በሕንድ የተፈፀመ ዘግናኝ የቡድን የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ዳግም ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Shahnawaz Ahmad
በሕንድ መዲና ዴልሂ አውቶብስ ላይ የአንዲት ሴት በቡድን መደፈር በመላው ዓለም መነጋገሪያ ከሆነ ከ13 ዓመታት በኋላ በቢሃር ግዛት ተመሳሳይ እና ዘግናኝ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ተፈጽሟል።
የመብት ተሟጋቾች የተጎጂዋ ታሪክ ፖሊስ እና የሕክምና ባለሥልጣናት ወሲባዊ ጥቃት በተለይም በሕንድ በተመለደባቸው በአነስተኛ ከተሞች እና መንደሮች ሴቶች ላይ የሚያሳዩት ግዴለሽነት አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ዘገባ የያዛችው አንዳንድ ዝርዝሮች የሚረብሹ ሊሆኑ ይችላል።
የሕንድ ሕግ የወሲባዊ ጥቃት ተጎጂዎች ስማቸው እንይገጽ ስለሚደነግግ የተጎጂዋን ስም ሶማ ብለነዋል (ትክክለኛ ስሟ አይደለም)።
የ28 ዓመቷ የአራት ልጆች እናት ለቢቢሲ ሂንዲ በቤቷ ውስጥ በቡድን የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እንደፈተጸመባት እና ቁሳቁሶች በማህፀኗ ውስጥ እንደከተቱ ተናግራለች።
ጥቃቱ የተፈፀመው ሰኔ 4/2018 ዓ.ም. በሕንድ ደሃ ማኅበረሰብ ተብሎ በይፋ ዕውቅና በተሰጠበት ወረዳ ጉሳሬ በተባለ መንደር ነው።
የሕክምና ባለሥልጣናት ጥቃቱን አረጋግጠው ቁሳቁስ በማህፀኗ ውስጥ እንደተገኘ እና ሐኪሞች እንዳወጡት ካሳወቁ በኋላ የቡድን የአስገድዶ መድፈር ጥቃቱ አገራዊ ትኩረት አግኝቷል። ተጎጂዋ የጥይት ቀለህ ይዛ የቀረበች ሲሆን፤ ቀለሁ በማህፀኗ ውስጥ ከገቡ ቁሳቁሶች ውስጥ አንዱ መሆኑን ተናግራለች።
ስለ ጥቃቱ ዝርዝር መረጃ የሰጠችው ሶማ ምሽት ላይ አንድ ክፍል ከሆነው ቤቷ ውጪ ከሚገኘው መፀዳጃ ቤት ሳለች አምስት ወንዶች እንደመጡ ተናግራለች። መፀዳጃው በር የለውም፤ ለግላዊነት መጠበቂ እንዲሆን መጋረጃ ብቻ አለው።
"ልብሴን አወለቁ፤ አፌን ሸፍነው እጆቼን አሰሩኝ። ለመታገል ስሞክር ደረቴን በስለት ቆረጡኝ እና ደፈሩኝ" ትላለች።
ባለቤቷ በመጀመሪያ የሰማው ድምፅ የድመት ድምፅ መስሎት ከቤት አልወጣም። ነገር ግን በኋላ ላይ በመጠራጠሩ ለማየት ሞክሯል።
"ነገር ግን ቤቱ ከውጭ ተዘግቷል። ጎረቤት ጠርቶ በሩን ከተከፈተ በኋላ ሁሉም ሁኔታየን ተመለከተ፤ ማልቀስ ጀመሩ።"

የፎቶው ባለመብት, Shahnawaz Ahmad
የበጉዳሪ የፖሊስ ተቆጣጣሪ ማኔሽ (የመጀመሪያ ስማቸውን ብቻ የሚጠቀሙ) ለቢቢሲ የሶማ "የሕክምና ሪፖርት ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባት አረጋግጧል" ብለዋል።
