በተስፋ ማጣት እና በሞት መሀል፡ የአማራ ክልል ሦስት የጦርነት ዓመታት

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 12 ደቂቃ

አስቴር* ለመጨረሻ ጊዜ ባለቤቷን ያየችው ቅዳሜ ዕለት ለምሳ ቤት ሲመጣ ነው።

ሁሌም እንደሚያደርገው ምሳ በልቶ የሁለት ዓመት ልጁን እና እርሷን ተሰናብቶ ነው የወጣው።

ይቺን ቀን አስቴር መቼም አትረሳትም፤ ተራ ቅዳሜ አይደለችም።

አስቴር ከልጇ ፊት ዞር አለች። ከቤታቸው ግቢ ውስጥ ቁጢጥ ብላ ከሁለት ዓመት በፊት ሕይወቷን ስለቀየረው ክስተት ወደ ኋላ እያብሰለሰለች ነው። አንድ ደቂቃ እንኳ በቅጡ አላወራችም፤ እንባዋ ቀደማት።

ሳግ እየተናነቃት ቀጠለች።

ቅዳሜ ነው፤ ቅዳሜ ከሰዓት። በአካባቢው የተሰማው ዜና የረበሻት አስቴር ባለቤቷ ላይ ደጋግማ ስልክ ትደውላለች። ባለቤቷም "'አታስቢ፤ እኛ ደኅና ነን፤ የሚፈጠረው ስለማይታወቅ ከቤት እንዳትወጪ'" ይላታል።

የአስቴር የጭንቀት ምንጭ በአማራ ክልል ጥቅምት 10/2016 ዓ.ም. ሁለት የመከላከያ ሠራዊት "አዛዦች" መገደላቸው ነው።

አካባቢው ተረብሿል።

ወታደሮቹ የተገደሉት ባለቤቷ ከሚመራው ተቋም ፊት ለፊት ነው። "እናንተ ናችሁ ለፅንፈኛው [ለፋኖ ኃይሎች] ጠቁማችሁ ያስገደላችኋቸው" በሚል የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የ36 ዓመቱን የአስቴርን ባለቤት ጨምሮ የሕንፃውን ባለንብረት እና የተቋሙን የጥበቃ ሠራተኛ ካምፕ ወዳደረጉት የግብርና ምርምር ተቋም እንደወሰዷቸው እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሕይወት የተመለሰው ግን አንድ ሰው ብቻ ነው።

"ከዚህ በኋላ የሆነውን አላውቅም" ትላለች አስቴር፤ በደመ ነፍስ ሆና አስከሬን መቀበሏን ስታስረዳ።

"እስከ 12 ሰዓት ድረስ ጠበቅኩ። ከዚያ የጥይት ድምፅ ሰማሁ። ደነገጥኩ። ይገድሉታል ብዬ አልጠበኩም። ከሠው የሚደርስ አይደለም። ባሌ ስለሆነ ብቻ አይደለም። እርሱ ለባዳም ለዘመድም ሩህ ሩህ ነው። ከራሱ በላይ ሠውን ያስቀድማል" ትላለች አስቴር ድምጿ በሐዘን እየተቆራረጠ።

ከተወሰደ ከሰዓታት በኋላ የአስቴር ባለቤት በጥይት ተመትቶ አስከሬኑ መንገድ ላይ ወድቆ ተገኝቷል።

ልጃቸው ገና ሁለት ዓመቷ ነበር።

ከአስቴር ባለቤት ጋር ተወስደው ከተገደሉት እና አስከሬናቸው ከከተማ ውጭ (ከካምፑ አቅራቢያ) የተገኙት የጥበቃ ሠራተኛው አቶ አበበ* የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባል እና የሦስት ልጆች አባት ነበሩ።

አንደኛውን ልጃቸውን ግን ለመሳም አልበቁም። እርሳቸው ሲገደሉ ባለቤታቸው የስምንት ወር ነፍሰ ጡር ነበሩ።

ሦስት ዓመታትን ደፍኖ አራተኛ ዓመቱን አንድ ብሎ መቁጠር በጀመረው የአማራ ክልል ጦርነት እንደ አስቴር ባለቤት እና አቶ አበበ ከፍርድ ውጭ ግድያዎችን ጨምሮ ንፁሃን ገፈቱን እየቀመሱ ነው።

ከወራት አለመረጋጋት በኋላ ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. በፋኖ ኃይሎች እና በመንግሥት መካከል ዳግም የፈነዳው የትጥቅ ግጭት ሚሊዮኖች ላይ ዳፋውን ማሳረፉን የትጥቅ ግጭቶችን የሚመዘግበው የአክሌድ መረጃ ይጠቁማል።

በአክሌድ ትንተና መሠረት ከጥር እስከ ሐምሌ 2018 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሰዎች 'ለግጭት' ተጋልጠዋል።

ግጭቱ ሁሉንም የክልሉን አካባቢዎች ቢያዳርስም ምዕራብ ጎጃም፣ ሰሜን ወሎ እና ሰሜን ሸዋ በስፋት የተሰራጨባቸው አካባቢዎች ናቸው፤ እንደ አክሌድ መረጃ።

ስሜ አይጠቀስ ያሉ የሕግ እና ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ የአማራ ክልልን የሦስት ዓመት የጦርነት ዓውድ ሁሉንም ወገኖች እያወደመ ያለ ጦርነት ሲሉ አስከፊነቱን ይገልፁታል።

ሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመፈፀም ቢከሰሱም የመንግሥት ኃይሎች በአማራ ክልል ውስጥ ለሚፈፀሙ አብዛኛዎቹ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ ናቸው።

ባለሙያዎች መንግሥት የዜጎችን መብት የመጠበቅ እና ማስጠበቅ የሕግ እና የሞራል ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ብቻ ሳይሆን ራሱ አጥቂ ሆኖ በመቅረቡ ከባድ ክስ ያቀርባሉ።

ክልሉ ከሦስት ዓመታት በላይ ሕጋዊ ባልሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር የሚገኝ ሲሆን፤ የመብት ገደቦች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው።

ቢቢሲ ከክልሉ መንግሥት ምላሽ ለማግኘት ለሳምንታት ቢጠብቅም መልስ አላገኘም።

አብዛኞቹ ንፁኅንን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል ውጊያ ከተደረገ በኋላ የሚፈፀሙ ሲሆኑ፤ ዒላማቸውን በሳቱ የከባድ መሣሪያ ጥቃቶች የተገደሉ ነዋሪዎችም አያሌ ስለመሆናቸው ሪፖርቶች ያመላክታሉ።

ከውጊያ ግንባር ውጭ በተለይም በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ የሚፈፀሙ የዒላማ ግድያዎችም የክልሉ የጦርነት ዓውድ ሌላኛው መገለጫ ነው።

የመንግሥት ኃይሎች ደግሞ የፋኖ ቤተሰቦች ላይ ሲያነጣጥሩ፤ "ፋኖን ይደግፋሉ" ያሏቸውን ንጹኅን ጨምሮ እስራት፣ ግድያ እና ሌሎች ጥቃቶችን በስፋት እንደሚፈፀሙ ምርመራዎች ያሳያሉ።

የግፍ ነፍሶች

ግንቦት 29/2016 ዓ.ም. የሰሜን ሸዋ ዞን የቀወት ወረዳ የአስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ሚሊሹ በቀለ መንገድ ላይ ተገድለዋል።

የስድስት ወር ነፍሰ ጡር ነበሩ።

ወ/ሮ ሚሊሹ በአማራ ክልል ጦርነት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ በሚያነጣጥሩ ጥቃቶች ከተገደሉ በርካታ ሰዎች መካከል አንዷ ናቸው።

ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ወ/ሮ ሚሊሹን ጨምሮ የአካባቢው አመራሮች በታጣቂዎች የሚደርስ ጥቃትን ሽሽት ቤታቸውን ጥለው ጥብቅ ጥበቃ በሚደረግበት የአስተዳደር ቢሮ እንደሚያድሩ ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለ15 ዓመታት ያህል በጤና ባለሙያነት ያገለገሉት ወ/ሮ ሚሉሹ ለአዳር ወደ አስተዳደር ቢሮ እየተጓዙ እያለ ሰርገው በገቡ እና "ፋኖ ናቸው" በተባሉ ሁለት ታጣቂዎች መንገድ ላይ እንደተገደሉ ባለቤታቸው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

"ሲነግሩኝ በቁሜ ወደቅኩ። ሰዎች ደገፉኝ፤ ስረጋጋ ሮጬ ሄጄ አስከሬኗ ላይ ወደቅኩ። ከወደቀችበት አንስተው ነጠላ አልብሰው አስተኝተዋታል። ማየት አለብኝ አልኳቸው፤ 'ምኑን ታያታለህ?' አሉኝ። ዓይኗ ስር ነው የተመታችው።"

"በግፍ ነው የገደሏት፤ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ" ይላሉ።

በኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከገዢው ብልፅግና ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያላቸው የአካባቢ አስተዳዳሪዎች የጥቃት ዒላማ እንደሚሆኑ አክሌድ በሪፖርቱ ይገልፃል።

ይህ የስጋት አዝማሚያ ከ2015 ዓ.ም. አጋማሽ ወዲህ በአማራ ክልል መስፋፋቱን የሚጠቁመው ድርጅቱ የአካባቢ አስተዳዳሪዎች ጥቃት የፖለቲካ ግብን ለማሳካት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ብሏል።

". . .የአካባቢ ባለሥልጣናት ለታጣቂ ቡድኖች ተቃራኒ ፍላጎቶችን ይወክላሉ። ስለዚህም የዓመፁን ከፍተኛ ዳፋ ተሸክመዋል።"

የፋኖ ኃይሎች የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የካቢኔ አባላት እና የብልፅግና ፅ/ቤት እንዲሁም የፀጥታ ኃላፊዎች ላይ እንደሚያነጣጥሩ ይታመናል።

ደቡብ ጎንደር ዞን ከሌሎቹ የክልሉ አካባቢዎች የባሰ በሚመስል ሁኔታ በርካታ የወረዳ አስተዳዳሪዎች እና የሥራ ኃላፊዎች ተገድለዋል።

አንድ የአካባቢው የመንግሥት ምንጭ በስብሰባዎች ላይ ፋኖን የሚያንቋሽሽ አስተያየት የሚሰጡ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ዒላማ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

". . . መረጃ አላቸው። ሠዎችን ይመርጡና 'እናንተን አንለቃችሁም። እንዲህ እናደርጋለን' ብለው ዛቻ ይልኩባቸዋል። ምቹ ሁኔታ ካገኙ አይምሯቸውም" ሲሉ ኃላፊዎች እንዴት ዒላማ እንደሚደረጉ ገልፀዋል።

