ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስለትብብሩ እና ስለ ቀጣይ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ታዋቂዎቹ ፖለቲከኞች ጃዋር እና ልደቱ ምን ይላሉ?
አቶ ልደቱ አያሌው እና አቶ ጃዋር መሐመድ በሰባት ታጣቂ ኃይሎች የተመሠረተውን ፀረ-መንግሥት ትብብር በተመለከተ የተለያየ አቋም አላቸው።
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ)ን ጨምሮ በስድስት ክልሎች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሰባት አማጺያን 'ትብብር ለኅልውና' የተባለ ጥምረት መመሥረታቸውን መስከረም 10/2019 ዓ.ም. አስታውቀዋል።
ቢቢሲ ትብብሩን በተመለከተ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ ልደቱ አያሌው የተለያየ ምልከታቸውን አጋርተዋል።
ሁለቱም ፖለቲከኞች የትብብሩን ምሥረታ አስፈላጊነት በተለያየ አገላለፅ ቢያምኑበትም በሂደቱ፣ በትብብሩ አባላት የእርስ በርስ ግንኙነት እና በቀጣይ ውጤቱ ላይ ግን ልዩነቶችን አንፀባርቀዋል።
አማጺያኑ "መጣመራቸውን አልተቃወምኩም፤ መጣመራቸው ጥሩ ነው፤ እነዚህ ኃይሎች እንዲቀራረቡ እፈልጋለሁ" የሚሉት አቶ ጃዋር፤ ነገር ግን ይህ ትብብር "ስትራቴጂክ [ስልታዊ] አይደለም" ሲሉ ይተቻሉ።
ትብብሩ አገርን ማረጋጋት የሚችል ሳይሆን "የአጭር ጊዜ ታክቲካል ጥምረት" እንደሆነ ነው የሚያምኑት።
የትብብሩ አባላት የሆኑት በተለይ ኦነሠ፣ ህወሓት እና አፋብን በመካከላቸው ከርዕዮተ-ዓለም ባሻገር የመሬት ይገባኛልን ጨምሮ ሌሎች ልዩነቶችም እንዳሏቸው የሚያነሱት አቶ ጃዋር፣ ትብብር የመሠረቱት "እነዚህን ልዩነቶቻቸውን ለጊዜው በማቆየት አርስ በርሳቸው በጎንዮሽ ላለመጋጨት እና በአንዳንድ ነገሮች ላይ ለመደጋገፍ ብቻ ነው" ይላሉ።
በመሆኑም "በጉዟቸው ላይ እንቅፋት ሊመታቸው ይችላል፤ ብዙ ላይሔዱ ይችላሉ" ይላሉ። ትብብሩ ጠለቅ ያለ የፖለቲካ ውይይት እና ድርድር እንዲሁም ስምምነት የተደረገበት እነዳልሆነም ይገልጻሉ።
ከዚህም የተነሳ "ሥርዓቱን ለማስወገድ በሚያደርጉት ጉዞም ሆነ ከዚያ በኋላ በምትኖረው ኢትዮጵያ ላይ አስተማማኝ የሆነ መሠረት ያለው አይደለም" ባይ ናቸው።
"ተባብረው እና ተረባርበው ሥርዓቱን ቢጥሉት እንኳን፣ ከዚያ በኋላ እርስ በርሳቸው የሚዋጉ ነው የሚሆኑት። ይሔ የግማሽ ፍጻሜ ዓይነት ስምምነት ነው። ለዋንጫ እርስ በርሳቸው ለመግጠም የተስማሙ ነው የሚመስለው" በማለት ትብብሩ ጥልቀት የጎደለው መሆኑን ተናግረዋል።
ሆኖም የትብብር "ሙከራውን እወደዋለሁ" የሚሉት ፖለቲከኛው፣ "ግን አሁንም ጠለቅ ያለ የፖለቲካ ይዘት ያለው ውይይት እና ድርድር ማድረግ ጠቃሚ ነው ባይ ነኝ" ይላሉ።
አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው በጃዋር ሀሳብ አይስማሙም።
ከአቶ ጃዋር በተለየ መልኩ ትብብሩ አገርን ለማረጋጋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ነው አቶ ልደቱ የሚያምኑት።
በከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ የነበሩ እና አንዳቸው ሌላኛቸውን በጠላትነት ሲያዩ የነበሩ ኃይሎች ወደ ትብብር መምጣታቸው አዎንታዊ እርምጃ እንደሆነ ነው አቶ ልደቱ የሚያምኑት።