"በዚህ መዝገብ ሦስት ሰዎች እና ሁለት ያልተለዩ ሰዎች ተጠርጥረዋል። ሁለቱን በቁጥጥር ስር አውለናቸዋል። ለዚህ መዝገብ የተመሠረተው ልዩ የምርመራ ቡድን ሌሎችን በቁጥጥር ስር ለመዋል ብርበራ እያደረገ ነው፤ እና ምርመራው እንደቀጠለ ነው" ሲሉ አክለዋል።
ፖሊስ ከተጠረጠሩት መካከል አንዳንዶቹ ከዚህ ቀደም የወንጀል ክስ ያላቸው መሆናቸውን ተናግሯል። ግለሰቦቹ የቡድን የአስገድዶ መድፈር አንቀፆችን በመተላለፍ ተጠርጥረዋል ብለዋል።
አሰቃቂ ጥቃቱ በተፈጸመባት ምሽት ሶማ ከፖሊስ እና ከሕክምና ባለሥልጣናት አነስተኛ እገዛ እንዳገኘች ተናግራለች።
የባጃጅ አሽከርካሪ የሆነው ባለቤቷ ከቤታቸው ሦስት ኪሎ ሜትር ወደሚርቀው ፖሊስ ጣቢያ ራሷን የሳተችውን ባለቤቱን ታቅፎ እንደሄደ ተነግሯል። ፖሊስ መዝገብ ከፍቶ አቤቱታ ለመቀበል አሻፈረኝ ብሎ እንደመለሰው እና ይልቁንም ወደ ሐኪም እንዲወስዳት እንደመከረው ተናግሯል።
ከዚህ በኋላ የፖሊስ ጣቢያው አዛዥ ራጂቭ ኩማር "በቸልተኝነት፣ በግዴለሽነት እና ሃዘኔታ በመንፈግ" መታገዳቸውን የአካባቢው ፖሊስ አስታውቋል። በመዝገቡ ላይ የመጀመሪያ የመረጃ ሪፖርት በፖሊስ ጣቢያው የተመዘገበው ከጥቃቱ ከሁለት ቀን በኋላ ነው።
ከጥቃቱ በኋላ ሶማ እና ባለቤቷ የተሻለ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውን ተናግረዋል።
በጥቃቱ ምሽት በአቅራቢ ካለ የግል ክሊኒክ ሕክምና ሳታገኘ መልሷታል። ክሊኒኩ የድንገተኛ አደጋ ሕክምና እንደማይሰጥ እና አገልግሎት የሚሰጡ ተረኛ ዶክተሮች እንደሌለው ተናግሯል። ሶማ ከዚህ በኋላ መንግሥታዊ ወደ ሆነ የማኅበረሰብ ጤና ጣቢያ ተወስዳ የመጀመሪያ እርዳታ ካገኘች በኋላ ወደ ሆስፒታል በቀጥታ ሪፈር ተብላለች።

የፎቶው ባለመብት, Shahnawaz Ahmad
ሶማ ለቢቢሲ በሆስፒታሉ ያገኘችው የመጀመሪያ ሕክምና ያላረካ እንደነበር ተናግራለች።
ሰኔ 5/2018 ዓ.ም. ስትነቃ ለባለቤቷ እና ለሐኪሞች እንደተደፈረች ተናግራለች። "ዶክተሯ መድኃኒት እየወጋችኝ 'ተደፍረሽም ነበር?' ብላ ጠየቀችኝ። 'አዎ' እያልኩ እና መናገር ቀጠልኩ" ትላለች።
ይሁን እንጂ በበጉሳሪ የቀዶ ሕክምና ሐኪም የሆኑት አሾክ ኩማር ሶማ ከሆድ ህመም ጋር በተያያዘ ጉዳይ ወደ ሆስፒታል እንደመጣች ለቢቢሲ ተናግረዋል። ስለ አስገድዶ መድፈሩ በማግስቱ "ሐኪሞች የሕክምና ምርመራ ካደረጉ በኋላ" እንዳወቁ ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ ይህን ካደረገ በኋላ ሶማ ወደ ቤቷ የተላከች ቢሆንም ራሷን በመሳቷ በሚቀጥለው ቀን ወደ ሆስፒታል መመለሷን ባለቤቷ ለቢቢሲ ተናግሯል። ከዚያም ከአንድ ቀን በኋላ ከሆስፒታል ወጥታለች።
"ራሷን መሳቷን በመቀጠሏ እና ሆዷ ላይ ከባድ ህመም እንደሚሰማት በተደጋጋሚ በመናገሯ የመንደሩ አዋላጅ ነርስ አይታታለች። ሰውነቷ ውስጥ የሆነ ነገር እንዳለ አስጠነቀቀችን። ሰኔ 11 ጠዋት ላይ ሶማ ከማህፀኗ የወጠውን የጥይት ቀለህ አሳየችን" ይላል፤ ከዚህም ወደ ሆስፒታል ዳግም እንደወሰዷት በመግለጽ።