በዞኑ እርሳቸው የሚያውቋቸው ከ10 በላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንደተገደሉ ጠቁመዋል።

"የብዙዎቹ አመራር ልጆች ወላጅ አልባ እየሆኑ ነው። ያለው አደጋ ከባድ ነው" ይላሉ።

የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ያለው ስጋት ሥራቸውን በርቀት እና ደኅንነት ባለባቸው አካባቢዎች ሆነው እንዲሠሩ አስገድዷቸዋል።

ስጋቱ ኃላፊዎቹ ያለ እጀባ እንዳይንቀሳቀሱ ከማድረጉ ባሻገር በተለይም የወረዳ ኃላፊዎቹ ኑሯቸውን የጦር ካምፕ ውስጥ እንዲያደርጉ ማስገደዱን አመልክተዋል።

"ማንኛውም አመራር ያለ እጀባ ከእያንዳንዱ ከተማ አስተዳደር እና ወረዳ ወጥቶ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ አይችልም"።

የደቡብ ጎንደር ዞን ፖሊስ ዋና አዛዥ ኮማንደር ንጉስ ታመነ የአመራሮች ግድያ "በተለይ 2016 እና 2017 የከፋ ነበር" ብለዋል።

ይሁን እንጂ ኮማንደሩ በዞኑ "አብዛኞቹ" የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች "በውጊያ" እንደተገደሉ ገልፀዋል።

የሲቪል መሪዎች "በውጊያዎች በቀጥታ" እንደሚሳተፉ የፖሊስ አዛዡ ተናግረዋል። "ራሳቸውን ለመከላከል መሣሪያ ታጥቀው ነው የሚንቀሳቀሱት" ሲሉ ያበራራሉ።

"ከተማረኩ በኋላ የሚገደለው ግን ብዙ ነው" ሲሉም የአካባቢያቸውን ነባራዊ ሁኔታ ገልፀው፤ የአመራር ቤተሰቦችም የጦስ ዶሮ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

የፋኖ ኃይሎች ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን "መሣሪያ ከያዘው ወታደር ለይተን አናየቸውም" በማለት የውጊያው አካል እንደሆኑ ተናግረዋል።

የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ደግሞ የፋኖ አባላት ቤተሰቦች እና "ፋኖን ይደግፋሉ" የሚሏቸው ንፁሃን ላይ ወከባ፣ ዛቻ፣ እስር፣ ንብረት ማገድ፣ ግድያ እንዲሁም ሌሎች ጥቃቶችን እንደሚፈፅሙ የሰብዓዊ መብት ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

በ2016 ዓ.ም. መጨረሻ በደጀን ወረዳ ባለቤቷ የፋኖ አባል በመሆኑ ለወራት ታስራ የቆየችው የስድስት ወር ነፍሰ ጡሯ ንፁህ መኮንን እና የ44 ዓመት አማቷ (የፋኖ አባሉ እናት) ከታሰሩበት ፖሊስ ጣቢያ እንዲወጡ ተደርገው በግፍ መገደላቸውን ቤተሰቦች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሕፃናትን ጨምሮ ስድስት የአንድ ቤተሰብ አባላት የፋኖ አባል የሆነው የንፁህ ባለቤት "እንዲመለስ" ለማስገደድ ለወራት መታሰራቸውን ገልፀዋል።

"ከእስር እና ድብደባ አልፈው ጭራሽ በመንግሥት ደረጃ ተይዘው ይገደላሉ የሚል ጥርጣሬ አልነበረንም" ብለዋል የቤተሰብ አባሉ።

የዓይን እማኞች ንፁህ እና አማቷን ጨምሮ ሌሎች ታስረው የነበሩ ሰዎችን ግድያ "የበቀል" ብለው መግለፃቸውን አንድ የሰብዓዊ መብት መርማሪ ለቢቢሲ ጠቁመዋል።

ግድያው የተፈፀመው በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ላይ የፋኖ ኃይሎች ጥቃት ከፈፀሙ በኋላ ነው።

የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ንፁኃን በግጭቱ ምንም ተሳትፎ ሳይኖራቸው በቤተሰቦቻቸው እንቅስቃሴ ምክንያት ብቻ የበቀል ጥቃት ዒላማ እንደሚሆኑ ይገልፃል።

እንደዚህ ዓይነት የንፁኃን ጥቃቶች ተነጥለው የሚታዩ ሳይሆኑ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ የሚያንፀባርቅ ሰፊ የጥቃት አዝማሚያ አካል መሆናቸውን ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

ይህም በውጊያ ወቅት ከሚገደሉት ሰላማዊ ሰዎች በዘለለ ንፁሃን ላይ ሆን ተብሎ የሚፈፀም ጥቃት ነው።

ሞት፣ ግድያ፣ የእንቅስቃሴ እቀባ እና ገደቦች፣ እንደ እገታ ያሉ ጦርነቱ የወለዳቸው ወንጀሎች፣ ስደት፣ ተስፋ ማጣት፣ የኑሮ ጫና የክልሉ መደበኛ ሕይወት ከሆኑ ዓመታት አልፈዋል።

"ገሃነም ነው"