በተጨማሪም "በሕዝብ ዘንድ ከባድ ተቀባይነት ያላቸው፣ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ናቸው" የሚሏቸው የእነዚህ ኃይሎች ፉክክር የአገሪቱን ሰላም እና ኅልውና በሚመለከት ትልቅ አንደምታ ይኖረዋል" ይላሉ።
እናም "እርስ በርስ ከመወጋጋት እና በጠላትነት ከመተያየት አገራዊ በሆነ ጉዳይ ላይ አንድ ትብብር ፈጥረን እንታገላለን" በማለት የመተባበር ፍላጎታቸውን ከገለፁበት ጊዜ ጀምሮ በድጋፍ መቀጠላቸውን ተናግረዋል።
በሰላማዊ ትግል ላይ ያላቸው አቋም የፀና መሆኑን የሚገልፁት አቶ ልደቱ፣ ነገር ግን በሰላማዊ መንገድ ለውጥ መምጣት አለበት ብለው የሚያምኑ ኃይሎች አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ተቀባይነት ማግኘት እንዳልቻሉ ያስረዳሉ። "መንግሥትም፣ አብዛኛው ተቃዋሚም፣ አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍልም ሰላማዊውን መንገድ ሊቀበለው አልቻለም" የሚል ድምዳሜ አላቸው።
በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ "ገዢ ሆኖ የወጣው እና ተቀባይነት ያገኘው አስተሳሰብ በትጥቅ ትግል ለውጥ ማምጣት አለብን የሚለው" በመሆኑ "ዕጣ ፈንታችንን እና ኅልውናችንን የሚወስኑት እነሱ [ታጣቂዎች] ሆነዋል" ይላሉ።
መንግሥትን "ለሰላም ድርድር እና ለውይይት በሩን ጥርቅም አድርጎ ዘግቷል ብለው የሚከሱት" አቶ ልደቱ፣ እናም የትጥቅ ትግል "አይቀሬ ሆኖ አፍጥጦ መምጣቱ የሚጠበቅ እንደሆነ" አጽንዖት ሰጥተዋል።
የትጥቅ እንቅስቃሴው ግን የሁሉንም የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስን መሆኑን በማንሳት፣ የትብብሩ ኃይሎች ሊፈጥሩት የሚችሉትን አደጋ መቀነስ እና ማስወገድ እንዲችሉ "እንደ ዜጋ አስተያየት የመስጠት ኃላፊነት ብቻ አይደለም ግዴታም አለብን" ካሉ በኋላ፣ ይህ ደግሞ "የትጥቅ ትግልን መደገፍ አይደለም" ሲሉ አስምረዋል።
የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ ኃይሎች ዘላቂ ለውጥ ያመጣሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልፀው፣ ነገር ግን ከዚያ በመለስ ያሉ የተለያዩ ጥቅሞችን ያስገኛሉ ብለው ያምናሉ።
ትብብሩ መንግሥትን ለሰላማዊ ድርድር በማስገደድ የሰላም ዕድል መፍጠር እንደሚችል ያምናሉ። "አገዛዙ የማይቀበል ከሆነ ደግሞ በቀላሉ እና በአጭር ጊዜ አገዛዙን ለማሸነፍ ዕድል ይፈጥራል" ሊሉም ተናግረዋል።
ፍልሚያው በሁለት ኃይሎች መካከል እንዲሆን በማድረግ በሰው እና በንብረት ላይ የሚደርሰው ጉዳት በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ እንደሚያስችልም ነው የሚገልፁት።
በተጨማሪም እነዚህ ኃይሎች ለድል ከበቁ ሁሉን አቀፍ የሆነ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት እንዲሁም በመካከላቸው ያሉ ቅራኔዎችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁነታቸውን መግለጻቸውን በመጥቀስ፣ የአገሪቱን ኅልውና በማስቀጠል ረገድ የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የተናገሩት።
ትብብሩ እስከምን ሊዘልቅ ይችላል?
