ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ማሸነፉ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister-Ethiopia
ገዢው ብልጽግና ፓርቲ በሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛውን መቀመጫ በማግኘት ማሸነፉን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
በዚህም መሠረት ብልጽግና ፓርቲ ከ547 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች 438 አሸንፏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እሁድ ሰኔ 14/2018 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ ባካሄደው ሥነ ሥርዓት የተረጋገጡ እና የፀደቁ የምርጫው ውጤቶችን ይፋ አድጓል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተቃዋሚ ፓርቲዎች 41፣ የግል ዕጩዎች ደግሞ 8 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ማሸነፋቸውን በተጨማሪ ይፋ ሆኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት ብልጽግና ፓርቲ የአሁኑን ምርጫ ሲያሸንፍ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ብልጽግና በአዲስ አበባ ከተማ 20 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን፣ በአማራ ክልል 117፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ 8፣ በጋምቤላ ክልል 3፣ በኦሮሚያ ክልል 167 መቀመጫዎች ማሸነፍ ችሏል።
በሲዳማ ክልል እንዲሁ 13 መቀመጫዎችን፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ 17፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ደግሞ 35 መቀመጫዎች አሸንፏል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ 28 መቀመጫዎች በሶማሌ ክልል ደግሞ 19 መቀመጫዎች አሸንፏል።
በዚህ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሌላ ጦርነት ሊከሰትበት ይችላል ተብሎ በተሰጋበት እና 38 መቀመጫዎች ባሉት በትግራይ ክልል ለሁለተኛ ጊዜ መራጮች አልተሳተፉም።
የፌደራል መንግሥቱ እና የህወሓት መሪዎች አንዳቸው ሌላኛቸውን ጦርነቱን ያስቆመውን የፕሪቶሪያ ስምምነትን ባለማክበር እየተካሰሱ ነ።ው
በተመሳሳይም የአገሪቱ አብኛውን የሕዝብ ብዛት እና የቆዳ ስፋት በሚሸፍኑት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ካለው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ አካባቢዎች ምርጫ አልተካሄደም።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ግንቦት 24/2018 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫ ላይ "በጥቂት የምርጫ ክልሎች ካጋጠሙ ችግሮች በስተቀር፣ ሂደቱ ስኬታማ" እንደነበር ገልጿል። ድምጽ ባልተሰጠባቸው የምርጫ ክልሎች መራጮች ድምጻቸውን እንዲሰጡ እንደሚደረግ ነገር ግን ቀኑ መቼ እንደሚሆን ቦርዱ አልገለጸም።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ በሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ 438 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ማሸነፍ ችሏል።
ይህም ከፍተኛ ቁጥር በመሆኑ በሚቀጥለው ዓመት መስከረም ማብቂያ ላይ በብልጽግና ፓርቲ የሚመራ መንግሥት የሚመሠረት ይሆናል። በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለቀጣይ አምስት ዓመታት በመንበራቸው ላይ ሊቀጥሉ ይችለሉ።