የትጥቅ ግጭት ሁነቶችን የሚሰንደው አክሌድ በመዘገበው የአማራ ክልል የሦስት ዓመታት ክስተት ዝርዝር ውስጥ በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል የሚደረግ ውጊያ 80 በመቶውን የክልሉን የጦርነት ዓውድ ይሸፍናል።

በክልሉ ግጭቶች ያዝ ለቀቅ የሚል ባህሪ አላቸው።

የአክሌድ የምሥራቅ አፍሪካ ክፍተኛ ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር ጃለሌ ጌታቸው "ኦፕሬሽን [ዘመቻ] በተጀመረ ጊዜ በጣም ከፍ ይላል። ኦፕሬሽን ለሁለት ሣምንት ወይም ለአንድ ወር [ገደማ] ይቆያል። ከዛ በኋላ ግጭቶቹ ይቀንሳሉ"።

"ሜዳ ላይ አይደለም ውጊያው የሚደረገው። ሠው የሚኖርበት አካባቢ ስለሆነ [ንፁኃን] ይጎዳሉ። መረጃዎቻችን ይህን ያሳያሉ" ብለዋል።

13 በመቶ የክልሉ የጦርነት ዓውድ በንፁሃን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ናቸው።

ጥር 2016 ዓ.ም. በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የጅምላ ግድያ የተፈፀመባት መርዓዊ ከተማ ከክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር በ35 ኪሎ ሜትር ገደማ ትገኛለች።

ከተማዋ እና አካባቢው የጦርነቱ ትኩሳት በቀዳሚነት ከሚደርስባቸው ስፍራዎች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው።

ሕይወት በመርዓዊም ሆነ በሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎች ጨለማ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ፍርሃት፣ ስጋት፣ ተስፋ ማጣት፣ ስደት፣ ግፍ፣ ሞት . . . ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ደጋግመው የሚገልጿቸው ቃላት ናቸው።

በቤተሰባቸው ወይም በሚያውቋቸው ሰዎች ላይ የደረሱ አሳዛኝ የግፍ ታሪኮችን ያጋራሉ።

"ለመሸከም እንኳ የሚከብዱ" ሲሉም እነዚህን ግፎች ይገልጿቸዋል።

የአራት ልጆች አባት የሆኑት ቄስ ስመኘው* "ሞትም መፈናቀልም ተለምዷል" ሲሉ የጦርነቱን አስከፊ ሁኔታ በመግለፅ መደበኛ ሕይወታቸው ከሆነ ውሎ ማደሩን ይናገራሉ።

"ሕፃናት እንደ ልብ ወጥተው ካልተማሩ፣ እናቶች አባቶች መንቀሳቀስ ካልቻሉ፣ሠራተኞች [ሥራ] ካልሰሩ፣ ሠው ቤተ ክርስቲያን በነፃነት ደርሶ ካልተመለሰ?" በማለት "አሰቃቂ" ያሉትን ሕይወት በጦርነት ይገልፃሉ።

በአማራ ክልል በሁሉም አካባቢዎች ግጭቶች ቢኖሩም በአብዛኛው የተፋላሚ ወገኖች ዋነኛ የጦር ሜዳ ግን ምዕራብ ጎጃም ነው።

"አብዛኛው ከፍተኛ የሟቾች ቁጥርም የተመዘገበው በምዕራብ ጎጃም ነው" ይላሉ የአክሌድ ከፍተኛ ተንታኝ።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ሰሜን ወሎ ዞን ከምዕራብ ጎጃም ቀጥሎ ከፍተኛ ውጊያ የሚደረግበት አካባቢ እንደሆነ የአክሌድ መረጃ ያሳያል።

በሰሜን ወሎ የምትገኘው ታሪካዊቷ ላሊበላ ጎብኝዎች ርቀዋት የቀድሞ መልኳን ማጣቷን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት የ60 ዓመቱ የቀድሞ መምህር አቶ ገዛኸኝ* ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት የነበራቸው ሕይወት እንዳይመለስ ሆኖ መቀበሩን ያስረዳሉ።

ማኅበረሰቡ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ "ገሀነም ነው" ይላሉ።

"ኑሮ አይደለም፤ ስቃይ ነው። በምን ቋንቋ እገልፀዋለሁ። ገበያ ውድ ነው። ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ስጋት ነው። ሲፈልግ ይገድላል፣ ይደበድባል፣ ያስራል. . .ከባድ ነው። ጭልም ያለ ነው።"

"በአገራችን ላይ ስደተኞች ነን። በግዞት ውስጥ ያለን ሰዎች ነን" ይላሉ፤ የተሻለ የገንዘብ አቅም ያላቸው ነዋሪዎች ክልሉን ጥለው መውጣታቸውን በመጠቆም።

የፋኖ ኃይሎች ጠንካራ ይዞታ የመሠረቱበት አካባቢ እንደሆነ የሚታመነው ምዕራብ ጎጃም ደጋ ዳሞት ወረዳ፤ አካባቢውን ለመቆጣጠር ከባድ ፍልሚያዎች የሚደረግበት አካባቢ ነው።

በወረዳው አርሶ አደር የሆኑት የሁለት ልጆች አባት አቶ ሲሳይ* "ግጭት የሚርቀው አካባቢ አይደለም" በማለት "ሁሌም መሳቀቅ ነው" ይላሉ።

