በፊት የቴሌቪዥን ጣቢያው ታግዶ እንደነበር አስታውሶ፣ ህወሓት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የተፈራረመውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ተከትሎ እገዳው ተነስቶለት እንደነበር ገልጿል።

    የትግራይ ቴሌቪዥን ላይ የተጣለው እገዳ ላልተወሰነ ጊዜ መሆኑን ጨምሮ አስታውቋል።

    ባለሥልጣኑ አክሎም የትግራይ ቴሌቪዥንን እንደ መረጃ ምንጭ መጠቀምም ሆነ የሚያሰራጫቸውን ዘገባዎች ማሰራጨት "በጥብቅ የተከለከለ" መሆኑን ጨምሮ ገልጿል።

    ህወሓት እና ሌሎች በአገሪቱ ስድስት ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በዕሁድ ዕለት “ትብብር ለኅልውና” የሚል ጥምረት መመሥረታቸው ይታወሳል።

    የትብብሩ ምሥረታን በሚመለከት ሰብሳቢው ዘመነ ካሴ መግለጫውን በትግራይ መገናኛ ብዙኃን ላይ አንብቧል።

    ትብብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥትን በመጣል "በሽግግር ቻርተር የሚመራ አካታች የሽግግር መንግሥት" ለመመሥረት ዓላማ እንዳለውም አስረድተዋል።

    የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከዚህ ቀደም የአዲስ ስታንዳርድ እና የዋዜማ ሬዲዮን የምዝገባ ፈቃዶች የሰረዘ ሲሆን፣ የሮይተርስ ጋዜጠኞች የዘገባ ፈቃድም ከሰረዘ በኋላ በቅርቡ መልሶ ሰጥቷል።

  7. ኤምኤስኤፍ በጋምቤላ ውስጥ በርካታ የቆሰሉ ሰዎች ወደ ጤና ጣቢያው መምጣታቸውን አስታወቀ

    መንግሥታዊ ያልሆነው ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) በጋምቤላ ክልል ውስጥ በሚገኘው ኩሌ ጤና ጣቢያ በርካታ የቆሰሉ ሰዎችን እያከመ መሆኑን ገለጸ።

    ባለፈው አርብ መስከረም 8/2019 ዓ.ም. በክልሉ ኢታንግ ልዩ ወረዳ ውስጥ የተፈጸመ ጥቃትን ተከትሎ የተጎዱ ሰዎች ናቸው ወደ ጤና ጣቢያው የመጡት።

    ጤና ጣቢያው በጥቃቱ የተጎዱ 88 ሰዎችን የተቀበለ ሲሆን፣ ከመካከላቸውም ስምንቱ የሞቱ ሲሆን ሌሎች አራት ሰዎች ወደ ጤና ጣቢያው ከሄዱ በኋላ በሕክምናው ቡድን ሕይወታቸውን ለማትረፍ ጥረት ቢደረግም መትረፍ አለመቻላቸውን ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን አስታውቋል።

    ከከባድ እስከ ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው የቀሩት ተጎጂዎች ሕክምና ማግኘታቸውን እና 13 ሰዎች ለተጨማሪ የሕክምና ድጋፍ ወደ ጋምቤላ ሆስፒታል መላካቸውን ቡድኑ ገልጿል።

    ናይሮቢ ኬንያ የሚገኙት የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን የኢትዮጵያ ኃላፊ ጉል ባድሻህ “እኛ በዋናነት ቅድሚያ የምንሰጠው የተጎጂዎችን ማንነት ከግምት ውስጥ ሳናስገባ ለማንኛውም ሰው የሚያስፈልገውን የሕክምና ድጋፍ ነው" በማለት "የግጭቱ ተሳታፊዎች ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ እንዲያደርጉ" ጥሪ አቅርበዋል።

  8. ኢራን በቴህራን የሚገኝ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ማዕከልን መዝጋቷን ተከትሎ ፈረንሳይ የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ ዛተች

    ፈረንሳይ በቴህራን የሚገኘው የቋንቋ ትምህርት ቤቷ መዘጋቱን ተከትሎ የኢራንን አምባሳደር ጠርታ እንደምታነጋግር አስታወቀች።

    የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፓስካል ኮንፋቭሩክስ “ይህ ፈረንሳይ በኢራን ባላት የባሕል ማዕከል ላይ የተቃጣ ጥቃት በሐምሌ ወር በሁለት የኤምባሲ ሠራተኞቻችን ላይ ከተፈጸመው የቀጠለ ሲሆን ምክንያት እና ተቀባይነት የሌለው ነው” ብለዋል።

    እሁድ ዕለት የኢራን ባለሥልጣናት በቴህራን የሚገኝ የፈረንሳይ የቋንቋ ማዕከል በአቃቤ ሕግ ትዕዛዝ መሠረት መዘጋቱን አስታውቀዋል።

    ከኢራን የፍትህ ተቋማት ጋር በቅርበት የሚሰራው ሚዛን የዜና ወኪል “በቴህራን ከሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር ግንኙነት ያለው እና በማስተማር ሽፋን ለዓመታት ሲንቀሳቀስ የነበረው ሕገወጥ ማዕከል ተዘግቷል” ሲል ዘግቧል።

