አሜሪካዊው ጋዜጠኛ በሚየንማር የ11 ዓመት እስር ተፈረደበት

ዳኒ ፌንስተር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሚየንማር ወታደራዊ ፍርድ ቤት በአሜሪካዊው ጋዜጠኛ ዳኒ ፌንስተር ላይ የ11 ዓመት እስር ፈረደበት።

ዳኒ ፌንስተር የአገሪቱን ኢሚግሬሽን ሕግን በመጣስ፣ በሕገወጥ ማኅበር ምስረታ እና በጦር ኃይሉ ላይ ተቃውሞን በማበረታታት ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

ጋዜጠኛው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሁለት ተጨማሪ የአመጽ እና የሽብርተኝነት ክሶች የቀረበበት ሲሆን እነዚህ ወንጀሎች በአገሪቱ ሕግ መሰረት ከፍተኛ የእድሜ ልክ እስራት የሚያስቀጡ ናቸው።

የአዳዲሶቹ ክሶች የፍርድ ሂደትም በሚቀጥለው ሳምንት ይጀምራል።

የ37 ዓመቱ ጋዜጠኛ 'ፍሮንቲየር ሚየንማር' የተባለ ድረ-ገፅ ዋና አዘጋጅ ሲሆን በቁጥጥር ስር የዋለውም በዋና ከተማዋ ያንጎን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ነው።

በየካቲት ወር በአገሪቱ የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ከታሰሩ በደርዘን የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነው።

ፍሮንቲየር ሚየንማር ድረ-ገፅ እንዳስታወቀው ዳኒ ከመፈንቅለ መንግሥቱ ወዲህ የጦር ኃይሉን በከፍተኛ ሁኔታ ሲተች ለነበረው 'ሚየንማር ናው' ለተባለ ገለልተኛ የዜና ጣቢያ ቀደም ብሎ ሲሰራ ነበር ብሏል።

"በአሁኑ ወቅት የተፈረደበት ክስ የተመሰረተው ሚየንማር ናው በተባለውና በታገደው መገናኛ ብዙኃን ይሰራ ነበር በሚል ነው። ዳኒ ከሁለት ዓመት በፊት ሐምሌ ወር ላይ ከሚየንማር ናው ለቆ በሚቀጥለው ወር ፍሮንቲየር ሚየንማርን ተቀላቅሏል። በቁጥጥር ስር በዋለበት ግንቦት ወር ላይም በፍሮንትየር ሚየንማር እየሰራ በነበረበት ወቅት ሲሆን፤ ዘጠኝ ወራትም ሰርቶ ነው የታሰረው" በማለት የሚሰራበት ድረ ገፅ አስታውቋል።

አክሎም "እነዚህ ዳኒ የተወነጀለባቸው ክሶች ውሃ የማይቋጥሩና መሰረት የሌላቸው ናቸው" ብሏል።

ሌላኛው ጃፓናዊ ጋዜጠኛ የሐሰት ዜና አሰራጭቷል በሚል ክስ ከወራት በፊት በቁጥጥር ስር ውሎ ነበር።

ለአብዛኞቹ የጃፓን ዋና ዋና የዜና ማሰራጫዎች ሲዘግብ የነበረው ዩኪ ኪታዙሚ በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ጥቂት የውጭ ጋዜጠኞች አንዱ ነበር።

የሚየንማር ባለሥልጣናት ሕጉን ጥሷል ብለው ቢከሱትም ነገር ግን ጃፓን ስለጠየቀች ከእስር ተለቋል።