ወረዳውን ከሦስት ወራት በፊት የፋኖ ኃይሎች ዳግም ከተቆጣጠሩት በኋላ ከሐምሌ መጀመሪያ አንስቶ "ከባድ ውጊያ" እየተደረገበት ነው።

አቶ ሲሳይ ግጭት ሲቀሰቀስ "ከብት አስገብተን ነው የምንጠፋው" ይላሉ። ስጋታቸውን ሲያስረዱም "ዛሬን አለፍኩ፤ ነገን አለፍኩ ነው" ይላሉ።

ከጦርነቱ በፊት ጭንቀታቸው "ዝናብ ዘነበ፤ አልዘነበም ነው። አንድ በሬዬን ነገ ሁለት አደርገዋለሁ ነው። ስለ ሰርቶ ማደር እንጂ ስለ ሌላ አስቤ አላውቅም" ይላሉ የዛሬ ጭንቀታቸው ቤተሰባቸውን የጥይት እራት ከመሆን መጠበቅ እንደሆነ በመጠቆም።

የክልሉ ነዋሪዎች እንቅስቃሴ የቅንጦት ያህል እንደሆነም ይናገራሉ። በመንገዶች መዘጋት እና በእንቅስቃሴዎች ላይ በሚጣሉ ገደቦች ምክንያት ወጥቶ መግባት እና ማኅበራዊ መስተጋብሮችን መከወን በእጅጉ እንደተገደበ ይናገራሉ።

ገበያዎች የፀጥታ ሁኔታው ነፀብራቅ ከሆኑ ውለው አድረዋል።

ማክሰኞ እና ቅዳሜ ገበያ በሚውልበት ፈረስ ቤት ደጋ ዳሞት ገበያው ጭር ካለ ከረምረም ማለቱን ነጋዴዎች ይናገራሉ።

ከግጭት በኋላ ለሳምንታት የሚበተነው የወረዳው ገበያ አርሶ አደሮች አነስተኛ ገበያዎችን በገጠር እንዲፈጥሩ አስገድዷል። ሆኖም እነዚህ አዲስ ገበያዎች አርሶ አደሮች ምርቶቻቸውን በአነስተኛ ዋጋ እንዲለዋወጡ ከማድረግ ባለፈ ወደ ከተማ የሚገቡ በተለይም የእህል ምርቶች መጠን እንዲቀንስ ማድረጉንም ነዋሪዎች ጠቁመዋል።

በፈረስ ቤት ከተማ የሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴ የሆኑት አቶ በላይ* አጠቃላይ ሁኔታውን "አስከፊ" ሲሉ ገልፀው፤ ወረታቸው እያሽቆለቆለ እንደሆነ፣ እቁብ መጣል እንዳቆሙ እና ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር እርዳታ መጠየቅ ግድ እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጦርነቱ ባሳረፈው ዳፋ በተለይም በእንቅስቃሴ ገደቦች ምክንያት የኑሮ ውድነት መከሰቱን የሚያነሱት ነዋሪዎች "በልቶ ለማደር ችግር ሆኗል" ይላሉ።

አቶ ገዛኸኝ የመሠረታዊ ሸቀጦች ከጦርነቱ በፊት እና በኋላ ያላቸውን ዋጋ በሰጡን ዝርዝር እስከ አራት እጥፍ ዋጋ መጨመሩን ቢቢሲ ተረድቷል። የክልሉ የኑሮ ሁኔታ አጠቃላይ በአገሪቱ ከተከሰተው የኑሮ ውድነት ተፅዕኖ ባሻገር ነው።

"ዋጋው የሚቀመስ አይደለም" ሲሉ ጦርነቱ ከሳረፈው ሰብዓዊ ቀውስ ባሻገር የማኅበረሰቡ ኑሮ ላይ ያሳደውን ተፅዕኖ ይገልፃሉ።

"በየጊዜው የዋጋ ጭማሪ አለ" ሲሉ አንድ ነጋዴ ሁኔታው ከእጃቸው ያለፈ እንደሆነ አመልክተዋል።

የላሊበላ ነዋሪው አቶ ገዛኸኝ ቀውሱ ስር የሰደደ መሆኑንም የበለጠ ሲገልፁ፤ እርሳቸው በሚኖሩበት ከተማ ልመና ከወትሮው በተለየ መልኩ ስለመስፋፋቱ አንስተዋል።

በአማራ ክልል ግጭቱ ወልዶታል ተብሎ በሚታመነው እገታ ብዙዎች አካባቢያቸውን ለቅቀው እንዲወጡም ገፊ ሆኗል።

ለአንድ ሠው የእገታ ማስለቀቂያ እስከ አስር ሚሊዮን ብር ድረስ እንደሚጠየቅ የሚናገሩት የፖሊስ አዛዡ ኮማንደር ንጉስ፤ አጋቾች ዒላማቸውን አጥንተው እንደሚመጡ እና የተቀናጀ ጥቃት እንደሚፈፀም ተናግረዋል።

ይህም በተለይም ባለሀብቶች ክልሉን ለቅቀው እንዲሰደዱ እንዳደረገ ገልፀዋል።

የአባት እና ልጅ ጦርነት

ሰሎሞን [ትክክለኛ ስሙ አይደለም] ገና የ18 ዓመት ተማሪ እያለ ነበር የትጥቅ ትግል እያደረጉ ያሉ ኃይሎችን የተቀላቀለው።

እስክርቢቶውን ጥሎ ብረት እንዲያነሳ ያደረገው "የአማራ ሕዝብ በደል እየደረሰበት ነው" የሚል ቁጭት ስላደረበት እንደሆነ ይናገራል።