አቶ ጃዋር፣ ትብብሩ "ዘላቂ ሆኖ ለድል መብቃት በጣም ይከብደዋል" ይላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ሊጫወትባቸው የሚችልባቸው ብዙ ካርዶች አሉ" የሚሉት አቶ ጃዋር፣ ትብብሩ እነዚህን ካርዶች ሊከብዱት ስለሚችሉ "ብዙ ቦታ ላይ እንቅፋት ይገጥመዋል" የሚል እምነት አላቸው።
መንግሥትን እንኳን ከሥልጣን ማስወገድ ቢችሉ፣ በመቀጠል የጋራ አገር ለመመሥረት እንደሚከብዳቸው ይገልፃሉ። "ሊለያዩ እንኳን ቢችሉ በሰላም ለመለያየት የሚያስችል ጠለቅ ያለ እና ደፈር ያለ የፖለቲካ ስምምነት ላይ አልተደረሰም" ብለውም ይሰጋሉ።
የኦነሠ፣ የፋኖ እና የህወሓት አመራሮች በተለያየ መልኩ ያደረጓቸውን ሰሞነኛ ንግግሮች ለዚህ በማሳያነት ያነሱት አቶ ጃዋር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ትብብሮች በተደጋጋሚ ተፈጥረው ፈርሰዋል፤ የሚፈርሱት ደግሞ ጠለቅ ብለው የረጅም ጊዜ ነገሮችን ተወያይተው ከመስማማት ይልቅ በጊዜያዊ ስምምነት እና የጋራ ጠላት ላይ ብቻ አነጣጥረው በመሄዳቸው ነው" ይላሉ።
በመሆኑም "የጋራ ጠላታቸውን ራሱ ሳይጥሉ እርስ በርሳቸው የሚጣሉበት ሁኔታ ነው ተደጋግሞ ያየነው" ሲሉ አብራርተዋል።
እነዚህ ኃይሎችም ልዩነቶቻቸውን አሁን ይፍቱ የሚል አስቸኳይ አቋም እንደሌላቸው የሚናገሩት አቶ ጃዋር፣ ይሁን እንጂ "የመፍቻ ዘዴ ላይ አልተወያዩበትም" ይላሉ። እናም ልዩነቶቻቸውን "ሊፈቱት አይደለም የመፍቻው ዘዴ ላይ ራሱ ደፍረው ለመወያየት አልሔዱበትም" ሲሉ ተችተዋል።
ከዚህም በመነሳት ትብብሩን ይፋ ለማድረግ "ቸኩለዋል" ብለው ያምናሉ። "ሴንሲቲቭ [ስሱ] ነገሮችን መንካት በውስጣችን ሌላ ችግር ይፈጥርብናል የሚል ጥርጣሬ አላቸው" ያሉ ሲሆን፣ ትብብሩ ሰፋ ያለ ውይይት ሳይደረግበት የይድረስ ይድረስ እንደሆነ ይከራከራሉ።
ይህን ሃሳብ የሚቃወሙት አቶ ልደቱ በበኩላቸው፣ የትብብሩ ምሥረታ "እንዲያውም ዘግይቷል" ይላሉ። ልዩነቶችን የሚፈቱበት ዘዴም እንዳላቸው ነው የሚያምኑት።
"የዛሬ ዓመት ወይም ሁለት ዓመት ይህን አድርገውት ቢሆን ኖሮ ብዙ ዋጋ ከመክፈል መዳን ይቻል ነበረ" ያሉት አቶ ልደቱ፣ "ከዚህ በኋላ እስከመቼ ነው ሊጠበቅ የሚችለው? ዘግይቷል እንጂ ፈጠነ ሊባል አይችልም" ባይ ናቸው።
"ትብብር ለመፍጠር ተዘጋጅተናል ካሉ እኮ ከዓመት በላይ ሆናቸው ከ20 በላይ ስብሰባ አካሒደናል ነው ሚሉት" በማለት በዝግጅት የተመሠረተ እንደሆነ ነው የሚከራከሩት።
በትብብሩ ኃይሎች መካከል ያለው ልዩነት አብሮ ለመቀጠል ስጋት ይሆናል ብለው እንደማያምኑ ሲያስረዱ ደግሞ "ልዩነት ሳይኖራቸው ተባበርን ቢሉ አይደንቀንም ነበር" የሚሉት አቶ ልደቱ፣ "የገረመን የገነገነ ልዩነት እያላቸው ለጋራ ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥተው በጋራ በመቆማቸው ነው" ሲሉ አክለዋል።
በተለይ በከፍተኛ መጠን የታጠቁ ናቸው የሚሏቸው ሦስቱ ኃይሎች፣ ከዚህ ቀደም ልዩነቶቻቸውን በኃይል ብቻ የመፍታት ፍላጎት እንደነበራቸው በማስታወስ፣ ከአቶ ጃዋር በተለየ መልኩ ልዩነቶቻቸውን እና ቅራኔዎችን "በሰላማዊ መንገድ በውይይት፣ በድርድር፣ በሕግ ማሻሻያ፣ በሕዝብ ውሳኔ እንፈታለን ብለው በዘዴው ላይ ተስማምተዋል" ይላሉ። ለዚህም በመግለጫቸው የገቡትን ቃል በማሳያነት ይጠቅሳሉ።