"ባዶ ቀለህ ነበር" በማለት ሐኪም ኩማር ተናግረዋል። "በድጋሚ መረመርናት እና ዶክተሮች ቁሳቁሶችን አስወገዱላት። አሁን ላይ ደህና ናት፤ እያገገመች ነው።"
የሶማ ጥቃት በሕንድ ቁጣን ቀስቅሷል። የመብት ተሟጋቾች በአውሮፓውያኑ 2012 በዴልሂ በቡድን ከተደፈረች በኋላ ሕይወቷ ያለፈውን የ23 ዓመት የህክምና ተማሪ ዘግናኝ ጥቃት እንዲያስታውሱ አድርጓቸዋል።
ወንጀሉ ዓለም አቀፍ ቁጣ በመቀስቀስ፤ በመላው ሕንድ ደግሞ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል። ዘመቻው በከባድ ጥቃቶች የሞት ፍርድን ጨምሮ ጠንካራ የፀረ አስገድዶ መድፈር ሕጎች እንዲወጡ ገፍቷል።
በጥቃቱ ጥፋተኛ የተባሉ አራት ወንዶች በ2020 በሞት ተቀጥተዋል፤ አንዱ በእስር ቤት ሕይወቱ ሲያልፍ፤ ዕድሜው ያልደረሰ ወንጀለኛ በማገገሚያ ማዕከል ታስሮ ከቆየ በኋላ ተለቅቋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከዚህን ጊዜ በኋላ ምንም እንኳ በወሲባዊ ወንጀል ፈጻሚዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ቢጠናከርም በየዓመቱ በሕንድ 30 ሺህ የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች ይመዘገባሉ።
የፀረ አስገድዶ መድፈር ጥቃት የመብት ተሟጋች የሆነችው ዮጊታ መሃያና "ምንም ትምህርት አልወሰድንም" ትላለች። ማኅበረሰቡ ለዘግናኝ ጥቃቶች ስሜት ባለመስጠቱ አብዛኞቹ ጥቃቶች ሪፖርት እንደማይደረጉ እና እንደሚደበቁም ታክላለች።
"እነዚህ ዓይነት ጥቃቶች መፈጸማቸው ቀጥሏል፤ ምክንያቱም መልዕክት በእያንዳንዱ የሕንድ ክፍል አልተዳረሰም። አስገድዶ መድፈር የሞት ቅጣት እንደሚያስቀጣ አልታወቀም። በማኅበረሰቡ ውስጥ ፍርሃት አልሰረጸም" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
"የሶማ ጥቃት የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ያገኘው በማህፀኗ ውስጥ የጥይት ቀለህ በመገኘቱ ምክንያት ነው። ቢያንስ እርሷ ተርፋለች፤ ይህን እንደ አዎንታ እመለከተዋለሁ" ብላለች።
በበጉሳሩ ሶማ የሆስፒታል አልጋ ላይ ናት። በጠያቂዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሰጪዎች ተደጋጋሚ ጉብኝት ትረበሻለች። አሁንም በከባድ ህመም ላይ ናት። ነገር ግን ቶሎ አገግማ ወደ ልጆቿ ለመመለስ ተስፋ ይዛለች።
"ልጆቼ በጣም ያስጨንቁኛል። ገና ልጅ ናቸው። ከዚህ 35 ኪሎ ሜትር በሚርቅ መንደር ውስጥ ዘመድ ጋር ይገኛሉ። ወደ ቤቴ፤ ወደ እነርሱ መመለስ እፈልጋለሁ።"