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ማንነትን መሠረት አድርገው በአማራ ተወላጆች ላይ የደረሱ ጥቃቶችን በማንሳት "በልጅነት አዕምሮዬ ትልቅ ጫና ፈጥሮብኛል። አመፀኛ እንድሆን አድርጎኛል" ይላል።

የሰሎሞን አባት ደግሞ 'ሚሊሻ' ናቸው።

የአማራ ክልል መንግሥት የግል የጦር መሣሪያ ባለቤቶችን እና በተለምዶ ሚሊሻ ተብለው የሚጠሩ ታጣቂዎችን እንደ አዲስ በማደራጀት እና በማሰልጠን በክልሉ ጦርነት "ጥምር ጦር" ለሚባለው እና የተለያዩ የፀጥታ አካላትን ላቀፈው ኃይል አሰልፏል።

የሰሎሞን አባት አቶ አባተ* የዚህ ጦር አባል ናቸው። የበኩር ልጃቸው ነፍጥ ያነሳበት ዓላማ ላይ እምነት ስለሌላቸው በተቃራኒ ወገን መቆማቸውን ይናገራሉ።

ሰሎሞን እና አባቱ በአንድ ቀጣና በተቃራኒ ወገን ሆነው ይፋለማሉ፤ እስካሁን ድረስ አባት እና ልጅ ፊት ለፊት በጦር ግንባር ባይገናኙም።

በክልሉ ጦርነት እንደ ሰሎሞን እና አቶ አባተ ያሉ በርካታ የአንድ ቤተሰብ አባላት በተቃራኒ ወገን ሆነው እየተፋለሙ ነው።

ቢቢሲ ይህን የሚያጠናክሩ መረጃዎችን ከነዋሪዎች ያገኘ ሲሆን፤ ሰሎሞንም "ከእኛ ሻለቃ ብቻ ከሦስት እስከ አራት አሉ" በማለት የአንድ ቤተሰብ አባላት በተቃራኒ ጎራ ተፋላሚ ሆነው መሰለፋቸው ሰፋ ያለ መልክ እንዳለው ይናገራል።

"ማንኛውም ሠው ከወንድሙ፣ ከአባቱ፣ ከአጎቱ ጋር ነው ገጥሞ እየተገዳደለ ያለው" ይላሉ አቶ አባተ መሬት ላይ ያለውን ገሀድ ሲገልፁ።

ሰሎሞን እና አቶ አባተ በአንድ ወረዳ ነው የሚንቀሳቀሱት።

አንዱ ሌላኛውን ከተሰለፉበት ተፋላሚ ወገን እንዲወጡ ለማድረግ በተደጋጋሚ በቤተሰብ "ማስመከራቸውን" ይገልፃሉ። ጥረታቸው ግን ባለመስመሩ ለዓመታት ጎራቸውን ይዘው በተቃርኖ አባት እና ልጅ እየተፋለሙ ነው።

በጦርነት ግንባር ፊት ለፊት እንገናኛለን የሚል ስጋት እንደሌለባቸው እና ቢገናኙም ከሌሎች ተፋላሚዎች ተለያይተው እንደማይተያዩ አመልክተዋል።

"አፈሙዝ ተዘርግቶ፣ የእገሌ ልጅ የእገሌ አባት አይባልም። ጦርነት አስከፊ ነው" ይላሉ አቶ አባተ።

"አባት ነው፤ ዝምድና አይሻርም። ግን ደግሞ ለእርሱ ያለኝ ስሜት አሁን ዜሮ ነው" ይላል ሰሎሞን ከወጣበት ዓለማ ንቅንቅ እንደማይል እየገለፀ።

ሰባት ወንድሞች እና እህቶች እንዳሉት የሚናገረው ሰሎሞን፤ የአባት እና ልጅ በተቃራኒ ወገን መቆም ተፅዕኖ እንዳሳደረባቸው ይናገራል።

"በሕፃን ልቦናቸው ፀብን ያውቁታል። ሕፃን ቢሆኑም ያውቁታል። . . . ያለቅሳሉ፤ በጣም ይሰማቸዋል። ማልቀስ ብቻ ነው" ይላል።

የተዘጉ የሚመስሉ የሰላም በሮች

ሚሊዮኖችን ለጥቃት ያጋለጠው የአማራ ክልል ጦርነት የድሮን እና የከባድ መሣሪያ ድብደባዎችን ጨምሮ ሰፊ ውጊያዎች በየቦታው እንደሚደረጉ መረጃዎች ያሳያሉ።

በአማራ ክልል ግጭት ከንፁኃን ጥቃቶች ባሻገር የእምነት ተቋማትን ጨምሮ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እና የሲቪል መገልገያዎች የጥቃት ዒላማ ከመሆን አልዳኑም።

መንግሥት የተመጣጣኝነትን መርኅ ባለማክበር በተለይም በከባድ መሣሪያ ጥቃቶች የጤና ተቋማት፣ አብያተ ቤተ ክርሲያናት እና የመኖሪያ መንደሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቋል።

