አሸናፊው ብልጽግና እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስለ ምርጫው ውጤት ምን አሉ?

የአብን ሊቀ መንበር በለጠ ሞላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የኢዜማ መሪ ኢዮብ መሳፍንት

የፎቶው ባለመብት, MoIT/Abiy Ahmed/EZEMA

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ አሸናፊ የሆነው ብልጽግና ፓርቲ፤ "ዘላቂ ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን" እንዲሁም "የሕግ የበላይነትን በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት" በቁርጠኝነት እንደሠሚራ አስታወቀ።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) "የዜጎች የደኅንነት ዋስትናን የማረጋገጥ" እና "በሃይማኖት እና በብሔር ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን የማስቆም" የአሸናፊው ፓርቲ "ጊዜ የማይሰጣቸው" የቤት ሥራዎች እንደሆኑ ገልጿል።

"ብሔራዊ ጥቅሞችን በሚያሳኩ ጉዳዮች" ላይ "ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃይል" መተባበር እንደቀሚጥል ያስታወቀው፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በበኩሉ ብልጽግና ፓርቲ "ፍትሐዊ የፖለቲካ ምኅዳርን ለሁሉም እኩል ተደራሽ" እንዲያደርግ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እሁድ ሰኔ 14/2018 ዓ.ም. ባካሄደው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ማሳወቂያ መርሃ ግብር ላይ ብልጽግና ፓርቲ መንግሥት መመረሥት የሚያስችለውን አብላጫ ድምፅ ማሸነፉን አስታውቋል።

ከምርጫ ቦርድ እወጃ በኋላ እሁድ መግለጫ ያወጣው ብልጽግና፤ ውጤቱ ሕዝብ ለፓርቲው "አዲስ የዴሞክራሲ እና ማኀበራዊ ውል" መስጠቱን እንደሚያመለክት ገልጿል። በዚህ መሠረት "የሥልጣን ባለቤትነቱ የሕዝብ መሆኑን በተግባር" እንደሚያረጋግጥ አስረድቷል።

"መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጠንን የዴሞክራሲ ውል በታላቅ ትህትና እና በከፍተኛ አክብሮት እንቀበላለን" ያለው አሸናፊው ፓርቲ፤ በስኬቱ እንደማይኩራራ ይልቁንም "ጉድለቶቹን እያረመ ሕዝብን በቅንነት ለማገልገል" ፅኑ እምነት እንዳለው አስታውቋል።

ፓርቲው በመንግሥትነት በሚቆይባቸው ቀጣይ ዓመታት "የሕዝብ ጥያቄዎች የሆኑና የጋራ ጥረት በሚጠይቁ ቁልፍ ጉዳዮች" ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚረባረብ ቃል ገብቷል። ይህንን የሚያደርገውም ከሕዝብ እና "ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በሙሉ በመተባበር" መሆኑም ጠቅሷል።

ፓርቲው ከዚህ ጋር በተያያዘ በቁርጠኝነት ለመሥራት ከዘረዘራቸው ጉዳዮች ውስጥ በቀዳሚነት የተጠቀሰው "ዘላቂ ሰላም እና ፀጥታን ማስፈን" እንዲሁም "የሕግ የበላይነትን በፅኑ መሠረት ላይ የመገንባት" ጉዳይን ነው።

"በመገባደድ ላይ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ሂደት የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ በሚገባ" እንደሚደግፍም አስታውቋል። ለዚህም ሲባል "የዴሞክራሲ ተቋማትን ይበልጥ ነፃ፣ ገለልተኛ እና ጠንካራ እንዲሆኑ" እንደሚያደርግ የገለጸው ፓርቲው፤ "ብሔራዊ ጥቅሞችን ማዕከል ባደረገ መልኩ" ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በትብብር እንደሚሠራ በመግለጫው አስፍሯል።

ብልጽግና በመግለጫው "የኑሮ ውድነትን ለማቃለል እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ዘላቂ የሥራ ዕድሎችን በስፋት ለመፍጠር" የጀመራቸውን ሥራዎች እንደሚያስቀጥል ገልጿል። የዜጎችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እና ሀገራዊ አስተዋጽኦ ማሳደግም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ተጠቅሷል።