በችግር መፍቻው ዘዴ ላይ ከመስማማት ባለፈ፣ በሕዝብ የተመረጡ ባለመሆናቸው ልዩነታቸውን አሁን ቁጭ ብለን "በጠረጴዛ ዙሪያ እንፍታ የማለት መብትም የላቸውም" ብለው ያምናሉ።
አጀንዳዎቻቸውን እንደያዙ በመታገል "መንግሥት ከወደቀ በኋላ በሽግግር ሂደት በሰላማዊ መንገድ እንፈታቸዋለን" ብለው መስማማታቸውን በመጥቀስ ትክክለኛውም አካሔድ ይህ እንደሆነ የሚያምኑ መሆኑን ያስረዳሉ።
"በቃል፣ በጽሁፍ ተስማምተዋል። ይሔን አክብረው እንዲሄዱ ግፊት ማድረግ እና ክትትል እያደረግን ከዚያ ሲወጡ ልክ አይደላችሁም ብሎ መገሰጽ ነው ከእኛ ሚጠበቀው" ሲሉም ተናግረዋል።
አክለውም "ሁሉም በዚህ ስምምነት እጠቀማለሁ ብሎ ነው ወደ ስምምነት የመጣው። ለራሳቸው ሲሉ ተባብረው መቀጠል ነው ያለባቸው" ብለዋለ።
የውጭ ኃይሎች ሚና
ምንም እንኳን የትብብሩ አባላት በይፋ ባይገልፁም፣ በትብብሩ ውስጥ የተለያዩ አገራት እጅ እንዳለበት አቶ ጃዋር ያምናሉ። አቶ ልደቱም እንዲሁ የውጭ ኃይሎች እንዳሉበት ይገምታሉ።
ኤርትራ በቀጥታ ተሳትፎ እንዳላት ግልፅ ነው የሚሉት አቶ ጃዋር፣ ግብፅ እና ሱዳንም በቀጥታ ተሳትፎ እንዳላቸው ጠቅሰው "ሳዑዲ አረቢያም ከቀይ ባሕር ጋር በተያያዘ በገደምዳሜ ልትኖር ትችላለች" ብለዋል። በመንግሥት ጎን ደግሞ ኤሚሬቶች እና የእስራኤል መንግሥት "በቀጥታ እየተሳተፉበት ነው" ብለው ያምናሉ።
በመሆኑም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሔደው ግጭት ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንደሚኖረው ተናግረዋል። "እንዲህ ዓይነት ግጭት ውስጥ ስትገባ ደግሞ ዐቢይን አወርዳለሁ ብለህ ኢትዮጵያን ብትንትኗን ልታወታ የምትችልበት ዕድል ስላለ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብህ። ለዚህ ነው ጠለቅ ያለ ውይይት የሚያስፈልገው" ብለዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፣ ትብብሩ በችኮላ እንዲፈፀም እያደረጉ ያሉት ከፍተኛ የኅልውና ጥያቄ ያለባቸው ህወሓት እና የኤርትራ መንግሥት ናቸው። በመሆኑም "ሳይቀድመን እንቅደመው፤ ጦርነቱን በተቻለ መንገድ ከድንበራችን እናርቀው" በሚል እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ይገልፃሉ።
አቶ ልደቱ ደግሞ የውጭ ኃይሎች ተሳትፎ እንደሚኖር ቢገምቱም፣ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዳላቸው ግን በእርግጠኝነት ለመናገር አልደፈሩም።
"እንደዚህ ዓይነት ማንንም በኃይል አንበረክካለሁ የሚል መንግሥት ባለበት፣ ታጣቂ ኃይሎች ፈለግንም አልፈለግንም ከውጭ ኃይሎች ጋራ ሊተባበሩ ይችላሉ" ያሉ ሲሆን፣ ነገር ግን "አገር ውስጥ ያሉ ኃይሎች ከተባበሩ በቂ ናቸው፤ የውጭ ኃይል እገዛ አያስፈልጋቸውም" ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