ከዚህ ባሻገርም ኮሌጆችን ጨምሮ ትምህርት ቤቶች፣ የመንግሥት ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶች እና የግለሰብ ንብረቶች በተፋላሚ ኃይሎች ካምፕ እንደተደረጉ ቢቢሲ ያሰባሰባቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በክልሉ በተለይ ንፁኃን ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች በሚገባ ተሰንደዋል ተብሎ ባይታመንም የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በሰብዓዊነት ላይ የተቃጣ እና እንደ ጦር ወንጀል የሚታዩ ጥቃቶች መፈፀማቸውን ይገልፃሉ።

መቀመጫቸውን በአውስትራሊያ ያደረጉት የሰብዓዊ መብት ባለሙያ ዶ/ር ይርጋ ገላው ግን በክልሉ በንፁሃን ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ከእነዚህ ወንጀሎችም ከፍ ያሉ ናቸው የሚል እምነት አላቸው።

"ሕዝቡ ለከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ተዳርጓል። ከዚህም አልፎ ሕይወቱን ወደ ፊት ለማስቀጠል የሚያስችለው ሠርቶ፣ ዘርቶ፣ ነግዶ ወዘተ ለመኖር እንዳይችል የሚያደርግ ሁኔታ [ተፈጥሯል]፤ በሰላም እና በሕግ የመኖር እድሉን አጥቷል" ሲሉ በአጠቃላይ በሕዝቡ የሚፀሙ በደሎች "የተቀናጁ እና ስልታዊ" ናቸው ይላሉ።

"ከዘር ተኮር ጥቃት ተለይቶ የሚታይ አይደለም" ይላሉ።

ላምኪን ኢንስቲትዩት ባለፈው መጋቢት ወር ለአማራ ክልል ሁለተኛውን "የዘር ፍጅት ማስጠንቀቂያ" አውጥቷል።

በአማራ ክልል ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች የትኞቹን አካባቢዎች እንደሚቆጣጠሩ በግልፅ ለማሳየት ከባድ ነው።

ይሁን እንጂ ከነዋሪዎች ምስክርነት እና ከተፋላሚ ኃይሎቹ እንቅስቃሴ በመነሳት በአመዛኙ የዞን እና ወረዳ ከተሞች በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ሲሆኑ፤ የገጠር ቀበሌዎች ደግሞ በፋኖ ኃይሎች ስር ይገኛሉ።

የፋኖ ኃይሎች ሙሉ ለሙሉ የሚቆጣጠሯቸው "የተወሰኑ" ወረዳዎች እንዳሉ ቢቢሲ ማወቅ ችሏል። በሚቆጣጠሯቸው አካባቢውም "አስተዳደር" ይመሰርታሉ። ምንም እንኳ መንግሥት ከቁጥጥሩ ውጭ የሆኑ አካባቢዎች እምብዛም የሉም ቢልም።

በዚህ መሀል ያለፉት ሦስት ዓመታት የክልሉ የጦርነት ዓውድ ገፈቱ ለንፁሃኑ ማኅበረሰብ መትረፉ በሰፊው ይታመናል።

ቢቢሲ ካናገራቸው በሁሉም የክልሉ ጥግ ያሉ ነዋሪዎች የጦርነቱ መቋጨት ላይ ተስፋ እንደሌላቸው ተረድቷል።

"በሠው የሚፈታ አልመሰለንም። መድኃኒዓለም ፊቱን አዙሮልን በቃችሁ ባለን" ሲሉ የላሊበላ ነዋሪው አቶ ገዛኸኝ ይማፀናሉ።

"ከዚህ ሁሉ ጉድ አውጣን እያልን ነው" ሲሉ ሌላ ነዋሪ ተማፅኗቸው ለፈጣሪ እንደሆነ ተናግረዋል።

የጦርነቱ ተፋላሚ ኃይሎች በየፊናቸው አሸናፊዎች እንደሆኑ መናገራቸውን ቀጥለዋል።

በጦርነቱ ሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች አሸናፊ ሆነው መውጣት እንዳልቻሉ የሚናገሩት የሕግና ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ የፌደራል መንግሥቱን እርምጃዎች እና አያያዝ ተንተርሰው የጦርነቱን መቀጠል መንግሥት ይፈልገዋል ሲሉ ይከስሳሉ።

ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ ለማስቆም እውነተኛ ጥረቶች እንዳሉ አይታመንም። ይልቁንም የድርድር እንቅስቃሴዎች በመንግሥት በኩል "የይስሙላ" ሆነው የሚታዩ ሲሆን፤ የፋኖ ኃይሎች ደግሞ ለድርድር በራቸውን የዘጉ ይመስላሉ።

ባለፈው ኅዳር መጨረሻ "ለሕዝብ እፎይታ" የሚሰጥ ነው የተባለ "የሰላም ስምምነት" ከፋኖ ተነጥሎ በወጣ ቡድን እና በአማራ ክልል መንግሥት መካከል ተፈርሟል።

ይሁን እንጂ ስምምነቱ ጦርነቱን ያስቆመ አይደለም።

በሥራቸው ምክንያት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ተንታኙ ይህን ስምምነት "እርባና የሌለው" የሚሉት ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ተሞክሮ የከሸፈ ስልት ነው ይላሉ።