የቢሮክራሲ "ማነቆዎችን ለመበጣጠስ"፣ የአገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ ለማዘመን እንዲሁም ሌብነትን እና ብልሹ አሠራርን "በቆራጥነት ለመከላከል" እንደሚሠራም አስታውቋል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምን አሉ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአጠቃላይ ምርጫ ውጤት ይፋ መሆኑን በማስመልከት መግለጫ ካወጡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል አንዱ 13 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም 73 የክልል ምክር ቤት ወንበሮችን በማሸነፍ ባገኘው የመቀመጫዎች ብዛት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ቀዳሚ የሆነው ኢዜማ ነው።

ፓርቲው ሰኞ ሰኔ 15 ባወጣው መግለጫ አሸናፊ ለሆነው ብልጽግና እና ሌሎች ድምፅ ያገኙ ተፎካካሪዎች "የእንኳን ደስ አላችሁ" መልዕክት አስተላልፏል። አሸናፊው ፓርቲ የዴሞክራዊ ምኅዳርን የማስፋት ጉዳይ ላይ እንዲሠራ ኢዜማ ጥሪውን አቅርቧል።

ብልጽግና "ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለመገንባትና ፍትሐዊ የፖለቲካ ምኅዳርን ለሁሉም እኩል ተደራሽ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንዲሠራ" ጠይቋል። አሸናፊው ፓርቲ "ለሀገር እድገትና ለውጥ ጠቃሚ ሀሳቦች ከማንኛውም ወገን ሊገኙ እንደሚችሉ" እንዲረዳ እና "አማራጭ ሃሳቦችን እንዲሰማ" የሚል ጥሪም አሰምቷል።

"ትችቶችን በሆደ ሰፊነት እያስተናገደ ሀገራችን የሚያስፈልጋትን ዴሞክራሲ በጋራ እንድንገነባ ጥሪ እናቀርባለን" ብሏል።

"በድምሩ 86 መቀመጫዎችን በማግኘት በሀገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚው ተፎካካሪ ፓርቲ" መሆኑን በመግለጫው ያነሳው ኢዜማ፤ "ተጨባጭ የተፎካካሪ ፓርቲነት ሚናውን ጊዜ ሳያባክን የሚጀምረው ዛሬ መሆኑን" አስታውቋል።

በቀጣዮቹ ዓመታት "ጠንካራ ጎኖችን" እንደሚያስቀጥል እንዲሁም "የነበሩበትን ክፍተቶች በስትራቴጂ እና ሌሎች አስፈላጊ ተግባራት" እንደሚሞላም ጠቅሷል።

ኢዜማ "ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ባሉት ዓመታት" ለማከናወን ቃል የገባበት ዋነኛ ጉዳይ "ጤናማ እና ዘመናዊ የፖለቲካ ባሕል የማዋለድ ተግባራችንን በተጠናከረ መልኩ [እንቀጥላለን]" የሚል ነው።

በዚህም መሠረት 'ከዚህ ቀደም ሲያደርግ' እንደነበረው "ብሔራዊ ጥቅሞችን በሚያሳኩ ጉዳዮች [ላይ] ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃይል ጋር" እንደሚተባበር ገልጿል። " የምንንቀሳቀስበት መፎካከሪያ አጀንዳዎች ላይ ማኅበረሰባችንን በሚመጥን ጨዋነት ልዩነቶቻችንን እና ትችቶቻችንን [እናቀርባለን]" ሲልም አቋሙን ገልጿል።

የምርጫ ውጤት ይፋ ማድረጊያ ስነ ስርዓት

የፎቶው ባለመብት, National Election Board of Ethiopia

ሌላኛው ተቃዋሚ ፓርቲ አብን በበከሉ "ሕዝባችን ለሰላም ሲባል ውድ ዋጋ ከፍሎ ያሸነፈበት ወሳኝ የታሪክ እጥፋት" ሲል ምርጫውን ገልጾታል። ምርጫው "በአማራ ክልል የትጥቅ እንቅስቃሴ እያደረጉ ላሉ ኃይሎችም… ጠቃሚ መልዕክቶችን" እንዳስተላለፈም እሁድ ዕለት ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።

ሕዝቡ በምርጫው አማካኝነት "የፖለቲካ ተሳትፎ መብት እና ነጻነቱን በኃይል የሚገፉ የጎበዝ አለቃዎች አዋጅን" እንዲሁም "የተፈጸመውን ጥቃት እንደሚቃወመው" ማሳወቁን ገልጿል።

