ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ ከፍተኛ የተባለውን ከ230 ሚሊዮን ዶላር በላይ ክሪፕቶከረንሲ የሰረቀው ሴንጋፖራዊ ወጣት
የሲንጋፖር ዜጋ የሆነ ወጣት በአሜሪካ ካጋጠመ ከፍተኛ ከሆኑት የክሪፕቶከረንሲ ስርቆቶች መካከል አንዱን በመምራት የቀረበበትን ክስ ተቀብሎ ለፍርድ ቤት ጥፋተኛ መሆኑን አመነ።
የ22 ዓመቱ ማሎን ላም ከጓደኞቹ ጋር በመተባበር 245 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ቢትኮይን በመስረቅ እና የተሰረቀውን በሕጋዊ መንገድ እንደተገኘ ለማስመሰል መሞከሩን አምኗል።
የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር እንደገለጸው፣ ላም እና ተባባሪዎቹ የተሰረቀውን ገንዘብ በመጠቀም በአንድ ምሽት እስከ 500 ሺህ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ በምሽት መዝናኛ ክለቦች ወጪ ያደርጉ ነበር። በተጨማሪም ዋጋቸው ከ100 ሺህ እስከ 3.8 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ውድ የቅንጦት መኪኖችንም ገዝተው ነበር።
ላም ጥፋተኝነቱን ማመኑን ተከትሎ እስከ 20 ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ሊፈረድበት ይችላል። ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ ኮሊን ኮላር-ኮቴሊ የቅጣት ውሳኔ ለማሳለፍ ቀን አልቆረጡም።
ላም ማሎን ለአሜሪካ መርማሪዎች በ14 ዓመቱ ሲንጋፖር ውስጥ የነበረውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አቋርጦ በጥቅምት ወር 2023 ወደ አሜሪካ በመጓዝ ከ2024 ጥር ወር ቪዛው ካለቀ በኋላም እዚያው መኖር መቀጠሉን ተናግሯል።
የፍርድ ቤት ሰነዶች እንደሚያሳዩት ይህ የወንጀል ድርጊት ከጥቅምት 2023 በፊት ጀምሮ እስከ ግንቦት 2025 ድረስ ቀጥሏል።
ተባባሪ ተከሳሾቹ ከካሊፎርኒያ፣ ኮኔቲከት፣ ኒውዮርክ፣ ፍሎሪዳ እና ከአሜሪካ ውጭ ከሚገኙ ቦታዎች ተይዘው የመጡ ሲሆን፣ በኢንተርኔት ላይ በሚካሄዱ የጨዋታ መድረኮች ላይ ነው የተዋወቁት።
የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር እንዳለው፣ ላም አን አታዌይ፣ $$ እና ኪንግ ግሬቪ በሚሉ የመለያ ስሞችም ይታወቅ ነበር። እርሱም የሚያጭበረብሯቸው ሰዎችን የሚለይ እና የተለያዩ ተባባሪዎቹን የሚያስተባብር የወንጀሉ ዋና መሪ እንደነበር ተገልጿል።
ተከሳሾቹ ሰዎችን በማታለል ምሥጢራዊ መረጃቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ ያደርጉ እንደነበር እና አንዳንድ ጊዜም ወደ መኖሪያ ቤቶች በመግባት የተጠቂዎቹን የክሪፕቶከረንሲ ዋሌቶች ባዶ ለማድረግ የሚያስችል መረጃ ያገኙ እንደነበርም የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።
የተሰረቀው ክሪፕቶከረንሲ በአስር ሺህ ዶላሮች የሚቆጠር ዋጋ ያላቸውን ቅንጡ ውድ ቦርሳዎች ለመግዛትም ተጠቅመዋል። ቦርሳዎቹንም በምሽት ክለብ ለተሰበሰቡ ሰዎች በመወርወር ይሰጡ ነበር ተብሏል።
በተጨማሪም ከወንጀሉ በተገኘው ገንዘብ እስከ 500 ሺህ ዶላር ዋጋ ያላቸው ውድ ሰዓቶች፣ በአስር ሺህ ዶላሮች የሚቆጠሩ ቅንጡ ልብሶች፣ በሎስ አንጀለስ፣ በሃምፕተንስ እና በማያሚ የሚገኙ የኪራይ ቤቶች፣ ለጉዞ የሚውሉ የግል ጄት አውሮፕላኖች እና የግል ጥበቃ ሠራተኞችን ለመቅጠር ወጥቷል።
ላም በሎስ አንጀለስ እና በማያሚ የምሽት ክለቦች ውስጥ በቅንጡ አኗኗሩ እና ከፍተኛ ወጪ በማውጣት የታወቀ እንደነበር ቀደም ሲል በፍሎሪዳ ፍርድ ቤት ተሰምቷል። ከክሪፕቶከረንሲ ስርቆቱ ያገኘው ትልቅ ሀብትም ትኩረት ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።
የኤፍቢአይ አባላት እርሱን እና አንድ ተባባሪውን በቁጥጥር ስር ካዋሉ በኋላ የላም የወንጀል ቡድን በመስከረም 2024 ፈርሷል።
ላም ያጭበረበረውን በመቶ ሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ በምሽት ክለቦች ውስጥ ከመርጨቱ በተጨማሪ ከ30 በላይ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ቅንጡ መኪኖችን ገዝቷል።
ባለፈው ሚያዝያ ወር፣ ከላም ተባባሪዎች አንዱ የሆነው ኢቫን ታንገማን በወንጀል ያገኘውን ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ የተገኘ እንደሆነ ለማስመሰል በመሞከሩ ከአምስት ዓመት በላይ እስር ተፈርዶበታል።
የፍትህ ሚኒስቴሩ እንዳለው፣ ታንገማን ላም ከታሰረ በኋላ ማስረጃዎችን ለማጥፋት ሞክሮ የነበረ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱም ይህን ተግባር "ድርጊቱ ወንጀል መሆኑን እንደሚያውቅ የሚያሳይ" ምልክት አድርጎ እንደወሰደው ተገልጿል።