"ዘላቂ ሰላምን የሚያሳካ እውነተኛ ድርድር ከማድረግ ይልቅ መንግሥት አሁንም እንቅስቃሴውን በመከፋፈል፣ ተነጥለው የወጡ ቡድኖችን በማስገባት እና ከእነርሱ ጋር ብቻ በመደራደር ፋኖን እንደሚያዳክም ያምናል" ሲሉ መሬት ላይ የመጣ ለውጥ እንደሌለ በመጥቀስ ከአጭር ጊዜ የፖለቲካ ትርፍ ውጭ ጠብ ያለ ነገር የለም ይላሉ።

ቢቢሲ የፋኖን ክንፍ ወክለው ስምምነቱን የፈረሙት አቶ ማስረሻ ሰጤን ስለ ስምምነቱ ይዘት እና ገቢራዊነት ለማነጋገር ጥያቄ ቢያቀርብም መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።

ስምምነቱን "አደራደሩ" የተባሉት አፍሪካ ኅብረት እና ኢጋድ ሚናቸውን በተመለከተ ቢቢሲ አስተያየት እንዲሰጡ ጠይቆ መልስ አላገኘም።

ቢቢሲ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ለተገኙት የአፍሪካ ኅብረት ምክትል ኮሚሽነር ሰልማ ማሊካ ሃዳዲ እና ለኢጋድ ምክትል ዋና ፀሐፊ ሞሐመድ አብዲ ዋሬ ጥያቄ አቅርቧል።

የሕግ እና ፖለቲካ ተንታኙ በአማራ ክልል ከሦስት ዓመታት በፊት ለፈነዳው ግጭት ስረ መሠረት የሆኑ ጉዳዮች "ታማኝ እና አካታች" በሆነ ድርድር የማይፈቱ ከሆነ ጦርነቱ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በአክሌድ የቢሆን እይታ የአማራ ክልል ጦርነት በመጪዎቹ ጥቂት ወራት (ከሦስት እስከ ስድስት ወር) ከዚህ በበለጠ የተባባሰ፣ የተወሳሰበ እና የሰፋ ሊሆን የሚችልበት እድል ከፍተኛ ነው።

ለዚህ ደግሞ ስጋት ያሳደረው የትግራይ ክልል ውጥረት ትልቅ ሚና የሚኖረው ሲሆን፤ ሁለቱ ክልሎች የባለቤትነት ውዝግብ የሚያነሱባቸው አካባቢዎች የጦርነት ሜዳ እንደሚሆኑ የሚገምተው አክሌድ፤ የፋኖ ኃይሎች ደግሞ ተስበው ከመገባት ባለፈ በአቋም ልዩነት ሊከፋፈሉ እንደሚችሉ ጠቁሟል።

የአማራ ክልል ጦርነት ትኩረት ተነፍጎት ዓመታትን እየቆጠረ ባለበት ጊዜ እንደ አስቴር ያሉ ቤተሰባቸውን በግፍ የተነጠቁ ሰዎች ዳፋውን መቋቋም እንዳልቻሉ ይናገራሉ።

የአስቴር ባለቤት የቤተሰቡ አስተዳዳሪ የነበረ ሲሆን፤ የልጃቸውን እና የቤተሰባቸውን ሕይወት የማሻሻል ህልም ነበረው።

አስቴር የባለቤቷን አስከሬን ለመቅበር አካባቢውን ለቅቃ ከወጣች በኋላ ትዳር መስርታ ወደ ነበረችበት ቤቷ ዳግም አልተመለሰችም።

ከግድያው በኋላ ባሉት ዓመታት አሁን አራት ዓመት የሆናትን ልጃቸውን ለማሳደግ የቤተሰቦቿን እጅ ማየት ብቸኛ አማራጯ ሆኗል።

"ቤት ሲፈርስ ብዙ ነገር ይጎድላል። በዓል ሲመጣ ትከፊያለሽ። ያሳለፍሽው ነገር ትዝ ሲልሽ ትከፊያለሽ። እና አለቅሳለሁ። ከባድ ነው። የእኔን ሕይወት ይህ ነው ብዬ ልገልፀው አልችልም።"

አስቴር ያለችበትን ሁኔታ እያወራች እያለ እስካሁን አባቷ በሕይወት እንደሌለ የማታውቀው የአራት ዓመት ልጇ ከቤት ወጣች።

"ዓይኔን አቃጥሎኝ ነው የኔ ወርቅ፤ ሂጂ ግቢ" አለቻት የእናቷን ማልቀስ በማየቷ ለተጨነቀችው ሕፃን።

አስቴር ምንም እንኳ የሕይወት አጋሯን በግፍ ብትነጠቅም፤ ለልጇ ስትል ጠንካራ መሆን እንዳለባት ታምናለች።

ግን ዛሬም ድረስ የባለቤቷን ሞት አምና መቀበል አልቻለችም። ይመጣል ብላ ተስፋ ታደርጋለች።

". . .ለልጄ መቆየት አለብኝ። ልጄ አባቷን አጥታ አሁን ደግሞ እኔን እንድታጣኝ አልፈልግም። ቢከፋኝም እነርሱን [ልጇ እና እናቷን] አስብና መልሼ እበረታለሁ።

"ምንም ተስፋ የማደርገው ነገር የለኝም"።

*ስማቸው ለደኅንነታቸው ሲባል የተቀየረ

ማስታወሻ፡ የተጎጂ ቤተሰቦች ማንነት እንዳይለይ አንዳንድ መረጃዎችን እና የአካባቢ ስሞችን ከመጥቀስ ተቆጥበናል።