    የኢራን የፍትህ አካላት “ከዲፕሎማሲ ስምምነት ውጪ ያፈነገጠ ሕገወጥ ተግባር ላይ ተሰማርቷል” ሲል ወንጅሎታል።

    አክሎም ማዕከሉ "የቋንቋ ማሰልጠኛ ተቋምነቱን አላግባብ ተጠቅሟል" እንዲሁም "የአገሪቱን ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በመለየትና በመካከላቸው ትስስር በመፍጠር፣ ከአገር እንዲወጡም አመቻችቷል" ሲል ከስሷል።

    ፈረንሳይ የቀረቡባትን ውንጀላዎች ውድቅ አድርጋ ከቅርብ ወራት ወዲህ ተደጋጋሚ ትንኮሳዎች እንዳጋጠሟት አስታውቃለች።

    ከቅርብ ወራት ወዲህ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ውጥረት እየተባባሰ መጥቷል።

    ባለፈው ወር ፈረንሳይ ወደ ኢራን ያቀኑ ሁለት ዲፕሎማቶቿ ለአጭር ጊዜ መታሰራቸውንና እንቅስቃሴያቸው መገደቡን ተከትሎ ሁለት የኢራን ዲፕሎማቶችን ከአገሯ አስወጥታለች።

    ቴህራን ዲፕሎማቶቹን በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ወንጅላቸዋለች።

  9. አሜሪካ እና ኢራንን ወደ ድርድር ለመመለስ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ኳታር ገለጸች

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ንግግር ለመጀመር አደራዳሪ ቡድኑ ለሁለት ሳምንታት ለሚጠጋ ጊዜ በእቅዶች ላይ እየተወያየ መሆኑን ኳታር ገለጸች።

    የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማጂድ አል አንሳሪ “ዋሽንግተንን እና ቴህራንን ወደ ድርድር ለመመለስ ለሁለት ሳምንት ለሚጠጋ ጊዜ የተለያዩ ሃሳቦችን እየተለዋወጥን ነው” ማለታቸውን የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

    ኳታር ከፓኪስታን ጋር በመሆን ሁለቱን ወገኖች ስታደራድር ቆይታለች።

    “ድርድሩን መጀመር ይቻል እንደሆነ በአደራዳሪ ቡድናችን በኩል ከቴህራን እና ከዋሽንግተን ጋር እየሰራን ነው። አደራዳሪዎችም በዚህ ሒደት ላይ ለውጥ ለማምጣት እየተንቀሳቀሱ ነው።” ብለዋል አል አንሳሪ።

    ቃል አቀባዩ ጨምረውም አካባቢውን ለማረጋጋት እና እንደ የሆርሙዝ ወሽመጥ ያሉ የባሕር መስመሮችን ለመጠበቅ ዓለም አቀፍ መረዳትን ለማምጣት ቀጣናዊ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

    "የባሕር መስመሮችን ከአንድ አገር ሉዓላዊነት ጋር ማያያዝ እና እንደ መሣሪያ መጠቀም ለሁላችንም አደገኛ ነው” ብለዋል።

    አሜሪካ በቅርቡ በኢራን ላይ ወታደራዊ ጥቃት ከፈፀመች በኋላ ወሽመጡን ሊያስከፍት ይችላል የሚል ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ድርድር ተቋርጧል።

    ኢራንም ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ በአረብ አገራት በሚገኙ የአሜሪካ መሠረተ ልማቶ ችላይ ጥቃት በመፈፀም ምላሽ ሰጥታለች።

    የተወሰኑ ጥቃቶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሱ ሲሆን በሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይም ውድመትን አስከትለዋል።

    በጥቃቱ ዒላማ የሆኑ አገራትም ጥቃቱን አውግዘው ኢራን ይህንን ድርጊቷን እንድታቆም ጥሪ አቅርበዋል።

    የካቲት ወር ላይ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በከፈቱት ጦርነት ከ3000 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ቴህራን አስታውቃለች። ኢራንም በወሰደችው የአፀፋ ጥቃት አሜሪካውያን እና እስራኤላውያን መገደላቸውን ገልጻለች።

    ኳታር አሁን ላይ ሁለቱን ወገኖች ወደ ድርድር ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለፀችው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በመካከለኛው ምሥራቅ ባለው ውጥረት ምክንያት በአካባቢው ለሚኖሩ ዜጎቹ እሁድ ዕለት የደኅንነት ማስጠንቀቂያ ካወጣ በኋላ ነው።

    ሚኒስቴሩ በቀጣናው የሚኖሩ ዜጎቹ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና ከቀጣናው ውጭ ያሉ ወይም በዚያ የሚያልፉም የሚያደርጉትን ጉዞ እንዲያጤኑ አሳስቧል።

    የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ኢራቅ እና ጆርዳንን ጨምሮ በቀጣናው ያሉ በርካታ የአሜሪካ ኤምባሲዎችም እሁድ ዕለት ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ አውጥተዋል።