"በተለይ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ናቸው ከምንላቸው ኃይሎች ጋራ መተባበር ከሞራልም ከሉዓላዊነትም አንጻር ትክክል ነው የሚል እምነት የለኝም" የሚሉት አቶ ልደቱ፣ ሆኖም ስለጉዳዩ "የተጨበጠ መረጃ" እንደሌላቸው ገልፀዋል።
ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ከአጎራባች አገራት ጋር ካለው ግንኙነት እንዲሁም የውጭ ኃይሎችም ካላቸው ጥቅም እና ፍላጎት አንጻር የውጭ ኃይሎች ትብብሩን ሊረዱ እንደሚችሉ ጥርጥር የላቸውም። ይህን በዋናነት ማስቀረት የሚችለው ግን፣ መንግሥት እንደሆነ ነው የሚያምኑት። መንግሥት በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ችግርን በፖለቲካዊ ውይይት እና በድርድር ለመፍታት ዝግጁ መሆን አለበት ይላሉ።
ትብብሩ በችኮላ እንዲመሠረት የሚያደርጉት ህወሓት እና የኤርትራ መንግሥት ናቸው የሚለውን የጃዋርን ሀሳብ "ሐሰት እና በጣም የተሳሳተ ግምገማ ነው" ይላሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት በህወሓት ላይ "እርምጃ እየወሰደ መሆኑን እንዲሁም በኤርትራ ላይ እየዛተ መሆኑን" ኮንነው፣ በሁለቱ ኃይሎች የሚደረገው ጥረት "ራስን የመከላከል እርምጃ ነው የሚሆነው" ብለዋል።
በቀጣይ ምን ሊፈጠር ይችላል?
ጦርነቱ ተጀምሯል ብለው እንደሚያምኑ የገለፁት አቶ ልደቱ፣ በጥቂት ቀናት ውስጥ "በኢትዮጵያ የተሟላ ጦርነት ሊቀጣጠል ይችላል" ብለው ይጠብቃሉ [ይህንን ከተናገሩ ከአንድ ቀን በኋላ ግጭት ተቀስቅሷል]። በጦርነቱ "ታጣቂዎች እንደሚያሸንፉ ምንም ጥርጥር የለኝም" ሲሉም ተናግረዋል።
አቶ ጃዋር ደግሞ ወደ ተሟላ ጦርነት የመገባቱ ዕድል አነስተኛ ነው ይላሉ። ለዚህም ምክንያታቸው በሁለቱም በኩል ሕዝቡም ጦሩም በውጊያ ተሰላችተዋል የሚል ነው። አሁን ያለው የዓለም አቀፍ አሰላለፍም ሌላ ጦርነትን "የሚፈልግ አይደለም" የብለው ያምናሉ።
በመሆኑም "ይሔንን ትብብር ለጦርነት ሳይሆን ምናልባትም ለድርድር የሚጠቀሙት ነው የሚመስለኝ" ብለዋል።
ወደ ጦርነት የሚገባ ከሆነ ግን "ወይ ዐቢይ እንደዛተው ሁሉንም መደርመስ ይችል ይሆናል። አለበለዚያ እነሱ ተባብረው እኛ ምንላቸውን ትችቶችም ተወጥተው ሥርዓቱን መፈንገል ይችሉ እሆናል። ሦስተኛ ደግሞ የተራዘመ የውጭ ኃይሎችንም ያሳተፈ አገር እና ሕዝብ አውዳሚ ጦርነት ውስጥ ልንገባ የምንችልበት ዕድል አለ" ሲሉ ሦስት የይሆናል ሀሳቦችን አስቀምጠዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለኅልውና (ትብብር ለኅልውና) የተባለው የሰባቱ አማጺያን ጥምረት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን መንግሥት የመጣል እና "በሽግግር ቻርተር የሚመራ አካታች የሽግግር መንግሥት" የመመስረት ዓላማ እንዳለው ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ትብብርሩን በተመለከተ በይፋ ያለው ነገር የለም። መንግሥት ከነዚህ ኃይሎች ጀርባ የውጭ ኃይሎች በተለይም የኤርትራ፣ የግብፅ እና የሱዳን መንግሥታት አሉበት ሲል ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ከሷል።