ሕዝቡ "ለሰላማዊ ትግል እና ለሀገራዊ የፖለቲካ ምኅዳር መጠናከር" ያለው ጽኑ ፍላጎት በምርጫው መታየቱን የገለጸው አብን፤ "ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የታጠቁ ቡድኖች ጭምር የሕዝቡን ውሳኔ የማክበር ግዴታቸውን እንዲወጡ" ጠይቋል።

"የሽምቅ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞቻችንም ወደ ፖለቲካዊ መድረክ በመምጣት በሕዝቡ ላይ የተጫነውን የመከራ ቀንበር እንዲያቀሉለት ጥሪ እናቀርባለን" ብሏል።

አሸናፊው ብልጽግና ፓርቲም በዚህ ምርጫ "ከወትሮው የተለየ ኃላፊነት እና የማይደገም ዕድል" እንደተሰጠው የአብን መግለጫ ያትታል። አብን፤ አዲስ የሚመሠረተው መንግሥት አሉበት ያላቸውን "ጊዜ የማይሰጣቸው" የቤት ሥራዎች ጠቅሷል።

በቀዳሚነት የተቀመጠው "በመላው ሀገሪቱ ሕግ እና ሥርዓትን በማስከበር ለዜጎች የደኅንነት ዋስትናን የማረጋገጥ" ሥራ ነው። "በሃይማኖት እና በብሔር ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን የማስቆም" እና "ተንቀሳቅሶ የመሥራት ነጻነትን የማስከበር" ተግባራትም ተካትተዋል።

"አገራዊ ጥቅሞችን የማስጠበቅ" ኃላፊነትንም በድኅረ-ምርጫ መከናወን ካለባቸው የመንግሥት የቤት ሥራዎች መከካል ጠቅሷል።

የምርጫ ሳጥኖች

የፎቶው ባለመብት, National Election Board of Ethiopia

"በተለይም በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልሎች የሰላም አማራጭን እየተቀበሉ" ያሉ ታጣቂዎች የሚስተናገዱበት ሂደት "ተቋማዊ ሥርዓት" እንዲዘረጋለት ጠይቋል።

አማራ "በመሠረተ-ልማት ወደ ኋላ እንዲቀር የተደረገ" ክልል መሆኑን በመግለጫው ያነሳው አብን፤ "በቀሪዋ ኢትዮጵያ እየደረሱ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች እየተቀረጹ እንዲተገበሩ" አሳስቧል። "የተቋረጡ ልማቶችን በማስቀጠል ላይ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ" እንዲሁም የሕዝቡ "የመልሶ ግንባታ እና የአዲስ ልማት ተጠቃሚነቱ በተጨባጭ እንዲረጋገጥ" ጠይቋል።

በተጨማሪም አብን "የወልቃይት እና ራያ ሕዝብ ከመደበኛው የምርጫ መርሃ-ግብር ውጪ በመደረጉ" ቅሬታውን ገልጿል።

የሚመሠረተው መንግሥት እና ምርጫ ቦርድ በእነዚህ አካባቢዎች "አፋጣኝ ምርጫ በማከናወን እና ነጻ የሕዝብ አስተዳደር እንዲዋቀር በማገዝ ዋጋ ለተከፈለባቸው የመብት ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጡ" ጠይቋል።

በአማራ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤቶች ወንበሮችን ያሸነፈው የወሎ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲም (ወዴፓ) መግለጫ ካወጡት ተቃዋሚዎች መካከል ነው።

"ሕዝብ በይሁንታ የተጠውን ድምፅ" እንደሚያከብር ያስታወቀው ፓርቲው፤ ለአሸናፊው ብልጽግና እና መራጩ ሕዝብም "እንኳን ደስ አላችሁ" ብሏል።

ቀጣዩ አምስት ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ "ሁለንተናዊ ችግሮች ሙሉ በሙሉ" እንደሚቀረፉ እና የሀገራዊ ምክክሩ "በውጤት የሚጠናቀቅበት" ይሆናል የሚል እምነቱን ገልጿል።

"ፓርቲያችን በሀገር ሉዓላዊነት፣ የልማት እና የእድገት ጉዞን የሚያደናቅፉ የውጭም ሆነ የውጥ የጥፋት ኃይሎችን ከመንግሥት ጎን ቆመን የምንታገል መሆኑን እናረጋግጣለን" ሲልም ቃል ገብቷል።